ፊንላንድ ለአባቶች የእናቶችን ያህል የሥራ ፈቃድ ልትሰጥ ነው

ጨቅላ ልጅ ያቀፈች እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ እንዲችሉ ለማድረግ ለሁሉም ወላጆች ተመሳሳይ የእረፍት ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያስችለውን ዕቅድ አዲሱ የፊንላንድ መንግሥት ይፋ አደረገ።

የጾታ እኩልነትንና ደህንነትን ለማበረታታት በሚል የሚሰጥው እረፍ ክፍያንም እንደሚጨምር ታውቋል።

የፊንላንድ ጎረቤረት የሆነችው ስዊድን ወላጆች ልጅ ከወለዱ በኋላ ለእያንዳንዳቸው 240 የወላጆች የእረፍት ፈቃድን በመስጠት በአውሮፓ ውስጥ ለጋስ የሆነ የተደነቀ ሥርዓትን በመዘርጋት ትታወቃለች።

የፊንላንድ የጤናና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት አይኖ-ካይሳ ፔኮነን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከመጀመሪያው አንስቶ የወላጆችን ግንኙነት ለማጠናከር ባለመ ሁኔታ "ቤተሰቦች በሚያገኙት ጥቅማጥቅሞች ላይ መሰረታዊ ለውጥ" ተደርጓል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፊንላንድ ለወለዱ እናቶች ከአራት ወራት በላይ የወሊድ ፈቃድ የምትሰጥ ሲሆን ለአባቶች ደግሞ ከሁለት ወር በላይ ፈቃድ ይሰጣል። ነገር ግን በአማካይ ከአራት ወንዶች አንዱ ብቻ ነው የተሰጠውን ፈቃድ የሚጠቀምበት። አሁን የታቀደው የፈቃድ አይነት የወላጆች ፈቃድን ብቻ የሚመለከት ነው ተብሏል።

ወላጆች ከሚሰጣቸው ፈቃድ ውስጥ 69 ቀኑን ወደ ሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ነፍሰጡር እናቶች አንድ የወር ደሞዝን ያህል ክፍያን ያገኛሉ ተብሏል።

የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪና ባለፈው ወር እንዳሉት አገራቸው የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚቀሯት ሥራዎች እንዳሉና ልጆቻቸው ታዳጊ እያሉ አብረዋቸው ጊዜ የሚያሳልፉ አባቶች ቁጥር በጣም ውስን ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

በኦስሎ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሊሲ ኢሊንግሳትር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፊንላንድ የምትገኝበት የኖርዲክ አካባቢ አገራት ወደ እናቶች የማይዘዋወር የወላጅነት የሥራ ፈቃድ በመስጠት በኩል ቀዳሚ ሆነው ቆይተዋል።

የአውሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ ውሳኔን እየተከተለ ሲሆን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አባል አገራት ለእያንዳንዱ ወላጅ የአራት ወር ፍቃድ እንዲሰጡና ከዚህም ውስጥ ሁለቱ ወር ወደ ሌላ ጊዜ የማይተላለፍ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው።

ፖርቱጋል የትኛውንም ጾታ የማይለይ ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ያላት አገር ናት። በዚህም ለሁለቱም ወላጆች የአራት የሥራ ፈቃድና ሙሉ ደሞዝ እንዲሁም የሚፈልጉ ከሆነ ተጨማሪ አንድ ወር ፈቃድና የደሞዛቸውን 80 በመቶ እንዲያገኙ ይፈቀዳል።

ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ፊንላንድ በአራት ፓርቲዎች ጥምረት እየተመራች ሲሆን እያንዳንዱን ፓርቲም የሚመሩት ሴቶች ናቸው።

ለወላጆች በሚሰጠው የሥራ ፈቃድ ላይ የሚደረገው ለውጥ የፊንላንድ መንግሥትን ተጨማሪ 110 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣው ተገምቷል።

ስዊዲን፣ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ኢስቶኒያና ፖርቱጋል ለቤተሰብ ተስማሚ የሆነ ፖሊሲ በማውጣት ባለፈው ዓመት በዩኒሴፍ አድናቆትን አግኝተዋል።