ውጥረት (ስትረስ) ለጤናችን ምን ያህል አደገኛ ነው? እንዴትስ ጉዳቱን ልናስቀር አንችላለን?

ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

የምስሉ መግለጫ, ውጥረት ያስከተለብዎ ነገር ምንድን ነው? አጣዳፊ ሥራ? የገንዘብ ችግር? የቤተሰብ ሁኔታ ወይስ አስደንጋጭ ገጠመኝ?

አብዛኞቹ አዋቂ ሰዎች ከራስ ምታት እስከ መረበሽ የሚደርስ የውጥረት ምልክት በየጊዜው ያጋጥማቸዋል።

አንዳንድ ውጥረቶች ጠቃሚ ሊሆኑ ቢችሉም፣ ሥር የሰደደ ውጥረት ግን በሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳል።

ለተለያዩ የሥነ ልቦና እና ሥነ አካላዊ መዛባቶች፤ የአእምሮ እና የአካል ጤናን በመጉዳት መልካም ሕይወት መምራት እንዲያቅት ሊያደርግ ይችላል ሲሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ውጥረትን መቆጣጠር እና ወደ ጥንካሬ ምንጭነት መቀየር ይቻላል።

ውጥረት (ስትረስ) ምንድን ነው? ለምንስ ያጋጥመናል?

ውጥረት ሰውነታችን ለችግሮች እና ለጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ የሚያዘጋጅ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው።

ሰውነት አስቸጋሪ ሁኔታን ለመቋቋም እንዲችል የሚያዘጋጁ ሆርሞኖችን እንዲያመነጭ ያደርጋል።

ለአጭር ጊዜ ሲሆን ይህ ምላሽ ትኩረትን ከፍ ሊያደርግ እና ውጤታማነትን ሊያሻሽል ይችላል።

ይኹን እንጂ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ውጥረት የልብ ሕመምን እና የበሽታ መከላከል አቅምን ማዳከምን ጨምሮ ከባድ የጤና አክሎቸን ያስከትላል ይላል የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር።

ውጥረትን የሚቀሰቅሱ ምክንያቶች ሥራ፣ የገንዘብ ችግር እና የግል ግንኙነቶችን ጨምሮ ሌሎችም ሲሆኑ፤ ብዙውን ጊዜ ሊወገዱ የማይችሉ ናቸው።

ዋናው ልዩነት ውጥረት ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው ነው። አጣዳፊ ውጥረት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እና ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ሥር የሰደደ ውጥረት ግን በሰውነት ላይ ዘላቂ ጫናን ያስከትላል።

በሃሳብ ውስጥ ያለ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አስቸጋሪ ወይም አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን አንጎላችን ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሆርሞኖች ያመነጫል

አጣዳፊ እና ሥር የሰደደ ውጥረት

"ፈጣን ውጥረት ለተወሰነ ሁኔታ የሚሰጥ የአጭር ጊዜ ምላሽ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎችም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ሳይኮቴራፒስት እና የብሪቲሽ የምክር እና ሳይኮቴራፒ ማኅበር (ቢኤሲፒ) አባል የሆኑት ራቼል ቮራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንጎላችን "ተጋፈጥ ወይም ሽሽ የሚል ምላሽን በመፍጠር አድሬናሊን እና ኮርቲሶል ይለቀቃል። ይህም ትኩረትን ለመጨመር እና ለበሽታ የመከላከያ ሥርዓታችን ጊዜያዊ ማበረታቻ ሊሰጥ ይችላል።"

በአግባቡ ከተያዘ አጣዳፊ ውጥረት ዘላቂ ጉዳት አያስከትልም። ግለሰቦች ለፈጣን ተግዳሮቶች ውጤታማ ምላሽ እንዲሰጡ ሊረዳቸው ይችላል። ሥር የሰደደ ውጥረት ግን በሰውነት ላይ ረዘም ያለ ጫና ይፈጥራል።

ውጥረት ለረዥም ጊዜ በሚቆይበት ጊዜ ከፍ ያለ የውጥረት ሆርሞኖች ለልብ በሽታ ተጋላጭነትን እንደሚጨምሩ፤ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን እንደሚያዳክሙ እና በአንጀት ላይ ቁስለት በመፍጠረ ለምግብ መፈጨት ችግሮች አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ቮራ አስረድተዋል።

ሥር የሰደደ ውጥረት ከጭንቀት እና ድብርት፣ ከግንዛቤ መጓደል፣ ከእንቅልፍ መዛባት እና ከተፋጠነ የሰውነት እርጅና ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

እንደ ቮራ ገለጻ ከሆነ ይህ የቆይታ እና የመፍትሔ መሠረታዊ ልዩነት ወደ ሥር የሰደደ ውጥረት ቀስ በቀስ በማደግ በርካታ የሰውነት ሥርዓቶችን ይጎዳል።

ውጥረት በሰውነት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ውጥረት ሆርሞኖችን በዋናነትም ኮርቲሶል እና አድሬናሊን በመልቀቅ አካላዊ ምላሾችን እንደሚያስነሳ ያስረዳል። እነዚህ ምላሾች የሚከተሉትን ያካትታሉ:

  • በኦክስጅን የበለፀገ ደም ወደ ጡንቻዎች በፍጥነት በማድረስ የልብ ምት እና የደም ግፊት ይጨምራል
  • በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ እንዲል በማድረግ ፈጣን የኃይል መጨመር ያስከትላል
  • የምግብ መፈጨትን እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅምን በማዳከም ፈጣን ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሰውነት ኃይልን ያግዛል።

ይኹን እንጂ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ውጥረት ጎጂ ሊሆን ይችላል። የማያቋርጥ ውጥረት ከሚከተሉት ጋር ይያያዛል፡-

  • የሰውነት ክብደት መጨመር (በኮርቲሶል ምክንያት በተለይም በሆድ አካባቢ)
  • ለረጅም ጊዜ ለጭንቀት ሆርሞኖች በመጋለጥ ምክንያት የሚከሰቱ የማስታወስ እና የትኩረት ችግሮች
  • የሰውነትን የማገገም እና የመጠገን አቅምን የሚረብሽ የእንቅልፍ መዛባት

የዩኬ በሔራዊ የጤና አገለገሎት የማያቋርጥ ውጥረት እንደ የልብ ሕመም፣ የምግብ መፈጨት ችግር እና እንደ ጭንቀት እና ድብርት ያሉ የአአምሮ ጤና ችግሮች ላሉ የረጅም ጊዜ ሁኔታዎች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያስጠነቅቃል።

አስቸጋሪ ወይም አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን አንጎላችን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚረጨው ሆርሞን የልብ ምትን ይጨምራል፤ የደም ግፊትን ይቆጣጠራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አስቸጋሪ ወይም አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን አንጎላችን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚረጨው ሆርሞን የልብ ምትን ይጨምራል፤ የደም ግፊትን ይቆጣጠራል

ውጥረት ጠቃሚ ሊሆን ይችላልን?

በካሊፎርኒያ ኧርቪን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጎልናዝ ታቢብኒያ "የመቋቋም ችሎታ ያለዎት ወይም የሌለዎት ነገር ብቻ ሳይሆን በጊዜ ሂደት ሊዳብር የሚችል ክኅሎት ነው" ብለዋል።

ተግዳሮቶችን ከመሸሽ ይልቅ በንቃት መጋፈጥ የመቋቋም ችሎታን ለመገንባት ይረዳል ሲሉ አክለዋል።

እንደ ዶ/ር ታቢብኒያ አመለካከት ሰዎች ውጥረትን ከጎጂነት ይልቅ አጋዥ አድርገው ሲመለከቱ የፊዚዮሎጂ ጭንቀት ምላሽ ይቀንሳል።

ቀላል የአስተሳሰብ ለውጥ ተአምራትን ይፈጥራል። በዚህም ጭንቀትን በመቀነስ አፈፃፀምን ያሳድጋል።

"ውጥረትን በቸልተኝነት ከማስወገድ ይልቅ በንቃት መቋቋም ወደፊት የሚፈጠሩ ጭንቀቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር አእምሮን እንደገና ያዘጋጃል። በጂም ውስጥ እንደመሆን ዓይነት ነው። ክብደት ማንሳት አስጨናቂ ነው፣ ግን የበለጠ ጠንካራ ያደርገናል" ብለዋል።

የውጥረት እና የጭንቀት ልዩነት

በውጥረት እና በጭንቀት መካከል ያለውን ቁልፍ ልዩነት እንዲያብራራ የጭንቀት መታወክ ያለባቸውን ግለሰቦች የሚደግፈውን 'አንዛይቲ ዩኬ' የተባለውን ብሔራዊ የበጎ አድራጎት ድርጅትን ቢቢሲ ጠይቋል።

ውጥረት ለምሳሌ እንደ የሥራ ቀነ ገደብ፣ የመንጃ ፈቃድ ፈተና ላሉ ለውጫዊ ሁኔታ የሚሰጥ ምላሽ ነው ሲል መልሷል። ከፈተናው ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን ችግሩ ከተፈታ በኋላም ይጠፋል።

ጭንቀት ግን ሊታወቅ በማይችል ምክንያት እንኳን ሊቀጥል ይችላል።

ጭንቀት ሰዎች በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆኑ ንቁ ሆነው እንዲቆዩ የሚረዳ ስሜት ቢሆንም፤ ከመጠን በላይ ወይም የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚረብሽ ከሆነ ግን ችግር ይፈጥራል።

ውጥረት እና ጭንቀት ሰውነት "እንዲጋፈጥ ወይም እንዲሸሽ" ምላሽ የሚሰጠውን የነርቭ ሥርዓትን ያንቀሳቅሳል።

ይህ ማለት ሁለቱም እንደ የልብ ምት መጨመር፣ ማላብ እና መንቀጥቀጥ ያሉ ምልክቶችን ይቀሰቅሳሉ። የጭንቀት ግን የበለጠ ዘላቂ እና ከባድ ይሆናል።

አጣዳፊ የጭንቀት እና የድንጋጤ አደጋዎችን ለመቆጣጠር አንዛይቲ ዩኬ የአተነፋፈስ ልምምዶችን ይመክራል።

ቀላል ነገር ግን ውጤታማው ዘዴ አየር ከማስገባት ይልቅ ማስወጣት ላይ ጊዜ መውሰድ መሆኑን ጠቅሷል። ይህም ሰውነት ዘና እንዲል በማድረግ የነርቭ ሥርዓትን በፍጥነት ያረጋጋል።

ፊቷን የሸፈነች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ውጥረትን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ውጥረት በሰውነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የባህሪ ልምምዶችን ጠቃሚ ውጤቶች የአካዳሚክ ጥናት አጉልቶ አሳይቷል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የጭንቀት ሆርሞንን በመቀነስ ጥሩ ስሜትን ከፍ እንደሚያደርግ ተረጋግጧል።

ሜዲቴሽን (አረምሞ/ተመስጦ) ደግሞ አእምሮን ለማረጋጋት ያግዛል። ማኅበራዊ ድጋፍ ስሜታዊ ጥንካሬን በማጉላት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ጥናቶች አመልክተዋል።

ዶ/ር ታቢብኒያ በበኩላቸው አመስጋኝነት እና ደግነት እንዲሁም ደግሞ በሳይንስ የተደገፉ እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ከቤት ውጪ ጊዜ ማሳለፍ እና ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር ያሉ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተዋል።

በለንደን የ7ብሪዝ መሥራች የሆኑት ዩኪ ደግሞ ሁሉንም የመከተልን አስፈላጊነት ያጎላሉ።

"ውጥረትን መቆጣጠር ማለት ዘና ማለት ብቻ አይደለም። የእርስዎን አእምሯዊ እና አካላዊ ደኅንነትን የሚደግፍ የአኗኗር ዘይቤን መፍጠር ነው። ለጤንነትዎ ቅድሚያ ሲሰጡ ውጥረትን ለመቋቋም ቀላል ይሆናል" ብለዋል።

ትኩረትን ማሳደግ፣ እንቅልፍን፣ የአካል እንቅስቃሴን እና የተመጣጠነ ምግብን እንደ ውጥረትን ለመቆጣጠር አስፈላጊ እንደሆኑ ገልጸዋል።

"የእርስዎ ማይክሮባዮም ጭንቀትን በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ለጤናማ ምግብ ቅድሚያ መስጠት ለአጠቃላይ ደኅንነት ቁልፍ ነው" ሲሉ አክለዋል።

እንደ ዩኪ ገለጻ ከሆነ ውጥረትን በፈጣን ጥገናዊ ለውጦች ማሻሻል አይቻልም። የዕለት ተዕለት ልማዶችን መፍጠር ነው ጥንካሬውን የሚያሳድጉት።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት "ውጥረት ያሻሽላል" የሚል አስተሳሰብን የተቀበሉ ግለሰቦች የተሻሻለ አፈጻጸም፣ የድካም ስሜት መቀነስ እና የተሻለ ስሜታዊነት አላቸው።

የሐርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ጥናት እንደሚያሳየው ውጥረትን እንደ አስጊ ሳይሆን እንደ ተግዳሮት መውሰድ በሰውነት ላይ ያለውን ተጽእኖ በእጅጉ ሊለውጠው ይችላል።

"ሰዎች ውጥረትን ከጎጂነት ይልቅ አጋዥ አድርገው ሲመለከቱ የፊዚዮሎጂ ውጥረታቸው ምላሽ ይቀንሳል" ሲሉ ዶ/ር ታቢብኒያ አጠቃለዋል።

"በውጥረት ላይ ያለውን አመለካከት በመቀየር ግለሰቦች ተግዳሮቶችን ወደ ግላዊ ዕድገት እና ችግሮችን የመቋቋም ዕድሎች ሊለውጡ ይችላሉ" ብለዋል።