ዊሊያም ሩቶ አምስተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ

ሳሙኤል ሩቶ 5ኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሳሙኤል ሩቶ

በኬንያ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ አምስተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ፈጸሙ።

የ55 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ 60 ሺህ ሕዝብ በታደመበት የካሳራኒ ስታዲየም ውስጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በፈጸሙት ቃለ መሐላ፣ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ለማክበርና ለማስከበር ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጤቱ የጸደቀውን ምርጫ ያሸነፉት 50.5 በመቶ ድምጽ አግኝተው ሲሆን፣ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ የ48.8 በመቶውን የመራጭ ድጋፍ አግኝተዋል።

መጭበርበሮች ነበሩበት በሚል ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የሄደው ይህ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ምርጫን የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጻና ፍትሐዊ ነው ሲል ባለፈው ሳምንት ውጤቱን አጽንቶታል።

ተሸናፊው ዕጩ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ገልጸው ነበር። በዚህም ምክንያት ግብዣው ቢደርሳቸውም በዛሬው ሲመተ በዓል ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

ለሁለት የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ኬንያን በፕሬዝዳንትነት የመሩት እና የራይና ኦዲንጋ ደጋፊ የነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ በሲመተ በዓሉ ላይ ከባለቤታቸው ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈው በዓለ ሲመት ላይ ታድመዋል።

ኬንያ እንደ አውሮፓዊያኑ 1963 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ወዲህ አራት ፕሬዝዳንቶች መርተዋታል።

ከእነዚህ መካከል አባትና ልጅ ይገኙበታል።

የመጀመርያው የኬንያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ ሲሆኑ ልጃቸው ተሰናባቹና 4ኛው ፕሬዝዳንት ደግሞ ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው።

ሟቾቹ ዳንኤል አራፕ ሞይ እና ኪባኪም ኬንያን ዘለግ ላለ ጊዜ መርተዋል።

ዊሊያም ሩቶ ባለፈው ወር የተደረገውን አገራዊ ምርጫ ያሸነፉት በጠባብ ውጤት ነበር።

ተቃናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ውጤቱን አልቀበልም ብለው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤት ማለታቸው አይዘነጋም።

ሆኖም ፍርድ ቤት የዊሊያም ሩቶን ድል አጽንቶታል።

ይህን ተከትሎ ራይላ ኦዲንጋ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብለዋል።

ሆኖም በዛሬው የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት አልገኝም ብለዋል።

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተሸናፊውን ፕሬዝዳንት ራይላ ኦዲንጋን እስከ መጨረሻው ሲደግፉ ነበር።

እስከ ትናንት ድረስም ለአሸናፊው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ሳያስተላልፉ ቆይተዋል።

ትናንት በመጨረሻ ቤተ መንግሥት ጠርተው ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ቤተ መንግሥቱንም በማስጎብኘት ርክክብ አድርገዋል።

ዛሬ ቃለ መሐላ የፈጽሙት ሩቶ ላለፉት 10 ዓመታት የኡሁሩ ኬንያታ ምክትል ሆነው ሠርተዋል።

ሆኖም በእርሳቸውና በኡሁሩ መካከል ቅራኔ ገብቶ ቆይቷል።

ዊሊያም ሩቶ ከሥልጣን በኋላ አገሪቱ ከተዘፈቀችበት ክምር ዕዳ የምትወጣበትን መንገድ ይፈልጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት በዚህ ሰዓት (ማክሰኞ ማለዳ) በናይሮቢ የካሳራኒ ስታዲየም የሩቶን ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ለመታደም 60ሺህ ሰዎች ተገኝቷል።

ኬንያ ባልተለመደ ሁኔታ ከነውጥ የራቀና የተሳካለት ምርጫ በማድረግ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሞካሽታለች።