እስከ 80 ሺህ ብር የሚከፈልበትና ገበያው እየደራ ያለው የፀጉር ንቅለ ተከላ በኢትዮጵያ

የመላጣ ሰው ጭንቅላት ከጀርባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሃይማኖት ሰይፉ ገና የ25 ዓመት ወጣት ቢሆንም ፀጉሩ እየሸሸ ራሰበራ መሆኑ ምቾት እንደነሳው፤ ብሎም በራስ መተማመኑን ሸርሽሮት እንደነበር ይናገራል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ለራሰበራነት እንደ መፍትሔ መዘውተር የጀመረው የፀጉር ንቅለ ተከላ እፎይታ ይሰጠኝ ይሆናል በሚል ወደ አንድ ክሊኒክ ጎራ ብሏል።

"እናቴ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ፀጉሬ ገና መብቀል ሲጀምር 'ስትወለድ ራሱ ግንባርህ ድረስ ፀጉር አልነበረህም' እያለች ቀልዳብኛለች። በርካታ ትችቶች አሉ" ሲል ሃይማኖት ፀጉሩ ከተመለሰ በኋላ የተሰጡትን አስተያየቶች በቀልድ አዋዝቶ ያስታውሳል።

ንቅለ ተከላውን ማድረግ ካሰበ በኋላ ሕመም ይኖረዋል የሚል ፍርሃት እንደበረው ይናገራል። ነገር ግን አገልግሎቱን የሰጠውን ተቋም ካማከረ በኋላ ፍርሃቱ ተወግዶ ባለፈው ግንቦት ወር ነበር ወረፋ ጠብቆ ቀዶ ሕክምናውን ያደረገው።

"የራሴን ፀጉር ነው ነቅለው ያስቀመጡት። ከንቅለ ተከላው በፊት በርካታ የጤና ምርመራዎች ተደርጎልኛል። ከንቅለ ተከላው በኋላ ክትትሎችን ስላደረኩ ምንም የጎንዮሽ ችግር አላጋጠመኝም" ሲልም ይናገራል።

በአዲስ አበባ ከተማ በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሙያ ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ መሰለ፤ ማርሻ የተሰኘ ግልጋሎቱን የሚሰጥ ክሊኒክ አላቸው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የፀጉር ንቅለ ተከላውን የሚሰጡት ዶክተሩ እርሳቸውም የዚሁ የአገልሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ይህ ንቅለ ተከላ በተለይም ለዕይታ ሲባል የሚሠራ እንደሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የንቅለ ተከላ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

"እኔ መጀመሪያ እዚህ አገር ስመጣ 'እኛ አገር እኮ የኮስሞቲክ ቀዶ ጥገና የሚሠራ አይኖርም' ይሉኝ ነበር። አሁንም ደፍረው የሚናገሩ አሉ። ነገር ግን ሰው ዓይኑ እስካለ ድረስ በቀላሉ የሚስተካከሉ ነገሮችን ይጠቀማል። የፀጉር ንቅለ ተከላም እንደዛ ነው። የመታወቁ እና የአቅም ጉዳይ እንጂ ማንም ሰው ይጠቀማል ብዬ አምናለሁ፤ እሱም እውን ሆኗል" ሲሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ የአገልግሎቱ ፈላጊ ቁጥር መጨመሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ማድረግ ረዥም ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ የሚናገሩት ሐኪሙ "አንድ ፀጉር በምሠራበት ሰዓት አራት ቦርጭ እሠራለሁ" ሲሉ በምሳሌ ያስረዳሉ።

ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች፣ እንደ ስኳር እና ልብ ያሉ ሕመሞች ያሉባቸው ሰዎችን ጨምሮ የተወሰኑ በቅድመ ምርመራ ወቅት በሚለዩ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ለንቅለ ተከላው ብቁ የማይሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

በተለይም ከ20ዎቹ መጀመሪያ እስከ 50ዎቹ ያሉ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው ይላሉ።

ሃይማኖት ሰይፉ

የፎቶው ባለመብት, HAIMANOT

የምስሉ መግለጫ, ሃይማኖት ሰይፉ

እንዲሁም አንድ ሰው የራሱን ፀጉር ብቻ ማስተካከል እንደሚችል እና የሌላ ሰው ጸጉር እንደማይተከል ሐኪሙ ያስረዳሉ።

ትሪቢያን በተሰኘ ክሊኒክ የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም ብሎም የፀጉር ንቅለ ተከላ አማካሪ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ቅድስት የኔነህ፤ የፀጉር ንቅለ ተከላ በሕክምናው ዓለም "አሎፔሺያ" ተብሎ ለሚጠራው የፀጉር መርገፍ ችግር የሚሰጥ ሕክምና ነው ይላሉ።

ይህም ፀጉር በሚረግፍበት እና መመለጥ በሚከሰትበት ጊዜ የሚሠራ ቀላል ቀዶ ሕክምና ሲሆን፤ ቀዶ ሕክምናው በሚካሄድበት አካባቢ ማደንዘዣ ተሰጥቶ የሚከናወን ብሎም የተወሰነ መድማትን የሚያስከትል ነውም ይላሉ።

በወንዶች ላይ የሚከሰተው የፀጉር መርገፍ በተለይም በሆርሞን ጥቃት ምክንያት የሚከሰት መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ቅድስት፤ የጎን እና የኋላ ፀጉር እንደ የፊት ፀጉር ተጠቅቶ እንደማይረግፍ ያክላሉ።

ሕክምናው የሚሰጠውም በዚህ ሆርሞን የማይጎዱ የፀጉር ክፍሎችን በመውሰድ በረገፈው የራስ ቅል ክፍል ላይ በመትከል ነው።

ለንቅለ ተከላው አማካይ ወጪው ስንት ነው?

በመላው ዓለም የፀጉር ንቅለ ተከላ ማካሄድ በኢንሹራንስ የማይሸፈን የውበት ቀዶ ሕክምና ወጪን ይጠይቃል።

ይህም ከ4000 ዶላር (198 ሺህ ብር ) እስከ 15000 ዶላር (743 ሺህ ብር) እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ዶ/ር ቴዎድሮስም ከሰለጠነው ዓለም በመለስተኛ ዋጋ አገልግሎቱን በምትሰጠው ቱርክ አንድ ሰው አገልግሎቱን ከፈለገ እስከ አምስት ሺህ ዶላር ድረስ መክፈል እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ።

በእርግጥ በኢትዮጵያ በሚገኙ ክሊኒኮችም ቀዶ ሕክምናውን የሚያከናውኑ ሐኪሞች ከቱርክ እንደሚመጡ ቢቢሲ ያናገራቸው ክሊኒኮች ገልጸዋል።

ሃይማኖት ቀዶ ሕክምናውን ባደረገበት ወቅት በነበረ ቅናሽ ተጠቅሞ በአጠቃላይ ወደ 70 ሺህ ብር ማውጣቱን ይናገራል። "አቅሙ ኖሮኝ [ፀጉር] በማስተከሌ ደስ ይለኛል። ጓደኞቼም አቅሙ ኖሯቸው ቢያደርጉት ደስ ይላቸዋል" ሲል ይናገራል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ አማካይ ወጪው ከ70 እስከ 80 ሺህ ብር መሆኑን ገልጸው ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋጋም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛው ነው ይላሉ።

ዶ/ር ቴዎድሮስ በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, dr tewodros

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ቴዎድሮስ በሥራ ላይ

ተጓዳኝ ችግሮቹስ?

የፀጉር ንቅለ ተከላ ማካሄድ የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያስከትላል ተብለው ከሚነሱ ነገሮች ውስጥ የፀጉር ወደ ውስጥ መብቀል፣ ስንፈተ ወሲብ፣ መሃንነት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

ዶ/ር ቅድስት ግን እነዚህ የሚወሩት ነገሮች "የሕክምና እውቀት ከማነስ የመጡ ናቸው" በማለት ሕክምናው በሆርሞን ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በቀዶ ሕክምና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም ለቀዶ ሕክምናው ሰዎች ያላቸው ፍርሃት ከእነዚህ መላ ምቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ብሎም ከቀዶ በመጥቀስ፣ ከሕክምናው በፊት በማማከር ሂደት ወቅት ለደንበኞቻቸው በዝርዝር እንደሚያብራሩም ይናገራሉ።

ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ዶ/ር ቅድስት ይጠቅሳሉ።

አንድ ሰው በየወሩ የሕክምና ክትትል እንደሚደረግለት እና የፀጉር እድገቱ እየታየ የተለያዩ ቅባቶች እና የፀጉር ድጋፍ ሰጪ ምግቦች እንደሚሰጠውም ይናገራሉ።

ፀጉር ይሄ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት ከተተከለ በኋላ ደግሞ ይረግፋል ወይ? ስንል ሁለቱንም ባለሞያዎች ጠይቀናል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ "የእኔ እንግዲህ እስካሁን አልረገፈም" ሲሉ በቀልድ ይጀምራሉ።

ፀጉር ከተተከለ በኋላ ረግፎ እንደ አዲስ እንደሚበቅል እና ከዚያ በኋላ የመመለጥ ዕድል አለ ወይም የለም? የሚለውን ግን የሚያሳይ ጥናት እስካሁን እንዳላዩ ይገልጻሉ።

በንቅለ ተከላው የበቀለው ፀጉር በሂደት ከሌላው ፀጉር ተለይቶ እንደማይቀር እና አብሮ እንደሚሸብትም ሐኪሙ ያክላሉ።

ዶ/ር ቅድስት እንደ ካንሰር የመሰሉ ሕመሞች ካሉ ፀጉሩ ሊረግፍ እንደሚችል ይናገራሉ።

የጉበት መጎዳት፣ ኤችአይቪ እንዲሁም የፕሮቲን እጥረት የሚያመጡ ሕመሞች ከተከሰቱ ፀጉሩ ድጋሚ ሊረግፍ እንደሚችል ሐኪሟ ይናገራሉ።

ከእነዚህ ሕመሞች ውጪ ግን ፀጉሩ እንደማንኛውም ፀጉር እያረጀ እንደሚሄድ እና በድጋሚ ራሰራነት እንደማያጋጥም ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የአገልገሎቱ ፍላጎት እንዳለ የሚናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ በዘርፉ የሰው ኃይል ማሰልጠን ከተቻለ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአካባቢው አገራትም ጭምር አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ይናገራሉ።