በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት በውሃ ጥም የሚሰቃዩት የደቡብ አፍሪካ ከተሞች

ውሃችንን ስጡን የሚል ፖስተር የያዘች ሴት

በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ አቅራቢያ ለወትሮው ፀጥታ የሰፈነባቸው የከተማ ዳርቻ ሰፈሮች በቁፋሮ መሳሪያ ድምጽ ሰላማቸው እየደፈረሰ ነው።

የመሬት መሰርሰሩ የሚካሄደው አዲስ የማዕድን ሃብት ፍለጋ አይደለም። ሠራተኞች ቁፋሮውን የሚያካሂዱት በጣም ውድ የሆነውን ውሃ ለማግኘት ነው።

በአገሪቷ የኢኮኖሚ እምብር ውስጥ በሚገኙ የሃብታም መኖሪያዎች ሳይቀር ቧንቧዎች እየደረቁ በመሆናቸው የግል የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ነው።

በአካባቢው የቤት ባለቤት የሆኑ አንድ ግለሰብ “ውሃ መቼ እንምትመጣ እና መቼ እንደማትኖር አለማወቃችን አሰልችቶኛል” ይላሉ።

በመሆኑም “የግላችንን የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈር በመንግሥት ላይ በጣም ጥገኛ እንዳንሆን ያደርጋል። ለቤተሰቤ የሚጠቅመውም ይህ ነው” ብለዋል።

በአካባቢው ያለው የውሃ አቅርቦት በአብዛኛው ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር የተሳሰረ ነው።

ውሃውን ከምንጩ ከፍታ ቦታ ላይ ወደሚገኙት ጆሃንስበርግ እና ፕሪቶሪያ ከተሞች በግፊት [ፓምፕ] ለመሳብ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም የግድ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ አፍሪካ የታየው ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር በውሃ አቅርቦትም ላይ እክል ፈጥሯል።

ባለቤትነቱ የመንግሥት በሆነው እና ከአገሪቷ ዋነኛ ውሃ አቅራቢዎች አንዱ በሆነው ራንድዎተር ኃላፊ የሆኑት ሲፎ ሞሳይ፣ “ሁሉም የውሃ ጣቢያዎቻችን የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋሉ። በተፈለገበት ቦታ ውሃ ለማድረስ በፓምፕ መሳብ ይጠበቅብናል” በማለት የውሃ አቅርቦት ችግሩ የኤሌክትሪክ መሆኑን አስረድተዋል።

“ኤሌክትሪክ ለምንሰራው ሥራ የልብ ትርታ ነው፤ ስለዚህ ኤሌክትሪክ ከሌለ ችግር ነው” ሲሉም አክለዋል ኃላፊው።

የ35 ዓመቱ የአካባቢው ነዋሪ ዚዚ ድላንጋ ለተከታታይ ቀናት የውሃ እና የመብራት መቋረጥ ሕይወታቸውን ፈታኝ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ።

በጆሃንስበርግ ሰሜናዊ አካባቢ የምትኖር አንድ ግለሰብም ውሃ ሲመጣ ለማጠራቀም እንደተገደደች እና ገላዋን ለመታጠብ ወደ ጂምናዚየም እንደምትሄድ ተናግራለች።

“ውሃ ባይኖርም የምከፍለው የውሃ ክፍያ ግን ተመሳሳይ ነው። ይህም በጣም ያበሳጨኛል። ሌላ ውሃ የማገኝበት አማራጭም የለኝም” ብላለች።

በደቡብ አፍሪካ በሃብታም ሰፈሮች የውሃ ቁፋሮ ሲደረግ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በደቡብ አፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የቧንቧ ውሃ ቤታቸው ሳይገባላቸው ዓመታትን አሳልፈዋል።

አሁን እያጋጠመ ያለው የውሃ አቅርቦት ችግርም በውሃ ኢንደስትሪው ዘንድ ያጋጠመው ዘርፈ ብዙ ችግር አንዱ ገጽታ ነው።

የውሃ ባለሙያው ፕሮፌሰር አንቶኒ ተርቶን “የሥርዓት ውድቀት ውስጥ ነው ያለነው። የውሃ ዘርፉ እየፈራረሰ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ችግር ያጋጠመው በጥሩ ሁኔታ ባልተሰሩ መሠረተ ልማቶች ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፣"ይህም ለፍሳሽ ችግር እና የውሃ አቅርቦት እጦት ሰበብ ሆኗል” ብለዋል።

በእያንዳንዱ ቀን በውሃ ሥርዓቱ ላይ ባለው ችግር ምክንያት በሚያጋጥም ብክነት ሰባት ሚሊዮን ሊትር የታከመ፣ ንጹህ እና የሚጠጣ ውሃ ይባክናል።

አብዛኛው የውሃ ብክነት የሚፈጠረውም ከተሞች ጥገና ስለማይሰሩ፣ በሙስና እና በስርቆት ምክንያት ነው።

የውሃ እጥረቱ እና እንዲሁም ብክለቱ የሕብረተሰብ ጤና ቀውስም አስከትሏል።

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፕሪቶሪያ ውጪ በምትገኝ ሃማንስክራለ ከተማ በኮሌራ ሳቢያ 29 ሰዎች ሞተዋል።

ወረርሽኙ ከደረጃ በታች የሆነ ውሃ የማጣራት ልምድ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተነግሯል።

ይህም የታሸገ ውሃን ገበያ አድርቷል።

በቅርቡ የታሸገ ውሃ የመንገድ ላይ ንግድን የተቀላቀለው ሎረንስ ማሎፕ “ብዙ ሰዎች ውሃ ይገዙኛል። ምክንያቱም መጠጣት የሚፈልጉት ንጹህ ውሃ ነው። ከቧንቧ የሚወጣው ቆሻሻ ነው” ይላል።

እርሱ ግን ቤት ውስጥ የዝናብ ውሃን በመሰብሰብ እና ከመጠቀማቸው በፊት በማፍላት ይጠቀማል።

ማሎፕ ከቧንቧ በሚወጣው ቆሻሻ ውሃ ምክንያት በርካታ ሰዎች እየታመሙ መሆኑንም ገልጿል።

“አንዳንዶቹ እንዴት ውሃውን ማከም እንዳለባቸው አያውቁም።በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ሕጻናት ልጆች አሉ በእውነቱ ከሆነ ደኅንነታችን ያሰጋኛል።” ብሏል።

ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር የሃማንስከራል ከተማ ብቻ አይደለም።

በቅርቡ ከውሃ ጉዳዮች እና ከንጽሕና መሥሪያ ቤት የወጣ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ለውሃ ህክምና ሥርዓት ከተወሰዱ 155 ናሙናዎች ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት የውሃ ጥራት ችግር ታይቶባቸዋል። በመሆኑም ችግሩ በመላ አገሪቷ ሊስተዋል ይችላል።

ይህን የውሃ ችግር ለመፍታት ያለው አንደኛው አማራጭ የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈር ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም የሚቻል አይደለም። ምክንያቱም ቢያንስ 7 ሺህ ዶላር ይጠይቃል።

ዋተርካን የተባለው አዲቮኬሲ ቡድን የሚሰሩት ዶ/ር ፌሪያል አዳም “ይህ በሃብታሞች እና በድሃዎች መካከል ያለውን ክፍተት ያሰፋል፤ ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ይፈጥራል” ሲሉ ሌላ አማራጮች መኖር እንዳለባቸው ተከራክረዋል።

የአገሪቷ መንግሥት በበኩሉ ችግሩ መፈጠሩን አምኖ፣ አንዳንድ የማዘጋጃ ቤት ባለሥልጣናትን በግድየለሽነት ክስ ፍርድ ቤት አቅርቤያለሁ ብሏል።

ዶ/ር አዳም ግን ይህ በቂ አይደለም ብለዋል። “እንዲህ አይነት ነገሮች ለውጥ አላመጡም። ይህም ሕይወትን አደጋ ላይ ጥሏል” ሲሉ ሌሎች መፍትሔዎች እንዲሰጡ ጠይቀዋል።