በደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ መድረክ ነውጥን በመፍጠር የሚወቀሰው ጁሊየስ ማሌማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጁሊየስ ማሌማ ምንም እንኳ በትምህርቱ ደካማ የነበረ ቢሆንም፣ በከፋፋይ አጀንዳው ቢታማም፣ የደቡብ አፍሪካ ሁለተኛው ግዙፍ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በርካታ ደጋፊዎች አፍርቷል።
ማሌማ ይህን ፓርቲ ያቋቋመው ከምንም ተነስቶ ነው። ግራ ዘመሙ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) በ10 ዓመት ውስጥ ገዝፎ እዚህ ደርሷል።
በዚህ ጊዜ ማሌማ ከዩኒቨርሲቲ በኮሚዩኒኬሽንስ እና በአፍሪካ ቋንቋዎች በዲግሪ ተመርቋል። በፍልስፍና ደግሞ የክብር ዲግሪ አግኝቷል።
የ42 ዓመቱ ፖለቲከኛ ትልቅ ስም ባለው ዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪውን ለመሥራት ተመዝግቧል።
ብዙዎች ማሌማ ለዚህ ይበቃል ብለው አልገመቱም። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ያመጣው ውጤት ሾልኮ ወጥቶ ትምህርት ያልዘለቀው እንደነበር አሳብቋል።
አወዛጋቢው እና ተናጋሪው ፖለቲከኛ ጥላችን በመስበክ ይወቀሳል፣ በሒሳብ ዕውቀቱ እና በእጅ ሥራ ትምህርት ውጤቱ መዘባበቻ ሆኗል።
ነገር ግን በዚህ ሳይገታ ትምህርቱን አጠናቋል፤ ምክንያቱም “አናጢ ሳይሆን ማኅበረሰብ አንቂ አሊያም ፖለቲከኛ የመሆን ነው ሕልም” ስላለው።
ተማሪ ሳለ ኮሳስ ወይም ኮንግረስ ኦፍ ሳው አፍሪካን ስቱደንትስ የተባለው በአፓርታይድ ጊዜ ዘረኝነትን የሚቃወመውን ንቅናቄ ተቀላቅሎ ነበር።
በወቅቱ ሁለት ጊዜ የሁለተኛ ደረጃን ማጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ ሁለት ጊዜ ከክፍሉ መውደቁን ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ “ኮሳስን ስቀላቀል እጅግ በጣም ደስተኛ ሆኜ ትምርህቴን ረሳሁ” ነው።
በፈረንጆቹ 1994 አናሳው የነጮች አገዛዝ ተገረሰሰ። አፓርታይድን በመቃወም ከፊት የነበረው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ነበር። ፓርቲው የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያውን ዴሞክራቲክ ምርጫ አሸነፈ።
እነሆ ማሌማ ዘንድሮ የወቅታዊ ዜናዎች መሪ ነው። ምንም እንኳ ማሌማ ነው ያነቃቃን ባይሉም በርካታ ቁጥር ያላቸው ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች ትምህርት መጨረስ እንዳለባቸው ያውቃሉ።
“በትምህርት እና በትምህርት ብቻ ነው የጥቁር ኩራትን መልሰን ማግኘት የምንችለው” ሲል ማሌማ በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።
በሐምሌ ወር መባቻ ማሌም ለደጋፊዎቹ ንግግር ሲያደርግ ወደፊት ፓርቲውንም ሆነ አገር መምራት የሚሹ ከሆነ ቢያንስ የማትሪክ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል ብሎ ነበር።
“መቼም ከኤኤንሲ የባስን ልንሆን አይገባም. . . ኢኤፍኤፍን ወይም አገሪቱን መምራት የምትፈልጉ ከሆነ ወደ ትምህርት ቤት ሂዱ።”
ከደቡብ አፍሪካ ወጣቶች 51 በመቶው ያህሉ ሥራ አጥ ናቸው። ከእነዚህ መካከል በተለይ ተመርቀው ሥራ ያላገኙት ያጋጠማቸውን ሁሉ ዕድል ከመጠቀም ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።
በማሌማ ደጋፊዎች ምክንያት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተበጥብጧል፤ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሊያካሂዱ ያቀዱት ንግግር ተቋርጧል።
እርግጥ ነው በርካታ ሰዎች ማሌማ በሚያራምደው የፖለቲካ አካሄድ አይስማሙም። ነገር ግን ሰውዬውን ያከብሩታል።
“በ2024 ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ እሰጣለሁ። ምንም እንኳ ኢኤፍኤፍ ለወጣቶች አንዱ አማራጭ ቢሆንም ፓርቲው በፓርላማ የሚያራምደውን በጥባጭ አካሄድ አልደግፍም” ይላል የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ሲያቦንጋ።
ኢኤፍኤፍ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሥልጣን ሚዛን ጨብጧል፤ ጥምር መንግሥት መሥርቷል፤ አፍርሷልም።
ታድያ ይህ አካሄድ ማሌማ ልክ እንደሌሎቹ ፖለቲከኞች ዋናው ማነቆ የሆነውን የዜጎችን ችግር ከመፍታት ይልቅ ፖለቲካዊ ጨዋታ ላይ አተኩሯል ብለው እንዲወቅሱት አድርጓል።
አንዳንድ ተንታኞች ይህ የማሌማ እንቅስቃሴ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የደቡብ አፍሪካ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ሊያሳጣው ይችላል ይላሉ።
በቅርቡ የተሰበሰበ አንድ ድምፅ የማሌማ ፓርቲ 13 በመቶ ድጋፍ አለው ይላል። በ2019 በተሰበሰበው ድምፅ የፓርቲው ድጋፍ 11 በመቶ ነበር። ይህ ማለት የማሌማ ፓርቲ አሁን ሦስተኛው ተመራጭ ነው።
በተደጋጋሚ የጥላቻ ንግግር በማድረግ የሚወቀሰው ማሌማ በሁለት መዝሙሮች ምክንያት በሲቪል መብት ማኅበራት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
አንደኛው መዝሙር ‘ሹት ዘ ቦር’ አሊያም በግርድፍ ትርጉሙ ‘ገበሬውን በለው’ ይላል። በዚህ አግባብ ‘ገበሬው’ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ለመግለፅ የገባ ነው።
ሌላኛው መዝሙር ‘ኮል ዘ ፋይር ብሪጌድ’ የተሰኘ ሲሆን እኒህ ሙዚቃዎች ጥላቻን የሚሰብኩ እና መገለልን የሚያነሳሱ ናቸው የሚል ወቀሳ ይደርስባቸዋል።
በሌላ በኩል የኤኤንሲ ድጋፍ ከ27 በመቶ ወደ 50 ዝቅ ብሏል። ምናልባት በሚቀጥለው ምርጫ ጥምር መንግሥት ሊቋቋም እንደሚችል ጠቋሚ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ማሌማ በአንድ ወቅት የኤኤንሲ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ መሪ ነበር። ጃኮብ ዙማ ወደ ሥልጣን እንዲወጡ አስተዋፅዖ ቢያደርግም ሁለቱ ሰዎች ባለመስማማታቸው ማሌማ ከፓርቲው ተወገደ።
የኢኤፍኤፍ መሪ ሆኖ በለተይ የቀድሞው ፕሬዝደንት የመንግሥት ገንዘብ ተጠቅመው የግል መኖሪያቸውን አድሰዋል በሚል ከተከሰሱ በኋላ ፀረ-ዙማ ዘመቻ በማካሄድ ቀንደኛው ነበር።
ብዙዎቹ ማሌማ በፈረንጆቹ 2012 ከፓርቲው ሲወገድ የፖለቲካ ሕይወቱ አበቃለት ብለው ነበር። ነገር ግን በዚያኑ ዓመት የተሻለ ክፍያ ለመጠየቅ ተቃውሞ የወጡ 34 ማዕድን ቆፋሪዎች በፖሊስ መገደላቸውን ተከትሎ ኢኤፍኤፍ ተወለደ።
ማሌማ ወዲያው ወደ ማዕድን ቆፋሪዎች ሄዶ ጉብኝት በማድረግ ራሱን የሠርቶ አደሩ ተወካይ አድርጎ ቀረበ።
እነሆ ኢኤፍኤፍ 10ኛ ዓመቱን ሲደፍን ወደ ሥፍራው ሄዶ ጉብኝት በማድረግ የፓርቲውን የምሥረታ በዓል አክብሯል።
የማሌማ ፓርቲ “ቅድመ አያቶችን ለማስደሰት” በሚል በክብረ-በዓሉ 15 ላሞች አርዷል፤ ባሕላዊ የገብስ መጠጥ ጠምቋል።
“ፓርቲያችን የተወለደው እዚህ መሬት ላይ የሠራተኞች ደም የፈሰሰ ዕለት ነው” ሲል ማሌማ በሥፍራው ለተሰበሰቡ በሺህ ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ተናግሯል።
የኢኤፍኤፍ ጠቅላይ አዛዥ በሚል መጠሪያው የሚታወቀው ማሌማ፤ ደቡብ አፍሪካ ነፃ ከወጣች ሦስት አሥርታት ቢሆናትም ጥቁሮች ሊያሳኩት ያልቻሉትን “የምጣኔ ሃብት ነፃነት” ለማምጣት ቃል ገብቷል።
ነገር ግን የማሌማ ተቺዎች የሰውየው ፖሊሲዎች በተለይ ደግሞ ንብረት መውረስ የሚለው ሐሳብ የምጣኔ ሃብት ነፃነት ሳይሆን አደጋን ያመጣል ይላሉ።
በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ጠቅላላይ ምርጫ ደቡብ አፍሪካውያን በነቂስ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለጊዜው ማሌማ የፓርቲውን 10ኛ ዓመት በማክበር፤ ከደጋፊዎቹ ጋር በመጨፈር እያሳለፈ ይገኛል።












