የደቡብ አፍሪካው ኦፕሬሽን ዱዱላ፡ “የውጭ ሃገር ዜጎችን የምንጠላበት ምክንያት”

የደቡብ ኦፕሬሽን ዱዱላ የተሰኘ የወጣቶች ቡድን የሌላ ሃገር ዜግነት ያላቸውን ሰዎችን የንግድ ሥፍራዎችን በማውደምና ሰቆች እንዲዘጉ በማድረግ ታዋቂ ሆኗል።
ቢቢሲ አፍሪካ ወደዚህ የፀረ-ስደተኛ ቡድን ዘልቆ በመግባት መመልከት ችሏል።

ዲማካፆ ማኮየና፤ ምስራቅ ጆሃንስበርግ በምትገኘው ክዋ ቴማ በሚገኝ አንድ የትምህርት ቤት ኩችና ሳንድዊች እየጠባበሰች ነው።
ሶስት ልጆች ብቻዋን የምታሳድገው የ57 ዓመቷ ዲማካፆ ለ10 ዓመታት ያክል ምግብ አብሳይ ሆኖ ሠርታለች።
“እውነቱን ለመናገር የሌላ ሃገር ዜጎችን እጠላለሁ። ጓዛቸውን ሸክፈው ሃገራችንን ጥለው ቢወጡ ምን ያክል ደስ ባለኝ” ትላለች እንባዋን እየታገለች።
ጥላቻዋ ምን ያክል ለመረዳት ቢከብድ ዲማካፆ ስልኳን አውጥታ የልጇን ፎቶ አሳየችን። መላው አካሉ በእሳት ተቃጥሎ ይታያል።
“አደገኛ ዕፅ መጠቀም የጀመረው ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው” ትላለች።
ልጇ ይህን አመሉን ለማስታገስ በሚል ወደ ስርቆት ተሰማራ። አንድ ቀን የኤሌክትሪክ ገመድ ሰርቆ ሊሮጥ ሲል ኤሌክትሪክ ይዞት ተቃጠለ።
ልጇ ክሪስታል ሜዝ እና ኒያዎፔ የተባለ እጅግ ኃይለኛ በሱስ የሚዘፍቅ፤ ደቡብ አፍሪካን እያመሳት ያለ ዕፅ ይጠቀማል።
እናቱ የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው ይህን ዕፅ እያመጡ በመሸጥ ልጄን ለዚህ የዳረጉት ስትል ወቀሳዋን ታሰማለች፤ ለዚህም ነው የኦፕሬሽን ዱዱላ አባል የሆነችው።
“ዱዱላ ማለት ወደፊት እንድራመድ እያደረገኝ ያለ እንቅስቃሴ ነው” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
ኦፕሬሽን ዱዱላ ከሁለት ዓመት በፊት በሶዌቶ የተቋቋመ ቡድን ነው። ምንም እንኳ የውጭ ሃገራት ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተለመደ ቢሆንም ይህ ቡድን በይፋ ተቋቁሞ መሰል ተግባር በመፈፀም የመጀመሪያው ሆኗል።
ራሱን የሲቪክ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ፀረ-ስደተኛ ቡድን ዱዱላ ስሙን ከዙሉ ቋንቋ የወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “በግድ ማስወጣት” ማለት ነው።
የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዝደንት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ መናገሻ የሆነችው ሶዌቶ የፀረ-አፓርታይድ ንቅናቄ መለዮ ነበረች።
አሁን ከተማዋ በሃገሪቱ እውቅና እያገኘች ያለችው የፀረ-ስደተኛ ቡድን መናኸሪያ በመሆን ነው።
እኩል የሆነ ማሕበረሰብ መፍጠር አልቻለችም በምትባለው ደቡብ አፍሪካ ከሶስት የሃገሪቱ ዜጎች አንዱ ሥራ አጥ ነው። ይህ ደግሞ የውጭ ሃገራት ዜጎች ቀላል ዒላማ እንዲሆኑ አድርጓል።
በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ የሚገኘው የደኅንነት ጥናት ተቋም [አይኤስኤስ] በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው ሪፖርት መሠረት በደቡብ አፍሪካ 3.9 ሚሊዮን ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን ይህ ከጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር 6.5 በመቶ የሚሆን ነው።
ይህ ቁጥር ሁሉንም ስደተኞች ማለትም ሕጋዊ መኖሪያ ያላቸውንም ሆነ ከየት እንደመጡ የማይታወቁትን ሳይለይ የተሠራ ነው።
የውጭ ዜጎች ጠል [ዚኖፎቢክ] የሆኑ ንግግሮች ከፖለቲኞች፣ ከባለሥልጣናት እና ከፀረ-ስደተኛ ቡድኖች አፍ ሲወጡ ይሰማሉ። ይህ ደግሞ ሃገሪቱ በውጭ ሃገር ዜጎች እየታመሰች ነው የሚል ያልተጣራ መረጃ እንዲንሰራፋ አድርጓል።
የደቡብ አፍሪካ ሶሻል አቲትዩድስ ሰርቬይ በ2021 በሠራው ጥናት ግማሽ ያክል ደቡብ አፍሪካዊያን ከ17 እስከ 40 ሚሊዮን ስደተኞች ሃገራቸው እንደሚኖሩ ያምናሉ ብሏል።
በቅርቡ እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአንድ ወቅት በማንዴላ ይመራ የነበረው ገዢው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ተቀባይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ50 በመቶ በታች ሊወርድ ይችላል።
ኦፕሬሽን ዱዱላ ይህን ክፍተት ተጠቅሞ ከክልላዊ የፀረ-ስደተኞች ቡድን ወደ ብሔራዊ ፓርቲ በመሸጋገር በሚቀጥለው ዓመት ሃገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ አልሟል።

ዛንዲሌ ዳቡላ ባለፈው ሰኔ የኦፕሬሽን ዱዱላ ፕሬዝደንት ሆና ተመርጣለች። የቡድኑን መልዕክት አንግባ “የውጭ ዜጎች” ለደቡብ አፍሪካዊያን መከራ ተጠያቂዎች ናቸው ትላለች።
ዘመቻው ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ነው የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላት ዛንዲሌ “ካለብን ችግር አብዛኛው በውጭ ሃገራት ዜጎች የመጣ መሆኑን ልንክድ አይገባም” ትላለች።
“ሃገራችን ቀውስ ውስጥ ናት። የውጭ ዜጎች ደቡብ አፍሪካን በ20 ዓመት ውስጥ የራሳቸው ለማድረግ እየሠሩ ነው።”
የ20 ዓመት ዕቅድ ያለችው ከየት የመጣ እንደሆነ በጥብቅ የተጠየቀችው ፕሬዝደንቷ የሚናፈስ ወሬ ቢሆንም እሷ ግን እውነት ነው ብላ እንደምታምን ትናገራለች።
“አደገኛ ዕፅ በየቦታው ታያለህ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የዕፁ ሱሰኞ ደቡብ አፍሪካዊያን እንጂ የውጭ ዜጎች አይደሉም። ምንድነው እየሆነ ያለው? እህት ወንድሞቻችን በክለው እነሱ ሃገሪቱን መቆጣጠር ቀላል እንዲሆንላቸው?” ትላለች።

ይህ ግልፍት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕጋዊ መንገድ መጥተው በሕጋዊ ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ የውጭ ሃገራት ዜጎችም ስጋት ሆኗል።
በያዝነው የአውሮፓዊያኑ ዓመት መባቻ የኦፕሬሽን ዱዱላ ጥቃት ሰለባ የነበረ አንድ ናይጄሪያዊ ሁለት ሴቶች መጥተው ጥቃት ካደረሰቡት በኋላ ልብሶቹን ወርውረው እንደሄዱ ለቢቢሲ ይናገራል።
“ወደ ናይጄሪያ ተመለስ። እኛ ኦፕሬሽን ዱዱላ ነን። እኛ ደቡብ አፍሪካዊያን ነን” ብለውት እንደሄዱ ያስታውሳል።
አሁን ምንም ነገር የለውም። መንገድ ላይ ለመተኛት እንደተገደደ የሚናገረው ናይጄሪያዊው ግለሰብ “እኔ ድምፅ እሰጣለሁ። የሃገሪቱ ዜጋ ነኝ። እንዲህ ሰዎችን የምታደርግ ሃገር አይቼ አላውቅም። ሕገ-ወጥ ነገር አድርጌ ከሆነ ይሁን። አስወጡኝ። ነገር ግን ምንም ሕገ-ወጥ የሆነ ድርጊት አልፈፀምኩም። አሁን ሕይወቴ ተዘበራርቋል። ኪራይ መክፈል አልችልም። መሄድ እሻለሁ” ይላል።
ኦፕሬሽንድ ዱዱላ ትልቁ ስጋቱ ወደ ሃገሪቱ እየገባ ያለው ዕፅ እንደሆነ በማስረፅ በጣም ዝቅተኛ ኑሮ ወደሚመሩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተሰራጨ ነው ይላሉ።
ነገር ግን ዕፅ የሚሸጡት ሰዎች ደቡብ አፍሪካዊያን ስላለመሆናቸው የሚያሳይ መረጃ የለም።
ምንም እንኳ ዕፅና ወንጀልን በተመለከተ ጠብሰቅ ያለ መረጃ ባይኖርም አይኤስኤስ የፍትሕ ሚኒስትሩን ዋቢ አድርጎ በጠቅላላው ከዕፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ከተፈረደባቸው ሰዎች መካከል በ2019 8.5 በመቶ፤ በ2020 ደግሞ 7.1 በመቶ ስደተኞች ናቸው ይላል።
ተቋሙ አክሎ በየዓመቱ እሥር ቤት ከሚገቡ ሰዎች መካከል 2.3 በመቶው ወረቀት የሌላቸው የውጭ ሃገራት ዜጎች ናቸው ይላል።
ቢቢሲ ወደ ምስራቅ ሶዌቶ አቅንቶ ዱዱላ ግብረ-ኃይል የተሰኘውን ቡድን ተቀላቅሏል። ሰብሰብ ያሉ ወንዶች አንድ ኪራይ አልከፈለም ያሉትን ሞዛምቢካዊ ለመጋፈጥ በመኪና እየሄዱ ነው።
መጀመሪያ በድርድር ለመፍታት የታሰበው ጉዳይ ወደ ግርግር አመራ። ይህ የሆነው ማንድላ ሌንኮሲ የተባለ ግለሰብ ሞዛምቢካዊውን ለመደብደብ ሲነሳ ነው።
ቢቢሲ ስለግልፍተኛ ባሕሪያቸው ሲጠይቃቸው “እኛ ሕግ እያስከበርን ነው” ይላሉ።
ሥራ አጡ ማንድላ ሌንኮሲ ወደ መኖሪያ ሥፍራዎችና ወደ ንግድ ሥፍራዎች በማቅናት ዕፅ ይሸጣሉ አሊያም ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የቆዩ ስደተኞችን መጋፈጥ የቀን ተቀን ሥራው ሆኗል።
ጓደኛው ሴድሪክ ስቶንም የዱዱላ ደጋፊ ነው። “ደቡብ አፍሪካ ወደ ቀድሞዋ ወደ ምናውቃት ደቡብ አፍሪካ ልትመለስ ይገባል” ይላል።
“እኒህ ሱቆች የአባቶቻችን ነበሩ። ዛሬ ግን ሁሉም ሱቆች በስደተኞ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን፣ በባንግላዴሺዎች እና በሶማሊዎች ተይዘዋል። ለምን?”
ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፖሳ ፀረ-ስደተኞ የሆኑ ንቅናቄዎችን ያወገዙ ሲሆን መሰል ቡድኖች የሚያደርሱትን ጥቃትም ተቃውመዋል።
በ2019 ብሔራዊ ዘረኝነትና ዚኖፎቢያን የሚከታተል ብሔራዊ ምክር ቤት ቢያቋቁሙም በርካቶች መንግሥት ከዚህ የበለጠ እንዲያደርግ ይሻሉ።
ይህን በደቡብ አፍሪካ በስፋት እየተሰራጨ የመጣውን ፀረ-ስደተኛ ንቅናቄ ለመግታት የተለያዩ ድርጅቶች ዘመቻ ጀምረዋል።
ነገር ግን የኦፕሬሽን ዱዱላ አባላት መንገዱን ሞልተው እየዘፈኑ ማለፋቸውን ቀጥለዋል። “የውጭውን ዜጋ አቃጥለው። እኛ ወደ ጋራዥ እንገባለን። ነዳጅ ገዝተን የውጭውን ዜጋ እናቃጥለዋለን” እያሉ።












