ኮሮናቫይረስ: ታይዋን ከአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ወሳኝ ጉባኤ ለምን ተገለለች?

ቤዝ ቦል የሚጫወት ህፃን

የፎቶው ባለመብት, Gene Wang/Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ካጠላበት ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም ላይ ያሉ የጤና ኃላፊዎች በሚቀጥለው ሳምንት ወሳኝ በተባለው የአለም ጤና ጉባኤ አለምን ከቀውሱ እንዴት እንታደጋት? በሚል ይመክራሉ። ጉባኤውን ያዘጋጀው የአለም ጤና ድርጅት ሲሆን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚካሄድ ይሆናል።

በአለም ላይ የወረርሽኙን አካሄድ በመቀልበስ፣ ቫይረሱን በመግታት ከፍተኛ እመርታ አሳይታለች የምትባለው ታይዋን ግን በዚህ በርካታ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል በተባለው ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ በአለም ጤና ድርጅት አልተጋበዘችም።

ሃያ ሶሰት ሚሊዮን ህዝብ ባላት ታይዋን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 440 ሲሆን፤ ሰባት ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል። ታይዋን የቫይረሱን መዛመትም ለመግታት ቀድማ ድንበሯ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን፣ የውጭ ሃገራት ዜጎች ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ መከልከል እንዲሁም ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ዜጎቿ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ አድርጋለች።

ታይዋን የወረርሽኙን መዛመት በፍጥነትና ውጤታማ በሆነው አካሄዷ አለም አቀፉን ውደሳ ማግኘቷን ተከትሎ ለአለም ሃገራትም ልምዷን ማካፈል አለባት የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ሆኖም ቻይና የግዛቴ አካል ናት ብላ የምትከራከርላትን ታይዋን ከጎርጎሳውያኑ 2016 ጀምሮ የአለም አቀፉ ድርጅት ስብሰባዎች ላይ እንዳትሳተፍ እግድ ጥላለች።

በባለፉት ሳምንታት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ጃፓንና የተለያያዩ ሃገራት ታይዋን ቢያንስ እንደ ታዛቢ ትሳተፍ በሚልም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉላት ነው።

የቫይረሱ መነሻ ናት የምትባለው ቻይና የወረርሽኙን ሁኔታ ባግባቡ ለአለም አላሳወቀችም እንዲሁም መረጃዎችን ደብቃለች በሚል በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ትችት እየደረሰባት ያለችው ቻይና ግን ታይዋን ትሳተፍ የሚለውን አካሄድ በከፍተኛ ሁኔታ ተችታዋለች።

ከዚህ ቀደም ከታይዋን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን የሃገር ውስጥ ጣልቃ ገብነት የምትለው ቻይና በቅርቡ ግን ታይዋን የአለም አቀፉ ጤንነት ድርጅት ትሳተፍ የሚለው የመገንጠልና የነፃነት ጥያቄ ላይ ያነጠጣረ ነው በማለት ተችታለች።

የሃገሪቱ ሚዲያ ዢኑዋም አሜሪካን ወርፎ አንድ ፅሁፍ አትሟል።

"በአለም ላይ ያለችው አንድ ቻይና ናት። የቻይናን ሪፐብሊክም ሆነ ግዛቶቿን የሚያስተዳድረው አንድ የቻይና ህጋዊ መንግሥት ነው። ታይዋን ደግም የቻይና አካል ናት" ያለው ፅሁፉ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለወረርሽኙ እየሰጠ ያለውን ምላሽ አሜሪካዊ ፖለቲካዊ ማድረጓን ታቁም ብሏል።

የታይዋን ግዛት ይገባኛል ቅራኔዎች ረዥም ዘመናትን እንዳስቆጠረ በዴቪድሰን ኮሌጅ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰሯ ሼሊ ሪገርስ ይናገራሉ።

በጎርጎሳውያኑ 1949 ቻይናን በወቅቱ ያስተዳድር የነበረው መንግሥት በኮሚዩኒስት ፓርቲ መወገዱን ተከትሎ ታይዋን ራሷን እያስተዳደረች ትገኛለች።

ይህ ሁኔታ ለቻይና ያልተዋጠላት ሲሆን፤ የታይዋን ህጋዊ መንግሥት በቻይና መንግሥት መጠቃለል አለበት ከማለት አልፋ፤ ግዛቷ በማንኛውም መንገድ በቻይና ስር እንደምትሆንና ፤ ሃይልን በመጠቀም ሊሆን እንደሚችልም ገልፃለች።

በአሁኑ ሰአት ታይዋንን እያስተዳደረ ያለው የፕሬዚዳንቷ ትሳይ ኢንግ ዌን ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ መንግሥት የግዛቷን ነፃነትን የሚደግፍ ሲሆን ከቻይና ጋር ያለውንም ግንኙነት የበለጠ አሻክሮታል።

ፕሬዚዳንቷ ትሳይ ኢንግ ዌን ቻይና በታይዋን ላይ አለኝ የምትለውንም የሉዓላዊነት ጥያቄ በጭራሽ አይቀበሉትም።

ታይዋን የራሷ የሆነ ሰራዊት እንዲሁም የመገበያያ ገንዘብ ያላት ሲሆን በአንዳንድ መንግሥታትም እንደ 'ዲፋክቶ' ሃገርም ትታያለች።

ግሎባል ታይምስ ባሳተመው ርዕሰ አንቀፅ ቻይና በታይዋን ላይ ሃይልን ልትጠቀም እንደምትችል አመላክቷል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ከመከሰቱ በፊት ታይዋንና ቻይናን በሚከፍለው የታይዋን ስርጥ በርካታ ጦር ማስፈሯ ተነግሯል።

በባለፉት ሶስት ወራትም እንዲሁ የጦር አውሮፕላኖችና ጄቶች በአካባቢው ሲያንዣብቡ እንደነበርም ተገልጿል።

ቻይና በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ታይዋንን ይደግፋሉ የምትላቸውን ሃገራትም ኢኮኖሚያዊ ማስፈራሪያዎች ታደርጋለችም ይባላል።

ታይዋን የአለም አቀፉን የጤና ጉባኤ እንድትሳተፍ ኒውዚላንድ ድጋፍ መስጠቷን ተከትሎ ቻይና የሁለቱን ሃገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያበላሽ ነው ብላለች።

የታይዋን ፕሬዚዳንት ትሳይ ኢንግ ዌን

የፎቶው ባለመብት, Carl Court/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታይዋን ፕሬዚዳንት ትሳይ ኢንግ ዌን

በቻይና ግፊት ምክንያት አስራ አምስት ሃገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያቋረጡ ሲሆን ታይዋን በበኩሏ የአለም አቀፉ ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች እውቅና እንድታገኝ እየሰራች ነው።

በአለም አቀፉ ማህበረሰብም ዘንድ የሃገርነት እውቅናም ማግኘትም ዋና አላማዋ ነው።

የተለያዩ ሃገራት ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ላለማበላሸት የታይዋንን ጉዳይ ወደ ጎን ገፋ አድርገውት ነበር። ሆኖም በአለም አቀፉ ጤና ድርጅት 'የቻይናዋ ታይፔይ' በሚል የታዛቢ ቦታ ነበራት። ነገር ግን በጎርጎሳውያኑ 2017 የፕሬዚዳንት ትሳይ ኢንግ ዌን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ እንዳትሳተፍ ተደርጋለች።

ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ታይዋን እንድትካተም ከፍተኛ ግፊት እያደረገች ነው። ሆኖም በዚህ አመት በርካታ ሃገራት እንድትሳተፍ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም ቻይናን ማስቀየም የማይፈልጉ ሃገራትም ለታይዋን ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን ይህም የሆነው በኮቪድ- 19 ምክንያት ነው ተብሏል።

የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ታይዋንን መጋበዝ ይችላል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችም በመነሳት ላይ ናቸው። ድርጅቱ የታይዋን አባልነትም ሆነ ተሳትፎ የሚወሰነው በአባላት ሃገራቱ እንደሆነ አሳውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የታይዋንን የጤና ሃላፊዎችም ጋር መነጋገሩንም አሳውቋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ በበኩላቸው የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ታይዋንን የመጋበዝ ስልጣን አላቸው ቢሉም፤ የድርጅቱ የህግ ቢሮ ኃላፊ ስቴቨን ሰለሞን በበኩላቸው ዳይሬክተር ጄኔራሉ መጋበዝ የሚችሉት አባላቱ ድጋፍ ሲያሳዩ ነው ብለዋል። እስካሁንም ባለው የአባላት ሃገራቱ ድጋፍ ላይ ግልፅ የሆነ ነገር የለምም ብለዋል።

ሆኖም ፕሮፌሰር ሼሊ ሪገርስ ከዚህ ቀደም ታይዋን ትሳተፍ እንደነበር ጠቅሰው እንዲሁም የሃገርነት እውቅና ያላገኙ ፍልስጥኤምና ቫቲካንም በታዛቢነት ይሳተፋሉ ብለዋል።

ታይዋን የተገለለችበት መንገድ ምከንያት አለው የሚሉት ፕሮፌሰሯ የታይዋን ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ሌሎች ሃገራት ከቻይና ጋር የሚያደርጉትን የውክልና ፍልሚያ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

ኮሮና
Banner