ከዩቲዩብ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚሰበሰቡት አስሩ ከፍተኛ ተከፋይ ዩቲዩበሮች ማናቸው?

የፎቶው ባለመብት, MrBeast/Youtube
ፎርብስ የተሰኘው የአሜሪካ የቢዝነስ መጽሔት እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ከዩቲዩብ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኘውን ዩቲዩበር ይፋ አድርጓል።
ስሙ ጂሚ ዶናልድ ሰን ቢሆንም ተከታዮቹ የሚያውቁት 'ሚስተር ቢትስ' በሚለው ቅጽል ስሙ ነው።
ሚስተር ቢትስ እድሜው 23 ሲሆን የልጅ ሃብታም ነው። ዩቲዩብ ላይ የጫናቸው ቪዲዮዎች በድምሩ ከአስር ቢሊዮን ጊዜ በላይ ታይተው 54 ሚሊዮን ዶላር ወይም በወቅታዊ ምንዛሬ ወደ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ኪሱ አስገብቷል።
ልጁ ከእሱ በ13 ዓመት የሚያንሰው የ10 ዓመቱ ራያን ካጅ ለሁለት ዓመታት ይዞት የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብሯል። የ10 ዓመቱ ታዳጊ ሃብታም ላለፉት ሁለት ዓመታት በዩቲዩብ ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰብ የሚወዳደረው ዩቲዩበር አለነበረም - አሁን ሚስተር ቢትስ መጣበት እንጂ።
እንደ ፎርብስ ግምት ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ የ2021 አስሩ ከፍተኛ ተካፋይ ዩቲዩበሮች በደምሩ 300 ሚሊዮን ዶላር [እንመንዝረው] 15 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር አግኝተዋል። ይሄ ከብዙ አገራት ዓመታዊ በጀት በብዙ እጥፍ የሚልቅ ወይም የሚስተካከል ነው።
ጄክ ቦል የተሰኘው ቦክሰኛ እና ዩቲዩበር ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ታዲያ የዘንድሮ የዩቲዩብ ከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር የዩቲዩብ ባለሙያዎችን ጭምር ያስገረመ ነው። ምክንያቱም ካለፉት ዓመታት በተለየ ወንዶች እና ነጮች የበዙበት ዝርዝር መሆኑ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወርርሽኝ በርካታ የመዝናኛ ኢንደስትሪዎችን ክፉኛ ያጎሳቆለበት ነው። ለዩቲዩብ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው። ማኅበራዊ መድረኩ ከምንጊዜውም በላይ ገበያው የደራለት ከወረርሽኙ በኋላ ነው።
ዩቲዩብ በ2021 በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተጠቃሚዎቹ 2.3 ቢሊዮን ደርሰውለታል። የዓለም ሕዝብ 30 በመቶ አካባቢ ማለት ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉት ተጠቃሚዎቹ በደምሩ በቀን አንድ ቢሊዮን ሰዓታት የሚፈጅ ቪዲዮ ይመለከታሉ።
ለመሆኑ የዓለም ከፍተኛ ተከፋይ ዩቲዩበሮች እነማናቸው?
10. ፕሬስተን አርሴመንት
ፕሬስተን አርሴመንት 'ማይንክራፍት' የተሰኘ ጨዋታ ላይ ያተኮሩ ቪዲዮዎችን በብዛት ቢሰራም ሌሎችንም ይዘቶችን ያጋራል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ አስረኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2021 በግምት 16 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል። ገቢው ካለፈው ዓመት አንጻር ዝቅ ያለ ሲሆን አምና በስደሰተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጦ ነበር።
9. ሎጋን ፖል
ሎጋን ፖል አወዛጋቢው ቦክሰኛ እና የዕለት ውሎውን በቪዲዮ የሚያስቃኝ [ቭሎገር] ነው። እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 አስረኛ ላይ ተቀምጦ ነበር። አምና ከዩቲዩብ 18 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።
8. ዱድ ፐርፌክት
አስቂኝ ፕራንክ የሚሰራው ዱድ ፐርፌክት በ2020 በዝርዝሩ ውስጥ ሦስትኛ ነበር። ባለፈው ዓመት ግን 8ኛ ሆኖ 20 ሚሊዮን ዶላር አስገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, YouTube/Ryan's World
7. ሪያን ካጂ
በዓለም ላይ በጣም ታዋቂው ዩቲዩበር የሆነው ሪያን ካጅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረበት የአንደኛ ደረጃ ወደ ሰባተኝነት ወርዷል።
በ2021 ከሚታወቅበት የህጻናት መጫወቻዎች ቅኝት በተጨማሪ ትምህርታዊ ቪዲዮዎች እና የቤተሰብ ቭሎጎች በመስራት 27 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል።
6. ናስታያ
የሰባት ዓመቷ ሩሲያዊ ዩቲዩብር ወደ 90 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ወይም ሰብስክራይበርስ አላት።
ናስትያ ዩቲዩብ የጀመረችው የልጆች መጫዎቸዎችን በተመልካቾች ፊት በመክፈት ነበር። አሁን ግን ቭሎጎችን እና የሙዚቃ ቪዲዮዎቿ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅነት እያገኙ ሲሆን በ2021 ወደ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘት ችላለች።

የፎቶው ባለመብት, Nastya/YouTube
5. አንስፒከብል
በከፍተኛ ተከፋይ ዝርዝር ውስጥ አዲስ ገቢ የሆነው አንስፒከብል ማይንክራፋት የተሰኘ ጫታዎች በዩቲዩብ ለአስር ዓመታት ሲያቀርብ ቆይቷል።
ከአንድ የስፖተር ቢዝነስ ጋር ያደረገው ስምምነት ገቢው ወድ 28.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲመነደግ አስተዋፅኦ አድርጓል።
4. ሬሄት ኤንድ ሊንክ
በዩቲዩብ የሚተላለፍ የውይይት ፕርግራም አዘጋጅ ሲሆኑ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 30 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።
3. ማርኪፕለር
የጨዋታ ወይም ጌም አበልጻጊ ሲሆን ማርኪፕሊየር የሰኘውን ስሙን ተጠቅሞ የተሳካ የንግድ ምልክት አድርጎታል። ባለፈው ዓመት 38 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል። ሦስተኛ ደረጃንም ይዟል።
2. ጄክ ፖል
ቦክሰኛው ጄክ ፖል በዩቲዩብ ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ኮከቦች ከተሰኙ ቦክሰኞች ጋር ያደረገው ከፍተኛ ፍልሚያ በርካታ ተመላካች ያስገኘለት ሲሆን በዓመቱ 45 ሚሊዮን ዶላር እንዲያገኝ ረድቶታል።
1. ሚስተር ቢትስ
በዩቲዩብ ከፍተኛ ገቢ አንደኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ተመልካቹን ለማስደሰት የተለያዩ ፕርግራሞችን እና ጨዋታዎችን ይጠቀማል።
በዩቲዩብ 10 ቢሊዮን ዕይታ ያገኘ ሲሆን 54 ሚሊዮን ዶላር ገቢን በመሰብሰብ አምና ከነበረበት 2ኛ ደረጃ ወደ 1ኛ ከፍ ብሏል።














