ሌ/ጄኔራል ይልማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢነትን ከአቶ ግርማ ዋቄ ተረከቡ

ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እና አቶ ግርማ ዋቄ
የምስሉ መግለጫ, ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እና አቶ ግርማ ዋቄ

በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሌተናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸውን አሳወቀ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዣዥ በኢትዮጵያ መንግሥት አማካይነት ከሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ. ም. ጀምሮ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸውን አየር መንገዱ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የአየር መንገዱ የቦርድ ላለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ግርማ ዋቄን ተክተው ነው የአገሪቱ አየር ኃይል አዛዥ የሆኑት ሌተናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ኃላፊነቱን የተረከቡት።

“ሌተናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንኳን ደህና መጡ ለማለት እና መልካም ምኞት ለማስተላለፍ እንወዳለን” ይላል ከድርጅቱ የወጣው መግለጫ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ውስጥ ቁጥር አንድ እና ግዙፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታት ብቃቱን የሚያመለክቱ የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኘ ተቋም ነው።

አየር መንገዱ አገሪቱን በመሩ በተለያዩ አስተዳደሮች ስር በስኬት እያደገ ከአህጉር አልፎ ዓለም አቀፍ ዝናን ለማግኘት የቻለ ተቋም ነው።

የቀድሞው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቆ “ለግሩፑ ስኬታማ አመራር ሰጥተዋል። በአቪየሽን ዘርፍ ያላቸውን ጥልቅ ዕውቀት አካፍለዋል” ሲል መግለጫው ጠቁሟል።

ከዚያ ቀደም የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚነትን እና የአመራር ቦርድ አባልነትን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ተቋሙን እንዳገለገሉ ያተተው መግለጫው፣ “ለአየር መንገድ ግሩፑ እድገት እና ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በግሩፑ ታሪክ ልዩ ስፍራም ይኖራቸዋል” ብሏል።

አቶ ግርማ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 37 ዓመታት ገደማ የሠሩ ሲሆን፣ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እስከሚተኳቸው ድረስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነውም አገልግለዋል።

በአየር መንገዱ ለሰባት ጊዜ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሠርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ከገለጹ በኋላ ነበር የአቶ ግርማ ሹመት ይፋ የተደረገው።

ከአቶ ግርማ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው።

የአየር መንገዱ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ሌተናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሲሆኑ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአየር ኃይሉ ውስጥ የተካሄደውን መልሶ የማደራጀት ሥራ የመሩ ናቸው።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ይህንን የአየር መንገዱን የቦርድ ሰብሳቢነት ሚና ከፍተኛ የገዢው ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ተፈራርቀው ይዘውት ነበር።