29 የኮሮናቫይረስ ጥቆማዎች እንደደረሱት ጤና ጥበቃ አስታወቀ

ኮሮና ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ይፋ ከሆነ በኋላ በሽታውን በተመለከተ 29 ጥቆማዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታውን ክስተት በተመለከተ ክትትል ለሚያደርገው አካል እንደደረሱ ተገለጸ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ጥቆማዎቹ በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ ለሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰው ክትትልና ማጣራት ተደርጎባቸዋል።

በዚህም መሰረት በ29ኙ ጥቆማዎች ላይ በተደረገው ማጣራት፤ 14ቱ በበሽታው የሚያስጠረጥሩ ምልክቶች አሳይተው ስለነበረ በሽታው መያዝ አለመያዛቸው እስኪታወቅ ድረስ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ መደረጋቸው ተገልጿል።

ከተጠረጠሩት አስራ አንድ ሰዎች የተወሰዱ ናሙናዎችም ለምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውንና ስምንቱ ከቫይረሱ ነፃ እንደሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ የሦስቱ ውጤትም ከደቡብ አፍሪካ እየተጠበቀ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በቀጣዮቹ ቀናት በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ የሦስት ሰዎች ናሙናዎች ለምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚላኩም መግለጫው አመልክቷል።

በተጨማሪም የበሽታው መነሻ እንደሆነች ከሚነገርላት የቻይና ዉሃን ከተማ የሚመጡ ሁሉም መንገደኞች አስፈላጊ የህክምና ክትትል ወደ ሚደረግበት ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ መወሰኑም ተገልጿል።

እንዲሁም ከቻይና የሚመጡ ሰዎች በሙሉ ከሌሎች መንገደኞች ጋር ሳይቀላቀሉ ተገቢውን ስልጠና ባገኙ ባለሙያዎች አማካይነት አስፈላጊው የሙቀት ምርመራ ቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ እንዲደረግላቸውና የኢሚግሬሽን አገልግሎት የሚሰጥ ልዩ መስኮት እንደተዘጋጀላቸውም ተጠቅሷል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ስምንት ሰዎች መገኘታቸው ተገልጾ የነበረ ሲሆን በተደረገላቸው ምርመራም ከበሽታው ነጻ መሆናቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።