ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ሥራውን ማቋረጡን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በተጣለበት ዕገዳ መሠረት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚያከናውናቸውን ሥራዎቹን ማቋረጡን አስታወቀ።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የተጣለበትን የሦት ወራት ዕገዳን በማክበር በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በደቡብና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሥራውን አቁሟል።
ድርጅቱ በተጠቀሱት አካባቢዎች ያለውን ሥራውን ቢያቋርጥም "በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ጉጂ፣ በደቡብ ክልልና በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ውስጥ የህክምናና የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎቱን ይቀጥላል" ብሏል።
የእገዳ ትዕዛዙ ከተሰጠው በኋላ የሚደረገው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚሰጠውን የህክምናና የሰብአዊ እርዳታ ሥራዎችን ጨምሮ ሁሉንም ተግባራቱን ለሦስት ወራት ማቋረጡን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ኤምኤስኤፍ ባሉት ክሊኒኮች ውስጥ የነበሩ ታካሚዎች በአጭር ማስጠንቀቂያ እንዲወጡ መደረጉንና አንድ ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞቹ ከቤታቸው ሆነው እንዲጠባበቁ እንዲሁም ሁሉም በሚባል ደረጃ የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ሠራተኞቹ ከአገሪቱ እንዲወጡ መደረጋቸውን አመልክቷል።
ድርጅቱ እነዳለው የሚያካሂደው የህክምናና የሰብአዊ እርዳታ ሥራ እንዲያቋርጥ የታዘዘው በአገሪቱ ያለው የተለያየ አይነት የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ከፍተኛ በሆነበት ጊዜ መሆኑን ገልጿል።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሥራውን ማከናወን ባቆመባቸው በምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለሕዝቡም ሆነ ለእርዳታ ሠራተኞች አደገኛና ተለዋዋጭ ነው ሲል ገልጿል።
በሶማሌና በአማራ ክልል ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሰዎች እንዲሁም በጋምቤላ ውስጥ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ሁኔታ እንደሚያሳስበው የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድኑ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ድርጅቱ ከሦስት ወራት በፊት ትግራይ ውስጥ ስለተገደሉት ሠራተኞቹ ጉዳይ አስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደም ሆነ ስለግድያው ሁኔታ ምንም ግልጽ ያለ ነገር እንደሌለና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተደረገ ስላለው ምርመራ የሚያደርግውን ክትትል መቀጠሉን ገልጿል።
ኤምኤስኤፍ የባልደረቦቹን ግድያ ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙት ማዕከላዊና ምሥራቃዊ ዞኖች ውስጥ ሲያከናውን የነበረውን እንቅስቃሴ ማቋረጡ ይታወሳል።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ ለ37 ዓመታት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከክልል መስተዳድሮች ጋር በመተባበር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በገለልተኝነትና በሰብአዊነት የህክምና ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን አመልክቷል።
ድርጅቱ የሚሰጠውን ሰብአዊ አገልግሎት ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት ገልጾ ለዚህም የተጣለበት ዕገዳ እንዲነሳና ሥራውን ለመቀጠል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ መሆኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቅርቡ በአገሪቱ ይሰሩ የነበሩ ሦስት የበጎ አድራጎት ተቋማትን ማገዱን መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን ለሦስት ወራት እገዳ እንደተጣለባቸው አስታውቆ ነበር።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሦስቱ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመንግሥት በሰጣቸው ፍቃድ በተለያዩ የሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሶ፤ ኤጀንሲው በሚያደርገው ክትትል መሠረት ድርጅቶቹ ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እግዱ እንደ ተጣለባቸው አመልክቷል።















