ትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች የሚፈልጉትን ገንዘብ ለማውጣት ተቸገርን አሉ

ትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ገንዘብ ማውጣት አለመቻላቸው ተናገሩ።
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ደንበኞች ገንዘብ ማውጣት አለመቻላቸውን ለቢቢሲ ገለጸዋል።
በአብዛኞቹ የኢዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከአንድ ሺህና ከሁለት ሺህ ብር በላይ ማውጣት እንደማይችሉ ተነግሮናል ይላሉ።
ለምሳሌ በዓድዋ ከተማ ሰሎዳ ዓዲኣቡን በተባለው ቅርንጫፍ ብር ለማውጣት የሄደችው ተጠቃሚ ወጣት፤ "ከሁለት ሺህ ብር በላይ ማውጣት አትችይም" መባሏን ለቢቢሲ ትናገራለች።
በዚህ ከተማ የሚገኙ ሌሎች ቅርንጫፎች ደግሞ ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሲሰጥ እንደዋለ ከዚያ በላይ ግን ብር የለም በማለት አልስጥም መባላቸውን ተገልጋዮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በውቅሮ ክልተውላዕሎ የሚገኘው ቅርንጫፍ ከአንድ ሺህ ብር በላይ አልሰጥም ማለቱን የባንኩ ደንበኞ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አምስት ሺህ ለማውጣት ወደ ቅርንጫፉ ሂዳ፤ አንድ ሺህ ብር ብቻ የተሰጣት አንድ ነዋሪም በተመሳሳይ የገጠማትን ተናግራለች።
ከዚህ መጠን በላይ ማውጣት አትችሉም ተብለው የተከለከሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ተጨንቀው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
እንዲሁም ደግሞ ደመወዛቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚከፈላቸው የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛ በተመሳሳይ "ብር የለም ጠብቁ" መባላቸውን ምንጮች ይናገራሉ።
በመቀለ የሚገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር ተዘዋወሮ እንተመለከተው፤ በመቀለ የሚገኙ ቅርንጫፎችም በወረፋ መጨናነቃቸውንና የጠየቁት ብር ሳይሰጣቸው ስለቀረ ሲበሳጩና በቁጣ ሲናገሩ ታዝቧል።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው አንድ በመቀለ ቅርንጫፍ በኃላፊነት ላይ የሚገኝ የባንኩ ሠራተኛ፤ ባንኩ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው ይናገራል።
በተለይ በትግራይ የሚገኙ ቅርንጫፎች ምንም ብር እንደሌላቸው ተናግሯል። ለዚህ እንደምክንያት የተጠቀሰውም የተለያዩ ሰዎች ገንዘባቸው ከባንኩ እያወጡ እንደሆነ ነው።
ችግሩ በሌሎች አከባቢዎችና በሌሎች የግል ባንኮችም፤ ሊከሰት እንደሚችል አመላክቷል።
የባንኩ ሠራተኛ አክሎም በትግራይ ውስጥ፤ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው አራት ዋና ዋና አከፋፈይ ማዕከላት በመቀለ፣ በማይጨው፣ በዓድዋና ሽረ እንዳሥላሰ የሚገኙ ሲሆን፤ በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ የብር እጥረት ስለአጋጠመ ነው ወደ ቅርንጫፎች ብር ያልተላከው ይላል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ይኸው ኃላፊ እንጋለው ብሔራዊ ባንክ ችግሩን በጥቂት ቀናት ለመፍታት እየሰራ እንደሆነ አክሎ ተናግሯል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አልሰን አሰፋ ግን የገንዘብ ዕጥረት እንደሌለ ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዕጥረት አልገጠመውም። ምናልባች የኔትወርክ ችግር ቢኖርበት ነው" በማለት የተባለው ውሸት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ጨምረውም "ከ2 ሺህ ብር በላይ አታወጡም የሚል ህግም የለም" የሚሉት አቶ አልሰን፤ ያለው ችግር ከቴሌ ጋር የሚያያዝ እንደሆነም ይናገራሉ።
ገንዘብ የማውጣት ገደቡንም በተመለከተ "ይሄ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። የባንኩ አሰራርም አይደለም" ብለዋል።
"ማንኛውም ሰው በባንኩ ያስቀመጠውን ብር በየትኛውም ቅርንጫፍ የማውጣት መብት አለው። ይህንን መብቱ የመከልከል መብት የለንም። የተባለው ችግር በትግራይ ካለ ለምን የእዚያ አከባቢ ቅርንጫፍ ኃላፊዎች አላነሱልንም? እንደሱ የሚባል መረጃ አልደረሰንም" ብለዋል።












