ከአምልኮ ቦታ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ 'ግጭት' 7 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነገረ

የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት

የፎቶው ባለመብት, የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት

ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ገደማ በአዲስ አበባ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ እስካሁን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 7 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 7 ሰዎች መካከል አመራሮች ይገኙበታል ቢሉም አመራሮቹ የኃላፊነት ደረጃ አልጠቀሱም።

ምክትል ከንቲባው ከሰዓታት በፊትም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በግጭቱ የሁለት ወጣቶች ህይወት ማለፉ እንዳሳዘናቸው ገልጸው "በየትኛውም ወገን ያሉ የጥፋቱ አካላትን በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን" ብለው ነበር።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

ምክትል ከንቲባው ከይዞታ ይገባኛል ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ አስተዳደራቸው ጥያቄዎችን ሲመልስ መቆየቱን አመልክተው፤ "በመንግሥት እና በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት በከተማችን ይሆናል ያላልነው፤ እንዳይሆንም የለፋንበት ድርጊት ተፈጽሟል" በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አመሻሽ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቤተክርስቲያኗ ትናንት ምሽት በተፈጠረ አለመግባባት የሁለት ወጣቶች ህይወት ማለፉ እንዳሳዘናት ገልጸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጉዳዮችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ መፍታት እየተቻለ የተፈጠረው ችግር ተገቢ ያልሆነ እና መፈጠር የሌለበት ነው ብለዋል።

የወንጀል ምርመራወእን ሂደት ዝርዝር ሪፖርት ለህዝብ ይፋ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ውዝግብ ያስነሳው የማምለኪያ ቦታ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት የካህናት አስተዳዳር ኃላፊ የሆኑት መላዕከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በግጭቱ ሁለት ወጣቶች በጥይት ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው በአካባቢው ባለ አንድ የታጠረ ቦታ ምክንያት መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት ነዋሪዎች ፖሊስ ለምን እርምጃውን በወድቅት ሌሊት መውሰድ እንደፈለገ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

መላዕከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ስለክስተቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ለመንፈሳዊ ክብረ በዐል ዝግጅት እየተደረገ፣ ኅብረተሰቡ ፀሎት እያደረገ እያለ ነው በአሳቻ ሰዓት ላይ ከሌሊቱ ስድስት ተኩል ጀምሮ ፖሊስ እርምጃ መውሰድ የጀመረው።"

የቦታውን ባለቤትነት በተመለከተ ከአስር ዓመት በፊት ጥያቄ ቀርቦበት በጊዜው በመንግሥት ባለስልጣናት መቀያየር ምክንያት ምላሽ ሳያገኝ የቆዬ ሒደት እንዳለ ጠቅሰው "የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ይፋዊ ደብዳቤ ለወረዳው ፅፎ እየተከታተለ ነበር" ብለዋል።

መላዕከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ አክለውም በክስተቱ የሞቱ ወጣቶችን ቤተሰቦችን በማግኘት ማፅናናታቸውንና ጉዳት የደረሰባቸውንም ለማግኘት እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢቢሲ በትክክል የተፈጠረውን እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ለፌደራል ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ቢደውልም፤ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስን ማነጋገር እንዳለበት ተነግሮታል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ፋሲካ ለተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች እና የፅሁፍ መልዕክቶች ምላሽ አልሰጡም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ስልክም እንዲሁ ሳይመለስ ቀርቷል።

ሌሊት ምንድን ነው የተከሰተው?

ማክሰኞ ሌሊት ተኩስን ያስተናገደው ሃያ ሁለት በተለምዶ ቀበሌ 24 አካባቢ ረቡዕ ማለዳ የፀጥታ ኃይሎች ተበራክተውበት ተስተውሏል።

ለወትሮው ገና በማለዳው ደጆቻቸውን ከፍተው፣ ሞቅ ባሉ ሙዚቃዎች የደንበኞችን ቀልብ ለመግዛት የሚሞክሩ እና ከጎላጉል ሕንፃ አንስተው በግንባታ ላይ እስካለው አደይ አበባ ስታዲዬም ድረስ የተሰደሩ የንግድ መደብሮች፣ የአልባሳት መሸጫዎች እና አገልግሎት አቅራቢዎች በሮቻቸውን ዘጋግተዋል።

ባንኮች እና አንዳንድ ሆቴሎች ብቻ የተለመደ ሥራቸውን ይከውናሉ።

ከየሱቆቹ እና የአልባሳት መደበሮች የተዘጉ በሮች ጎን በርካታ ሰዎች በቡድን በቡድን ሰብሰብ ብለው ምሽቱን ሲከናወን ስላደረው ክስተት ይወያያሉ።

ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ ወደ ሃያ የሚጠጉ አድማ በታኝ ፖሊሶች ይገኛሉ።

በአካባቢው የተሰማሩ እና የአዲስ አበባ ፖሊስን የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ቁጥር ግን ከዚህም ይልቃል።

በስፍራው የተገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ የግጭት መንስዔ ሆኗል ወደተባለለት ከሆስፒታሉ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ገባ ብሎ ወደሚገኘው የታጠረ ቦታ መጠጋትም ሆነ ፎቶ ማነሳት እንደማይፈቀድለት በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ተነግሮታል።

ነገር ግን በታጠረው ቦታ ውስጥ ፍርስራሽ እንጨቶችን እና ሰማያዊ የድንኳን ጨርቅን ከርቀት መመልከት ችሏል።

ከቦታው ብዙም ሳይርቅ በሚገኝ የመጠጥ መደብር የምትሰራ ወጣት ለቢቢሲ እንደገለፀችው ተኩስ መሰማት የጀመረው እኩለ ሌሊት ገደማ ሲሆን፣ ተኩሱም ዘለግ ላለ ሰዓት የቀጠለ እና እርሷ እንደምትለው በግርግር ድምፅ የታጀበ ነበር።

"ጦርነት የተነሳ ወይም መንግሥት የወደቀ መስሎኝ ነበር እኔማ" ትላለች ወጣቷ በወቅቱ የነበራትን ስሜት ለቢቢሲ ስትገለፅ።

ከፀጥታ ኃይሎች በጥቂት ርቀት ወጣቶች በአጀብ በአጀብ ቆመው የሚሆነውን ይከታተላሉ።

ከመካከላቸው አንደኛው በስፍራው አዲስ የፈለቀ ፀበል መኖሩን እና እርሱን ተከትሎም ቤተ ክርስትያን ይሰራል ሲባል እንደሰማ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ ማክሰኞ ሌሊት እርሱ ቦታው የተያዘው እና የታጠረው በሕገ ወጥ መልኩ ነው ያሉ የፀጥታ አካላት መጥተው ማፋረስ ሲጀምሩ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መጋጨታቸውን ተራግሯል።