ዱዱላ፡ የውጪ አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠረው የደቡብ አፍሪካውያን አመጽ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጆሃንስበርግ አሌክሳንድራ ነዋሪዎች እና በጎዳና ንግድ ላይ በተሰማሩ የውጪ አገር ዜጎች መካከል ጠብ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
የአሌክሳንድራ ነዋሪዎች ምንም እንኳ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ቢመሩም በቅርብ ርቀት ተንጠራርተው የሰማይን ሆድ የሚስሙ የአገሩቷን ሕንጻዎች ይመለከታሉ።
የሳንድቶን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች፣ በአህጉሪቷ ካሉ የንግድ ከተሞች ሁሉ ቀዳሚ ናቸው። እነዚህ ለአሌክሳንድራ ምንዱባን በቅርብ ኪሎ ሜትር የሚገኙ ሕንጻዎች ሁሌም የኑሯቸውን ጥቀርሻ ማንፀሪያዎቻቸው ናቸው።
እነርሱ ማጣት እጅ አግራችን አስሮታል ብለው ሲያማርሩ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በእግር በፈረስ አቆራርጠው ደቡብ አፍሪካ የገቡ ደግሞ ከበረከቱ ተካፋይ ሆነዋል።
ይህ ታድያ ሁለት አወዛጋቢ ቡድኖች እንዲመሰረቱ ምክንያት ሆኗል።
ዘ አሌክሳንድራ ዱዱላ ሙቭመንት እና ኦፕሬሽን ዱዱላ
እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች ሰነድ አልባ የሆኑ መጤ ሕዝቦችን ከደቡብ አፍሪካ ይውጡልን ሲሉ የሚቀሰቅሱ ሲሆን ድሮም ሆድ የባሳቸው እና ከአገሪቱ የምጣኔ ኃብት ማዕድ ተገልለናል በሚሉ የአገሪቱ ምንዱባን ዘንድ ድጋፍን አስገኝቶላቸዋል።
እነዚህ ቡድኖች የሚፈልጉት ምንድን ነው?
በአገሪቱ ዜጎች እና በሰነድ አልባ ስደተኞች መካከል ለሚፈጠረው ውጥረት ሁሌም ድህነት ማጠንጠኛው ነው። የነገር ውሉ ሲፈታ ትክክልም ይሁን አይሁን የእነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን ቅሬታ ለችግሮቻችን ሁሉ ምክንያቶቹ እነዚህ ሰነድ አልባ ስደተኞች ናቸው የሚል ነው።
ዱዱላ በዙሉ ቋንቋ ወዙ ተመጥጦ ይተርጎም ከተባለ "አስወጧቸው" ወይንም "ይሂዱልን" ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቡድኖቹ ምን እንደሚፈልጉ ፍንጭ ይሰጣል።
ምንም እንኳ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የተለያዩ ቢሆኑም የመደራጀታቸው ምክንያት ግን ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጪ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እየመነጠሩ ማስወጣት ይፈልጋሉ።
ይህንን በማድረጋቸውም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን ስራ እና የንግድ በሮችን እንደሚከፍቱ በብርቱ ያምናሉ።
በእነዚህ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
አሌክሳንድራ ዱዱላ ሙቭመንት የተመሰረተው ባለፈው ዓመት ነው። ቡድኑን የሚደግፉ ደግሞ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች በመንግሥት የሚደጎሙ ቤቶችን፣ ለድሃ ደቡብ አፍሪካውን ተብለው የተዘጋጁ፣ በመኖሪያነት ይዘዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ነገር ግን ይህ ዘመቻ ማንኛውም ሕጋዊ ሰነድ የሌለው ስደተኛ በአሌክሳንድራ እንዳይነግድ ወደሚል አድጓል።
ባለፈው ወር ይህ እንቅስቃሴ፣ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እና ፓስፖርት ማሳየት ያልቻሉ የንግድ ተቋማትን ዘግቶ ነበር።
ከዚያም ሱቆቹን ለደቡብ አፍሪካውያን አከፋፈለ። ዌንዲ ሲትሆል ከዚህ በፊት ሌሎች አፍሪካውያን ይሸጡበት የነበረው ሱቅ ተሰጥቷት አትክልቶችን መሸጥ ጀምራለች።
"እኛ ደቡብ አፍሪካውያን ስራ በመፍታታችን ተቸግረናል። የምንፈልገው ስራ ማግኘት ብቻ ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። " በራሳችን አገር እንዴት አድርገን እንድንኖር ይፈልጋል?" ስትልም ትጠይቃለች።
ሁሉም የቡድኑ ድርጊት ግን ሕጋዊ አይደለም፤ በዚህም የተነሳ የአካባቢው ባለስልጣናት የተፈፀሙ የሕግ ጥሰቶችን እና ትንኮሳዎችን እየመረመሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ኦፕሬሽን ዱዱላ
የኦፕሬሸን ዱዱላ መቀመጫ በጆሃንስበርግ ሶፔቴ ነው።
በ33 ዓመቱ ናህላንሃላ ዴላሚኒ የተመሰረተ ሲሆን የበለጠ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሶዌቶ ነዋሪዎች ስደተኞችን "ጠራርገን እናስወጣቸው" የሚል ዘመቻ በጀመሩበት ወቅት ነበር።
ይህ ዘመቻ ትኩረት አድርጎ የነበረው የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን እና በሕገወጥ የመንግሥት ንብረቶችን ይዘዋል ባሏቸው ግለሰቦች ላይ ነበር።
ነገር ግን በአሌክሳንድራ ብቻ የቡድኑ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ እየሰፋ መጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዚህ ቡድን አባላት አሁን በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በውጪ አገራት ዜጎች የተያዙ ንግዶች ተዘግተው አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አነስተኛ ንግዶች ደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ቀጥረው እንዲያሰሩ ፍላጎት አላቸው።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ደቡብ አፍሪካውያንን ገሸሽ አድርገው በዝቅተኛ ዋጋ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ይቀጥራሉ ብለው ስለሚያምኑ ነው።
ባለስልጣናት እንደዚህ አይነት አዝማማያዎች ቢኖሩም ይህ ግን የተስፋፋ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ሁለቱም ቡድኖች መጤ ጠል አይደለንም ሲሉ ይናገራሉ። አክለውም የደቡብ አፍሪኣከውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከአደጋ እየተከላከሉ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚያም ወደ ኤኤንሲ፣ ገዢው ፓርቲ፣ ጣታቸውን በመቀሰር ይንንን ማድረግ ተስኖታል ሲሉ ይወነጅሉታል።
ቡድኖቹ አክለውም ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
ለተቃውሞው ምን ዓይነት ምላሽ ተሰጠ?
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጪ አገር ዜጎች በአገሪቱ ላለው የሰፋ ችግር ሁሉ እነርሱ ያለአግባብ ተጠያቂ እንደሆኑ ይናገራሉ።
"ምንም ዓይነት ስራ አልነጠቅናቸውም። እኛ የራሳችንን እድል ፈጥረን ነው እየሰራን ያለነው። ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን እንዳያደርጉ ያደረግነው አንዳች ነገር የለም" የሚለው ሞዛምቢካዊው ሳም ማኔኔ ነው።
ሳም ማኔኔ በአሌክሳክንድራ ላለፉት 10 ዓመታት የኖረ ሲሆን በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርቷል።
እንዲሁ ዓይናቸው እኛን ሲያይ ደም ይለብሳል ሲል ያክላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ ባይሰጥም አንዳንድ ፖለቲከኞች እና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ግን በአሌክሳንድራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጪ አገራት ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት፣ እንግልት እና ማሳደድ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።
አክለውም የሲቪል ማህበረሰቦች በአካባቢው ሰላም እና መቻቸል እንዲመጣ ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ነገር ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች ይህንን ጉዳይ የፖለቲካው ትኩሳት መለኪያ፣ የአጀንዳቸው ማገዶ ሊያደርጉት እየሞከሩ መሆኑ ተስተውሏል።
ከዚህ ቀደም እስር ቤት የነበረው እና ከተፈታ በኋላ ፓትሪዮቲክ አሊያንስ (ፒኤ) የሚል ፓርቲ የመሰረተው ጌይቶን ማኬንዚ ከእነዚህ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነው።
ይህ አዲስ የተመሰረተው ፓርቲ ምንም እንኳ በአገር አቀፍ ደረጃ መቀመጫ ባያገኝም በአካባቢ ምክር ቤት ውስጥ ተወካዮች አሉት። ፓርቲው ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ፣ በድንገት በጆሃንስበርግ የሚገኙ ምገብ ቤቶች ላይ "ምልከታ" አድርገዋል።
ይህም ምግብ ቤቶቹ ምን ያህል ደቡብ አፍሪካውያንን ቀጥረው እንደሚያሰሩ ለመቆጣጠር እና ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
ይህ አሁን ለምን ሆነ?
በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በ2008 እኤአ በመላ አገሪቱ በስደተኞች ላይ ጥቃት ደርሶ ነበር።
በዚህም የተነሳ ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በ2015 እንዲሁ በደርባን እና በጆሃንስበርግ በስደተኞች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ መንግሥት ወታደሮቹን ለማሰማራት ተገድዶ ነበር።
ከሶስት ዓመት በኋላም ሌላ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ተገድደዋል።
በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር በተስተዋለበት በአሁኑ ወቅት ይህ እንቅስቃሴ ለምን እንደተጀመረ በቂ መረጃ የለም።












