ሥራ ያጣው የጃፓን አየር መንገድ በአውሮፕላኑን ውስጥ ምግብ መሸጥ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, ANA
የጃፓን ትልቁ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተቀዛቀዘው የአየር ትራንስፖርት ምክንያት ሥራ አጥተው በቆሙት አውሮፕላኖቹ ውስጥ የምግብ ቤት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ለዚህ የመጀመሪያ ደረጃ በተባለለት የአውሮፕላን ውስጥ የምግብ አገልግሎት ለአንድ ጊዜ መስተንግዶ አንድ ሰው 540 ዶላር ወይም ከ22 ሺህ ብር በላይ መክፈል ይጠበቅበታል።
ይህ ኦል ኒፖን ኤርዌይስ በተባለው አየር መንገድ በቆሙ አውሮፕላኖቹ ውስጥ ምግብ የመሸጥ ሥራ የተጀመረው ትናንት ረቡዕ ሲሆን ቦታ ለመያዝ ትኬቶች በፍጥነት ተሽጠው ያለቁ በመሆናቸው ተጨማሪ ቦታዎችን እያዘጋጀ ነው።
አየር መንገዱ ይህንን ሃሳብ ያመጣው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አየር መንገዶች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ አጥተው የቆሙ አውሮፕላኖቻቸውን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያሰቡ ባለበት ጊዜ ነው።
በርካታ አየር መንዶች የመንገደኞች አውሮፕላኖቻቸውን ወደ ጭነት ማመላለሻነት በመቀየር ከዚህ በፊት አጋጥሞ የማያውቀውን አስቸጋሪውን የአየር ትራንስፖርቱን ዘርፍ ፈተና ለማለፍ እየጣሩ ነው።
ሌሎች ደግሞ አዳዲስ አገልግሎቶችንና ፈጠራዎችን በመጠቀም የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ ለመቆየት ጥረት እያደረጉ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር የሴንጋፖር አየር መንገድ በአገሪቱ ዋነኛ አየር ማረፊያ ውስጥ ቆሞ በሚገኘው ግዙፉ ኤርባስ ኤ380 አውሮፕላን ውስጥ ሰዎች ከፍለው እንዲመገቡ አድርጎ ነበር።
ለዚህም የተጠየቀው ክፍያ በጣም ውድ የነበረ ቢሆንም ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የተዘጋጁት ትኬቶች በሙሉ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ተሽጠው አልቀው ነበር።
የጃፓኑ ግዙፍ አየር መንገድም አሁን የጀመረው በአውሮፕላን ውስጥ የመመገብ አገልግሎት በዋና ከተማዋ ቶኪዮ ባለው ሃኔዳ አየር ማረፊያ ውስጥ ቆሞ በሚገኝ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ነው።
ይህ "ባለክንፉ ምግብ ቤት" የተባለው የአየር መንገዱ ሃሳብ የመነጨው ከአየር መንገዱ ሠራተኞች ሲሆን አገልግሎቱም እንደ አውሮፕላን ጉዞ በሁለት የተከፈለ ነው። የአንደኛው እጅግ ውድ የሆነው የመጀመሪያ ደረጃ አገልግሎት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በግማሽ የሚረክሰው የምግብ አገልግሎት ነው።
ባለፈው ሳምንት የብሪቲሽ ኤርዌይስም ምግብ ከሚያቀርብለት ኩባንያ ጋር በመተባበር ለተጠቃሚዎች የሚቀርብ የምግብ ዝርዝርን ይፋ አድርጓል። ነገር ግን ምግቡ አውሮፕላን ውስጥ ሚበላ ሳይሆን ተመጋቢዎች በምርጫቸው መሰረት ቤታቸው ድረስ የሚቀርብ ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባለፈው ዓመት ከተከሰተ በኋላ የዓለም አገራት የአየር ትራንስፖርት ላይ ለወራት በጣሉት እገዳ ምክንያት በርካታ አየር መንገዶች ከባድ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።
በዚህም ምክንያት ለኪሳራ የተዳረጉ አየር መንገዶች የሠራተኞቻቸው ክፍያ ከመቀነስ ጀምሮ በርካታ ሠራተኞችን እስከማሰናበት የደረሰ እርምጃ ለመውሰድ ተገድደዋል።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር እንዳለው የፈረንጆቹ 2020 በዘርፉ ታሪክ ውስጥ ከባድ ቀውስ የተከሰተበት እንደነበርና ተጽዕኖውም ለቀጣይ ዓመታት እንደሚቀጥ ተገምቷል።















