ድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን ሠራተኞቹ ትግራይ ውስጥ የተገደሉት ሆን ተብሎ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የስፔን ድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ፕሬዝደንት ፓውላ ጊል ከወራት በፊት ሠራተኞቻቸው በትግራይ የተገደሉት ሆን ተብሎ ተተኩሶባቸው ነው አሉ።
ፕሬዝደንቷ ሦስቱ የድንበር የለሸ የሃኪሞች ቡድን ባልደረቦች የተገደሉት በተኩስ ልውውጥ መካከል ሳይሆን ሆን ተብሎ በቅርብ ርቀት በተደጋጋሚ በጥይት ተመትተው ነው ብለዋል ዛሬ ባወጡት መግለጫ።
ሰኔ 17/2013 ዓ.ም. ሦስት የድርጅቱ ሠራተኞች በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ሥራ እየተጓዙ ሳለ ማንነታቸው ባልታወቁ ጥቃት ፈጻሚዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በጥቃቱ የተገደሉት የስፔን ዜግነት ያላት የ32 ዓመቷ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ የሆነችው ማሪያ ኽርናንዴዝ፣ ከመገደሉ ከጥቂት ወራት በፊት በድርጅቱ በረዳት አስተባባሪነት ሥራ የጀመረው የ31 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ዮሐንስ ሐለፎም እና ለግብረ ሰናይ ድርጅቱን አሸከርካሪ ሆኖ ያገለግል የነበረው የ31 ዓመቱ ቴድሮስ ገብረ ማሪያም ናቸው።
የሰፔን ድንበር የለሸ የሃኪሞች ፕሬዝደንት ፓውላ ጊል ምንም እንኳ ግለሰቦቹ ከተገደሉ ወራት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ ለግድያው ተጠያቂ የሆነ አካል የለም ብለዋል።
"ማሪያ፣ ቴዎድሮስ እና ዮሐንስ ከተገደሉ 6 ወራት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ ግድያቸውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልተገኘም፤ ለግድያው ተጠያቂ የሆነ አካል የለም" ብለዋል።
ሦስቱ ሠራተኞች ሰኔ 17 ለሥራ ጉዞ ከጀምሩ በኋላ ከድርጅቱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ በማግስቱ አስክሬናቸው ሲጓዙበት ከነበረው መኪና ከ100 እስከ 400 ሜትር ርቆ መገኘቱን ፕሬዝዳንቷ ይናገራሉ።
አስካሁን ድረስ ለሦስቱ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሠራተኞች ግድያ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም።
ከግድያው በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በግድያው የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው አቢ አዲ ተብሎ በሚጠራ "ህወሓት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ" መሆኑን አመልክቶ ነበር።
ጨምሮም እንዲህ አይነቱን "ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቀረት የእርዳታ ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ወታደራዊ እጀባ እንዲደረግላቸው መንግሥት ያቀረበው ጥሪ ትክክል መሆኑን ያመለክታል" ብሎ ነበር።
ህወሓት በበኩሉ ለእርዳታ ሠራተኞቹ ግድያ የመንግሥት ወታደሮችን ተጠያቂ አድርጎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Msf
ኤምኤስኤፍ ስለ ግድያው የሚያውቀው
ድንበር የለሸ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ባለፉት 6 ወራት ሠራተኞቹን ምን እንዳጋጠማቸው ለማወቅ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያካሂድ እንደቆየ ፕሬዝደንቷ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።
የሠራተኞቹ ግድያ እንዲመረመር እና ውጤቱም ለድርጅቱ እንዲገለጽ ከኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትሮች ጋር በተደጋጋሚ መገናኘታቸውን እና ለህወሓትም ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን ፖውላ ጊል ገልጸዋል።
ፕሬዝደንቷ ከዚህ በተጨማሪም ኤምኤስኤፍ የተለያየ የደኅንነት መረጃዎችን በመሰበሰብ እና በመመርመር፤ የኤምኤስኤስ ሠራተኞች የተጓዙበት መንገድ፣ ክስተቱ የት እና መቼ እንዳጋጠመ መለየት መቻሉን ይገልጻሉ።
ማሪያ፣ ቴዎድሮስ እና ዮሐንስ የተባሉት ሠራተኞች ሰኔ 17/2013 ዓ.ም. በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ይገኙበታል ወደተባለው ሾአተ ኢጉማ ወደተባለ ቦታ ለመሄድ በደቡባዊ አቢ አዲ ጉዞ መጀመራቸውን ያትታሉ።
አንድ ሰዓት በኋላ ጉዞ በኋላ ሾአቴ ኢጉማ አካባቢ እንደደረሱ መኪናቸውን እንዲቆም ተደርጓል። "ከዚያም አስክሬናቸው ሲጓዙ ከነበረበት ተሸከርካሪ ከ100 - 400 ሜትር ርቆ ተገኝቷል። የደረሰባቸው ጉዳት ሁሉም በቅርብ ርቀት በጥይት መመታታቸውን አሳይቷል" ብለዋል ፕሬዝደንቷ።
ይህ መረጃም የሠራተኞቹ ግድያ በተኩስ ልውውጥ መካከል የተከሰተ ሳይሆን፤ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ግድያ ነው ብለዋል ፓውላ ጊል።
"ሠራተኞቻችን የሰብዓዊ ሥራ ሠራተኞች ስለመሆናቸው በግልጽ መለየት ይቻል ነበር። ተሸከርካሪውም የኤምኤስኤፍ አርማ ያረፈበት ነው። ሁለት ባንዲራዎችን ያውለበልብ ነበር" ካሉ በኋላ ተሸከርካሪውም በጥይት መበሳሳቱን እና እንዲቃጠል መደረጉን ገልጸዋል።
ኤምኤስኤፍ ከፌደራሉ መንግሥት ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት ማካሄዱን እና ግድያውን በተመለከተ ምርመራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል ይላሉ ፖውላ ጊል።
ህወሓትም በተመሳሳይ ምርመራ አካሂዶ ውጤቱን ለኤምኤስኤፍ እንዲያጋራ ቢጠየቅም እስካሁን ድረስ በጎ አድራጊ ድርጅቱ የምርመራ ውጤት ማግኘት አልቻልኩም ይላል።
ፕሬዝደንቷ ኤምኤስኤፍ በመጀመሪያ ደረጃ መርመራው የደረሰበትን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማካፈሉን እና ክስተቱ ባጋጠመበት ቦታ እና ሰዓት የመንግሥት ወታደሮች ስምሪትን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠይቀናል ብለዋል።
ድርጅቱ ለህወሓትም ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረቡን ፖውላ በመግለጫቸው አትተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኤምኤስኤፍ ስፔን ፕሬዝደንት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችን በተመለከተ የሚሰጡ ይፋዊ መግለጫዎች በሠራተኞች ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ስለመሆኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሳወቃቸውን በመግለጫቸው አውስተዋል።
እንደ ፕሬዝደንቷ ከሆነ ይፋዊ መግለጫዎችን እና አስተያየቶችን ተከትሎ የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች ተደጋጋሚ የሆነ ማዋከብ፣ ማስፈራሪያ እና እስር እያጋጠማቸው ነው።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በትግራይ የሠራተኞቹን ግድያ ተከትሎ በአቢ አዲ፣ አዲግራት እና አክሱም ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎቹን አቁርጧል።
ከሐምሌ 2013 ጀምሮ መንግሥት የኤምኤስኤፍ የአማራ፣ ጋምቤላ፣ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ እና የሶማሌ ክልል የሥራ ፍቃድን ለሦስት ወራት አቋርጦ እንደነበረ ይታወሳል።















