አውሮፓ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሰጋታል?

በጣልያን ጭምብል ያጠለቁ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አውሮፓ ሁለተኛ ዙር የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚያሰጋት ተናግረው ነበር። ነገር ግን ለዚህ ግምት ማስረጃ ሊሆን የሚችል ነገር አለ?

ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ተከሰተ ማለት ደግሞ እንደገና በርካቶች ሃዘናቸው ሲመለስ፣ ሲሞቱ ልንመለከት ነው ማለት ነው።

ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ተከስቶ የነበረው 'ስፓኒሽ ፍሉ' ያጋጠመው ይሄ ነበር። በሁለተኛ ዙር የጀመረው በሽታው ግን ከመጀመሪያው ይበልጥ ከባድና ገዳይ ነበር።

በዓለም ጤና ድርጅት የሚሰሩት ማርጋሬት ሃሪስ ግልጽ ለማድረግ እንደሞከሩት የመጀመሪያው ዙር ወረርሽኝ በራሱ ገና በመላው ዓለም እየተሰራጨ ነው የሚገኘው።

እንደ ደቡብ ኮሪያ እና ሲንጋፖር ያሉ አገራት ገና ከጅምሩ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን በመውሰድና ንክኪ ያላቸው ሰዎችን በቶሎ በማግኘት የቫይረሱን ስርጭት ከሌሎች አገራት በተሻለ መቆጣጠር ችለዋል።

ነገር ግን እንደ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ጣልያን ያሉት አገራት ደግሞ እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ መገደብ ላይ በማተኮር ሰርተዋል። ይህን ያደረጉበት ምክንያት ደግሞ ረቀቅ ያለ ተላላፊ በሽታዎችን መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል የጤና ስርአት ስላልነበራቸው ነው።

ምንም እንኳን ትንሽ ዘግየት ያለ ቢመስልም እነዚህም አገራት ቫይረሱን በመቆጣጠር ረገድ በርካታ እምርታዎችን አስመዝግበዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ወረርሽኙ በድጋሚ የመከሰት ምልክቶችን እያሳየ ነው፤ በተለይ ደግሞ ስፔን ውስጥ።

በኖርዊች ሜዲካል ትምህርት ቤት መምህርና የኮቪድ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ሀንተር እንደሚሉት ወረርሽኙ ሁለተኛ ዙር ላይ አልደረሰም። አሁን እየሆነ ያለውን እንዴት እናስረዳው? ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰሩ '' ከመዘናጋት ጋር አብሮ የሚመጣ የስርጭት መጠን መጨመር እንጂ ሁለተኛ ዙር አይደለም'' ብለዋል።

ይህንን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በዋነኛነት ቫይረሱ ያለባቸውን በምርመራ ማግኘትና ንክኪዎችን መለየት፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና የግልልና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ወሳኝ ናቸው።

ስለዚህ መንግሥታትና ዜጎች እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ላይ ሲዘናጉ ነው ቁጥሩ የሚጨምረው እንጂ ሁለተኛው ዙር መጥቶ አይደለም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

አክለውም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ገና ከዚህም በላይ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል ይላሉ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰት ችግር ሳይሆን ትልቅ ‘ማእበል’ መሆኑን አስጠንቅቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ወረርሽኙ እንደ ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ ወቅትን ጠብቆ የመጥፋት እና የመመለስ ባሕርይ ስለሌለው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቋል።

በተለይም ደግሞ በፈረንጆቹ የበጋ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና መዘናጋቶች አሳሳቢ መሆናቸውንና ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ድርጅቱ አስታውቋል።

ኮሮና