በደቡብ አፍሪካ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እየጨመረ ነው፡ የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሚፈጸመው መጤ ጠል ጥቃት እየጨመረ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች አስጠነቀቁ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች እንዳሉት ይህ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እና መድልዎ እንዲጨምር በተለያዩ ወገኖች የሚያካሂደው መጤ ጠል ዘመቻን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በተለይም ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ጥቃቶች በመምራት ስሙ እየጎላ የመጣው ‘ዘመቻ ዱዱላ’ የተባለው እንቅስቃሴ ቀዳሚው ምክንያት ነው ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማትን በእሳት የማውደምና ግድያዎች እንዲፈጸሙ አድርጓል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ ለመጣው መጤ ጠል እንቅስቃሴ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳ ዋነኛ አጀንዳ በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጣረ መሆኑ ችግሩን እያባባሰው ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ለዚህም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በውጭ ዜጎች ላይ የሚነዙት የጥላቻ ንግግር ጥቃቶቹ እንዲበረክቱ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የውጭ ዜጎች ላይ የተነጣጠሩትን መጤ ጠል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የአገሪቱ መንግሥት ጥቃቱን በሚቀሰቅሱና በሚያበረታቱ ላይ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በዋነኝነት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ፀረ የውጭ ዜጎች እንቅስቃሴ የሚያደርገው ‘ኦፕሬሸን ዱዱላ’ የተባለው ቡድን የሚንቀሳቀሰው ጆሃንስበርግ ውስጥ ነው።
ቡድኑ በ33 ዓመቱ ናህላንሃላ ዴላሚኒ የተመሰረተ ሲሆን የበለጠ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሶዌቶ ነዋሪዎች ስደተኞችን “ጠራርገን እናስወጣቸው” የሚል ዘመቻ በጀመሩበት ወቅት ነበር።
የዚህ ቡድን አባላት አሁን በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ እና በውጭ አገራት ዜጎች የተያዙ ንግዶች ተዘግተው አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋሉ። በዚህም የአገሪቱ ዜጎች የንግድ ሥራዎቹ ባለቤት የመሆንና ተቀጥረው የመሥራት ዕድል ያገኛሉ ብለው ያስባሉ።
በአሁኑ ወቅት የተባባሰው እና በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ዘንድ የተፈጠረው ስጋት አዲስ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል።
በ2008 (እኤአ) በመላ አገሪቱ በስደተኞች ላይ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ በዚህም ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በ2015 እንዲሁ በደርባን እና በጆሃንስበርግ ከተሞች በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ መንግሥት ወታደሮቹን ለማሰማራት ተገዶ ነበር።
ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ ሌላ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የጥላቻ ጥቃቶችን አጥብቀው በማውገዝ ሥርዓት እንደሚያሰፍኑ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ አደገኛው ጥቃት ጊዜ እየጠበቀ በማገርሸት የውጭ ዜጎችን ንብረትና ሕይወት አደጋ ላይ እየጣለ ነው።












