ለጄፍሪ ኤፕስታይን ታዳጊ ሴቶችን ስትመለምል የነበረችው ግለሰብ ጥፋተኛ ተባለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታስሮ በነበረበት ክፍል ውስጥ ራሱን ሰቅሎ ሕይወቱ ላለፈው ታዋቂው አሜሪካዊ የፋይናንስ ሰው ጄፍሪ ኤፕስታይን ታዳጊ ሴቶችን በመመልመል እና በማጓጓዝ በግለሰቡ ጥቃት እንዲደርስባቸው ሰርታለች በሚል የተከሰሰችው ጊሌይን ማክስዌል ጥፋተኛ ተባለች።
የ60 ዓመቷ ግለሰብ ቀርበውባት ከነበሩት ስድስት ክሶች በአምስቱ ነው ጥፋተኛ የተባለችው። ጥፋተኛ ከተባለችባቸው ክሶች ውስጥም እድሜያቸው ከ18 በታች በሆኑ ታዳጊዎችን የወሲብ ንግድ ተግባር ውስጥ መሰማራት የሚለው ከባዱ ሲሆን እስከ 40 ዓመት ድረስ ሊያስቀጣ ይችላል።
ይህም ግለሰቧ ቀሪ ሕይወቷን በእስር ልታሳልፍ እንደምትችል ያሳያል። ውሳኔው ትላንት ረቡዕ በተሰጠበት ወቅትም ተከሳሿ ምንም አይነት ስሜታዊ የመሆን ምልክት አላሳየችም።
ውሳኔው አራት ሴቶች ከአውሮፓውያኑ 1994 እስከ 2004 ባለው ጊዜ ውስጥ በኤፕስታይን ጥቃት እንደደረሰባቸው አንድ ወር ያህል በፈጀ የመሰማት ሂደት ምስክርነታቸውን ከሰጡ በኋላ ነው።
ውሳኔው ከተሰጠ በኋላም የጠበቆቿ ቡድን ይግባኝ ለማለት እየተዘጋጁ እንደሆነ እና ደንበኛቸው ጥፋተኛ አይደለችም የሚል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አኒ ፋርመር የተሰኘች በግለሰቧ ላይ ምስክርነቷን የሰጠች ግለሰብ "ዳኞቹ የበዝባዥነት ባሕሪዋን ተረድተው እውቅና በመስጠታቸው ትልቅ እፎይታ እና ደስታ ተሰምቶኛል" ሰትል ተናግራለች።
"ይህ ውሳኔ ሌሎች ይህ ፍትህ ለሚገባቸው ሁሉ መጽናናትን እንደሚሰጥ እና ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።
ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን ወንጀል ለሆነ የወሲባዊ ድርጊት ሲባል ማጓጓዝ እንዲሁም ለማጓጓዝ ማሴር የሚሉት ግለሰቧ ጥፋተኛ ከተባለችባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ እያንዳንዳቸው 10 እና አምስት ዓመት ቅጣትን ያዘሉ ናቸው።
አቃቤ ህግ ዳሚያን ዊሊያምስ ውሳኔው ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን ተጠቂዎቹ ወደ ፊት በመውጣት ያሳዩትን "ጀግንነት" አድንቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, US Attorney's Office SDNY












