ትራምፕ የቀደመ አቋማቸውን በመቀየር የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ እንዲሆኑ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ይዘውት የነበረውን አቋም በመቀየር፤ ሪፐብሊካኖች ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ በማሰማራት የተፈረደበት ጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነዶችን ይፋ እንዲያደርጉ ጠየቁ።
ትራምፕ እሁድ ምሽት 'ትሩዝ ሶሻል' በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ምንም የምንደብቀው ነገር ስለሌለን፤ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላት የኤፕስቲን ሰነዶች እንዲለቀቁ ድምጽ መስጠት አለባቸው" ብለዋል።
ይህ ሰነድ ይፋ እንዳይሆን ላለፉት ቀናት ሲታገሉ የነበሩት ትራምፕ አቋማቸውን የቀየሩት የአገሪቱ ምክር ቤት በዚህ ሳምንት በጉዳዩ ላይ ስብሰባ ሊያካሂድ መሆኑን ተከትሎ ነው። ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባው፤ የአገሪቱ ፍትሕ መስሪያ ቤት ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ወንጀል የተፈረደበት ኤፕስቲንን ሰነዶች ይፋ እንዲያደርግ ለማስገደድ ድምጽ ይሰጣል።
የዚህ ሀሳብ ደጋፊዎች ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው ለማድረግ የሚያስችል ድምጽ ማሰባሰብ ችለዋል። ይሁን እንጂ በቀጣይ ጉዳዩን የሚመለከተው የአገሪቱ ሴኔት በተመሳሳይ መልኩ ሀሳቡን ያጸድቀው እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ዴሞክራቶች እና የተወሰኑ ሪፐብሊካኖች ፍትሕ መስሪያ ቤቱ የኤፕስቲንን ሰነዶች ይፋ እንዲያደርግ የማስገደድ ሀሳብን ሲያቀነቅኑ ቆይተዋል። ትራምፕም ሀሳባቸውን በመቀየር ይህንን ጎራ የተቀላቀሉት በርካታ ሪፐብሊካኖች ከብዙኃን የፓርቲ አባሎቻቸው በተቃራኒ ሊቆሙ እንደሚችሉ ግልጽ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ሰነዶቹ ይፋ እንዲወጡ የሚያስገድደውን ሕግ ካረቀቁት አንዱ የሆኑ የሪፐብሊካን ተወካዩ ቶማስ ማስ እሁድ ዕለት ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ 100 የሚደርሱ ሪፐብሊካኖች ሀሳቡን ደግፈው ድምጽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የኤፕስቲን ሰነዶች ግልጽነት ሕግ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ይህ ረቂቅ፤ የፍትሕ መስሪያ ቤቱ በሚስጥር የተያዙ ቅጂዎችን፣ ሰነዶችን፣ ግንኙነቶችን እንዲሁም ከጄፍሪ ኤፕስቲን ምርመራ ጋር የተያያዙ ግኝቶችን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ያስገድዳል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ገጻቸው ባስተለለፉት መልዕክት፤ "የፍትሕ መስሪያ ቤቱ በ'ኤፕስቲን' ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ገጾችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፤ የተለያዩ ዲሞክራቶች (ቢል ክሊንተን፣ ሬድ ሆፍማን፣ ላሪ ሰመርስ፥ ወዘተ) ከኤፕስቲን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያየን ነው" ብለዋል።
አክለውም፤ "የምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ በሕግ የተፈቀደላቸውን በሙሉ ማግኘት ይችላሉ፤ አይመለከተኝም!" ሲሉም አዲሱን አቋማቸውን አስታውቀዋል።
ትራምፕ በጽሑፋቸው ላይ ክሊንተንን የጠቀሱት የፍትሕ መስሪያ ቤቱ የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ኤፕስቲን፤ ከዋና ዋና ባንኮች እንዲሁም የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተንን ጨምሮ ከበርካታ ስመጥር ዲሞክራቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት እንደሚመረምር በማረጋገጡ ነው።
ትራምፕ አክለውም፤ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ፓም ቦንዲ እና ኤፍቢአይ ኢፕስቲን ከክሊንተን እና ሌሎች ግለሰቦች ጋር የነበውን "ተሳትፎ እና ግንኙነት" እንዲመረምሩ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረው ነበር።
ክሊንተን በበኩላቸው የኤፕስቲን የወንጀል ድርጊቶችን ያውቃሉ መባሉን በጽኑ ተቃውመዋል።
ከኢፕስቲን ጋር ግንኙነት እንዳለው የተጠቀሰው ግዙፉ የአሜሪካ ባንክ 'ጄፒ ሞርጋን ቼዝ' ቃል አቀባይ በበኩላቸው ባንኩ ከግለሰቡ ጋር የነበረውን "ማንኛውም ግንኙነት" በተመለከተ የተሰማቸውን ጸጸት ገልጸዋል። ነገር ግን ቃል አቀባዩ፤ ባንኩ ኤፕስቲን "አሰቃቂ ድርጊቶችን እንዲፈጽም እገዛ እንዳላደረገ" ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤፕስቲን የኢሜል ልውውጦችን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ከተለቀቁ ሰነዶች ውስጥ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጠቀሱባቸው ነበሩ።
ዴሞክራቶች ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመሸሽ እየሞከሩ እንደሆነ በመግለጽ ይከስሳሉ።
ዎል ስትሪት ጆርናል ያደረገው ዳሰሳ እንደሚያመለክተው ይፋ በሆኑት 2,324 የኢሜይል ልውውጦች ላይ የትራምፕ ስም 1,600 ጊዜ ተጠቅሶ ተገኝቷል።















