የዩቲዩብ ኮከብ የሆነው ህንዳዊው የጉልበት ሠራተኛ

አይሳክ ሙንዳ በቤቱ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Isak Munda

ከህንዷ ኦሪሳ መንደር የፈለቀው አንድ የጉልበት ሠራተኛ 'ዕድሜ' ለኮሮናቫይረስ ይሁንና እነሆ አሁን የማሕበራዊ ድር አምባው ኮከብ ሆኗል።

ኢሳክ ሙንዳ የመጀመሪያዋን ተንቀሳቃሽ ምስል ዩቲዩብ ላይ የሰቀለው በፈረንጆቹ መጋቢት 2020 ነበር። የዛሬ ሁለት ዓመት ማለት ነው።

በወቅቱ ሕንድ ኮሮናን ለመከላከል በሚል ዜጎቿ ከቤታቸው ንቅንቅ እንዳይሉ ያዘዘችበት ጊዜ ነበር።

ኢሳክ የሚሠራበት የግንባታው መስክም በወረርሽኙ ምክንያት አከርካሪው ተመታ። እሱና መሰሎቹ ቤት መዋል ጀመሩ።

ይኼኔ ነው አንድ ሐሳብ ውልብ ያለበት።

ልጆቹ እንደ ዘንድሮ ልጅነታቸው ዩቲዩብ ላይ ተጥደው የሕጻናት ፊልም ያያሉ። ድንገት ግን አንድ ማስታወቂያ ብቅ አለ። ኢሳክ እንደወትሮው ይሄን ማስታወቂያ ለማሳለፍ አልቸኮለም።

ማስታወቂያ እንዲህ ይላል፡ ዩቲዩብ ላይ ቪድዮ ሰቅላችሁ ቤሳ መሰብሰብ ከፈለጋችሁ እኛ እናግዛችኋለን። ኢሳክ ይኼኔ ብሞክረው ምን አጣለሁ የሚል ሐሳብ መጣለት።

ወደ ሥራ ለመግባት አላመነታም። ዩቲዩብ ላይ የተሰቀሉ ስለዩቲዩብ የሚያወራ ምስሎችን እያማረጠ ይመለከት ጀመር።

ኢሳክ የመጀመሪያ ቪዲዮውን ዩቲዩብ ላይ ለጠፈ። ቪድዮው ተመልካቾቹን ሰላም ካለ በኋላ አንድ ሙሉ ቤተሰብ የሚመግብ ማዕድ ብቻውን ሲሰለቅጥ ያሳያል።

በርካታ ሚሊዮኖች ጎርፈው ይመለከቱታል ብሎ ቢጠብቅ፣ ዩቲዩብን እየዘጋ ቢከፍት የሱን ቪዲዮ ከቁብ የሚቆጥር ጠፋ።

"ለአንድ ሳምንት ያክል አንድም ሰው የኔን ቪዲዮ አልተመለከተም። በጣም ከፍቶኝ ነበር" ይላል።

ነገር ግን ኢሳክ ተስፋ አልቆረጠም። ወደ ዩቲዩብ መንደር ተመልሶ እንዴት ተመልካቾች ማፍራት እንደሚቻል ሲቃኝ ማስታወቂያ መሥራት እንደሚችል ተማረ።

"የፌስቡክ ገፅ ከፍቼ እዚያ ላይ ማስተዋወቅ ያዝኩ። 10 አሊያም 12 ሰዎች ተመለከቱልኝ።"

በርካታ ሺህ ሰዎችን የሳበለት ቪድዮ ባሲ ፓካላ የተባለ የህንድ ማዕድ እምሽክ ሲያደርግ የሚታይበት ነው። ኢሳክ በአንዴ ጣራ ነካ።

ኤእሳክ ሙንዳ ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Isak Munda

"በአንድ ጊዜ 20 ሺህ ሰዎች 'ሰብስክራይብ' አደረጉልኝ። ከመላው ዓለም - ከአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሞንጎሊያ ሰዎች ተመለከቱት" ሲል ያስታውሳል።

እነሆ ሁለት ዓመታት ተቆጥረው ኢሳክ ሙንዳ ኢቲንግ የተባለው የዩቲዩብ ገፁ ከ800 ሺህ በላይ ተከታዮች አሉት። እስካሁን የሰቀላቸው ቪዲዮዎች ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አፍርተውለታል።

ባለፈው ዓመት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፤ ኢሳክን በራድዮ ፕሮግራም ቀርበው አሞጋግሰውታል።

ዩቲዩብን በዩቲዩብ መቆጣጠር

ኢሳክ የሚሠራቸው ምስሎች በዩቲዩብ ቋንቋ "መክባንግ" ይባላሉ።

በዚህ ዘርፍ የሚመደቡ ሰዎች ከፊታቸው ካሜራ የሚሸፍን ምግብ ቆልለው አንዳንዴ በዝምታ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከተመልካቾቻው ጋር እያወጉ ምግብ ዶግ አመድ ሲያደርጉት ይታያሉ።

ይህ ፋሽን የተጀመረው በፈረንጆቹ 2012 ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ውስጥ ነው። ለጥቆ ወደ መላው ዓለም ተዛመተ። ሚሊዮኖች የመሰል ቪዲዮዎች አድናቂ ናቸው።

የመክባንግ ወዳጆች "ምግብ ስንበላ ይህንን ቪድዮ ከፍተን ነው የምንበላው ምክንያቱም ብቻችን እንዳልሆንን እንዲሰማን" ይላሉ።

ኢሳክ ምስሉን ዩቲዩብ ላይ ሲሰቅል ስለመክባንግ የሚያውቀው ጉድ አልነበረውም። ምን ዓይነት ምስል ብሰቅል ያዋጣኛል እያለ ሲያምስ ነው ምግብ ላይ ያረፈው።

"ተመልካቾች በምናዘጋጀው ምግብ ምን ዓይነት ኑሮ እንደምንኖር መመልከት ይሻሉ ብዬ አሰብኩ" ይላል።

አይሳክ ሙንዳ ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Isak Munda

ኢሳክ ስለዩቲዩብ ትምህርት የቀሰመው ከራሱ ከዩቲዩብ ነው።

ምን ዓይነት ካሜራ መግዛት እንዳለበት፣ ቪድዮ መቅዳትና ማሰናዳት፣ አልፎም ስለምግብ አዘገጃጀት ዕውቀት የቀሰመው ከዩቲዩብ ነው።

ካጠራቀመው ገንዘብ 3 ሺህ ሩጲ [39 ዶላር] መዥረጥ አድርጎ አውጥቶ ቪዲዮ የሚቀርፅበት ስልክ ገዛ። በወቅቱ 3 ሺህ ሩጲ ማለት ለኢሳክ ትልቅ ገንዘብ ነበር። ስልክ የገዛውም በወርሃዊ ክፍያ እንጂ በአንድ ጊዜ ክፍያ አልነበረም።

አስኳላ ቢሄድም አላገባደደም። የእንግሊዝኛ ቋንቋ እውቀት የሚያስመካ አልነበረም። ነገር ግን በይነ መረብ እያለ የሚሳነኝ የለም ሲል ተነሳ።

በኢሜልና በማሕበራዊ ድር አምባ ስለዩቲዩብ ገፁ ያውጅ ገባ። ጉግል ትራንስሌት የተሰኘውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ለሚያዘጋጀው ቪድዮ የእንግሊዝኛ ትርጉም አስገባ።

ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ መጣ።

በመጀመሪያ ቪዲዮው ላይ እንዲሁ ቁጭ ብሎ ከሰላምታ በኋላ ምሳውን ሲያላምጥ ነበር የሚታየው። ይህ እንግዲህ መጋቢት 2020 መሆኑ ነው።

ሁለት ዓመት ተጉዘን የካቲት 2021 ላይ የኢሳክን ገፅ ብንቃኘው ልዩነቱን እናስተውላለን።

አሁን እንደ ቀድሞው በየሰዓቱ ምግብ ሲበላ አይለጥፍም። አሁን በየመንደሩ እየዞረ የሃገሩን ባሕል እያስቃኘ 'ፓርቲ' ያለባቸው ቦታዎች እየሄደ ነው የሚቀረፀው።

ሕንዳውያን ገንቢ አስተያየት ይሰጡታል። በርካቶች የሚኖረውን ሕይወት ሳይጨምር ሳይቀንስ ለመላው ሕዝብ ስለሚያቀርብ ይወዱታል። 'ኦሪጂናሌ' ነው ይሉታል።

ኢሳክ በሚሠራቸው ቪድዮዎች ላይ ባለቤቱና ልጆቹ አልፎ አልፎ ይታያሉ።

እንጨት ፈልጦ፣ እሣት አቀጣጥሎ ያበሰለውን ሩዝ ከሚስቱና ባለቤቱ ጋር ተጋርቶ ሲመገብ ያሳያል።

"ምንም እንኳ አሁን በየቀኑ ስጋ መብላት ብንችልም እንደ ወትሮው ቀለል ያለ ምግብ መመገብ እንመርጣለን" ይላል።

ለልጆቼ የወፊት ሕይወት

ኢሳክ የቀን ሠራተኛ ሳለ በቀን የሚያገኘው ገቢ 250 ሩጲ ነበር። በወር 18 አሊያ 20 ቀን ሠርቶ የሚያመጣው ገንዘብ ቤተሰቡን ለማስተዳደር በቂ አልነበረም። አራት ልጆቹን፣ ሚስቱ፣ ወላጆቹን ለመደጎም እጅ ያጥረው ነበር።

አሁን ከዩቲዩብ የሚያገኘው ረብጣ ሩጲ ነው። በወር ከ60 ሺህ እስከ 300 ሺህ ሩጲ ይዝቃል።

ከዩቲዩብ ባገኘው ገንዘብ በፊት ደሰሳ ጎጆው የቆመበት መሬት ላይ ሁለት ፎቅ ያለው መኖሪያ ቤት ገንብቷል።

ለልጆቹ ወደ ፊት የትምህርት ቤት ወጭ የሚሸፍን ገንዘብ ቆጥቧል። 'ሰከንድ ሃንድ' መኪና ገዝቷል። ቪዲዮዎቹን የሚያሰናዳበት ላፕ ቶፕም ሸምቷል።

አሁን በመንደሩ ታዋቂ ሆኗል። ለአካባቢው ሰዎች አንዳንዴ ድግስ ያሰናዳል። ዶሮ አርዶ ያቀርባል።

የኢሳክ ቀጣይ ዕቅዱ ልጆቹ እንግሊዝኛ አቀላጥፈው እንዲናገሩ የሚያስችል ትምህርት ቤት ማስገባት ነው።

"ልጆቼ ምርጥ ትምህርት ቤት እንዲማሩ እፈልጋለሁ። እኔ ብዙ ሳልማር እንዲህ ማድረግ ከቻልኩ፤ እነሱ ትምህርት ቢቀስሙ የተሻለ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ አምናለሁ።"