ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች ሥራውን ማቋረጡን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ ሠራተኞቹ ትግራይ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚያከናውነውን ሥራ ማቋረጡን ገለጸ።
ሰኔ 17/2013 ዓ.ም ትግራይ ክልል ውስጥ ለሥራ እየተጓዙ ሳለ ማንነታቸው ባልታወቁ ጥቃት ፈጻሚዎች የተገደሉት የእርዳታ ድርጅቱ ሠራተኞች ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንዷ ደግሞ የስፔን ዜግነት ያላት ናት።
ድርጅቱ እንዳለው በሠራተኞቹ ላይ በተፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ዙሪያ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግና በክልሉ ውስጥ የእርዳታ ሠራተኞች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ እንዲፈቀድ ጠይቋል።
በሠራተኞቹ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም ኤምኤስኤፍ በትግራይ ክልል ማዕከላዊና ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙት አቢ አዲ፣ አዲግራትና አክሱም ውስጥ የሚያከናውነውን ሥራ ማቋረጡን አስታውቋል።
ነገር ግን ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ ባሉ ሌሎች አካባቢዎች አባላቱ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ ነዋሪዎች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚቀጥሉ ገልጿል።
"በባልደረቦቻችን ላይ ግድያው ከተፈጸመ ሁለት ሳምንት ሊሆነው ቢቃረብም ማንም ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የሌለ ሲሆን በተጨማሪም በግድያው ዙሪያ ስላለው ሁኔታ ምንም ግልጽ ያለ ነገር የለም" ሲሉ የድርጅቱ ኃላፊ ቴሬሳ ሳንክሪስቶቫል ተናግረዋል።
ጨምረውም በባልደረቦቻቸው ላይ በተፈጸመው ግድያ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ምርመራ አድርገው ምን እንደተከሰተና ተጠያቂው ማን እንደሆነ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በዚህም ሳቢያ "በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በጣም ከባድ ነገር ግን አስፈላጊ የሆነውን በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች የምናካሂዳቸውን ሥራዎቻችንን ለማቋረጥ ወስነናል" ብለዋል።
የእርዳታ ሠራተኞቹ ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በጉዞ ላይ እንዳሉ የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡንና በተከታዩ ቀን የሁለቱ ኢትዮጵያውያንና የስፔናዊቷ አስከሬን ይጓዙበት ከነበረው መኪና ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ መገኘቱንም የድንበር የለሽ ሐኪሞች በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቶ ነበር።
በጥቃቱ የተገደሉት የህክምና እርዳታ ድርጅቱ ባልደረቦች በየካቲት ወር ላይ በድርጅቱ በረዳት አስተባባሪነት ሥራ የጀመረው የ31 ዓመቱ ዮሐንስ ሃለፎም፣ በግንቦት ወር ለግብረ ሰናይ ድርጅቱን መሥራት የጀመረው የ31 ዓመቱ ሹፌር ቴድሮስ ገብረ ማሪያም እና ለዓመታት በድንገተኛ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪነት የሠራችው የ34 ዓመቷ ስፔናዊት ማሪያ ኽርናንዴዝ ናቸው።
አስካሁን ድረስ ለሦስቱ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሠራተኞች ግድያ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የሌለ ሲሆን ስለግድያው የወጣ ምንም አይነት ተጨመሪ መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግድያውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው አቢ አዲ ተብሎ በሚጠራ "ህወሓት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ" መሆኑን አመልክቷል።
ጨምሮም እንዲህ አይነቱን "ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን የሚፈጸምን ጥቃት ለማስቀረት የእርዳታ ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ወታደራዊ እጀባ እንዲደረግላቸው መንግሥት ያቀረበው ጥሪ ትክክል መሆኑን ያመለክታል" ብሏል።
ከመንግሥት ሠራዊት ጋር ለስምንት ወራት በጦርነት ውስጥ የቆየው የህወሓት ኃይልም በበኩሉ በእርዳታ ሠራተኞቹ ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዞ ድርጊቱ በመንግሥት ወታደሮች የተፈጸመ ነው ሲል ገልጾ ነበር።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በመደገፍና በማቋቋም እንዲሁም የህክምና ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች እርዳታን እያደረገ ያለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በባልደረቦቹ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም አገልግሎቱን አሁን ለማቋረጥ በወሰነባቸው አካባቢዎች ውስጥ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የተለያየ አይነት የጤና አገልግሎቶች ሲያርብ መቆየቱን ገልጿል።
የአገልግሎቱ መቋረጥም በርካታ ሰዎች ከረድኤት ድርጅቱ ሲያገኙት የነበረውን የሰብአዊና የጤና ድጋፎችን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
















