በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው፤ 780 ደርሷል

ጭምብል ያጠለቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር በጎርጎሳውያኑ 2003 ከተነሳው ሳርስ ወረርሽኝ ከቀጠፈው ህይወት እንደበለጠ ተገልጿል።

የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ሁቤ ግዛት የሟቾች ቁጥር 780 እንደደረሰና፤ በትናንትናው ዕለትም በግዛቷ 81 ሰዎችም እንደሞቱ የጤና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ በአጠቃላይ በቻይና የሟቾች ቁጥር 803 የደረሰ ሲሆን ከቻይና ውጭ ባለው ሁለት ሰዎች ሞተዋል።

እነዚህ ሟቾች አንደኛው በሆንግኮንግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በፊሊፒንስ ነው።

በጎርጎሳውያኑ የተከሰተው የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃው ሳርስ 774 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፤ እነዚህም በሃያ ሃገራት ነው ተብሏል።

እስካሁን ባለው መረጃ 34 ሺ 800 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ በቻይና ነው።

ከሳምንት በፊት አለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን የአለም የጤና ስጋት ነው ብሎታል።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በሁቤዋ ግዛት ውሃን ሲሆን ለሳምንታትም የጉዞ፣ የመውጣትና የመግባት እግድ ተጥሎባታል።

ሆንግ በበኩሏ ከቻይና የሚመጣ ማንኛውንም መንገደኛ ለሁለት ሳምንት ያህል ተለይተው እንዲቆዩ አዛለች።

ጎብኝዎች በሚያርፉበት ሆቴልም ሆነ የመንግሥት ማዕከላት ተለይተው እንዲቆዩ እንዲሁም ነዋሪዎቿም ቢሆን ለሁለት ሳምንት ያህል ከምንም አይነት ግንኙነት ርቀው ቤታቸው እንዲቀመጡ ትእዛዝ አስተላለፋለች።

ይህንን ተላልፎ የሚገኝ ሰው የገንዘብ እንዲሁም የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል።

በሆንግ ኮንግ በቫይረሱ የተጠቁ 26 ሰዎች ተገኝተዋል።

ዶ/ር ሊል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከዚህም በተጨማሪ ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀስ ሲያስጠነቅቅ የነበረው ዶክተር ሊል ዌንሊያንግ መሞት በብዙዎች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

በውሃን ህመምተኞችን እያከመ በነበረበት ወቅት ነው በቫይረሱ የተያዘው።