የአውሮፓ ኅብረት በእስራኤሉ ቀኝ ዘመም ሚኒስትር ምክንያት መሰናዶውን ሰረዘ

ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ሚኒስትር ኢታማር ቤንጊር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ሚኒስትር ኢታማር ቤንጊር

የአውሮፓ ኅብረት የአውሮፓ ቀንን በማስመልከት በእስራኤል ሊያካሂድ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ መሰናዶ ሰረዘ።

መሰናዶው የተሰረዘው ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ሚኒስትር ኢታማር ቤንጊር መሰናዶውን ሊታደሙ አቅደው ስለነበረ ነው።

አዘጋጆቹ እንዳሉት አቋሙ ከመርሀቸው ጋር ለሚጻረር ሰው “መድረክ መስጠት” አይፈልጉም።

የእስራኤል መንግሥት ወኪል እንደመሆናቸው መሰናዶው ላይ ንገግር እንደሚያደርጉ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።

የአውሮፓ ኅብረት መሰናዶውን መሰረዙ “ዲፕሎማሲያዊ ያልሆነ እርምጃ” ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ነቅፈዋል።

የእስራኤል መንግሥት ይፋዊ የዲፕሎማሲ መሰናዶዎችን የሚታደሙ ሚኒስትሮች የሚልከው በተራ በተራ ነው። የአውሮፓ አምባሳደሮች እኚህ ሚኒስትር ወደ መሰናዶው እንደሚላኩ ሲሰሙ ተደንቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ቀኝ ዘመም ሚኒስትሮች እንዳላኩ ቢፈልጉም ቀኝ ዘመሙ ሚኒስትር መሰናዶውን ለመታደም ተመርጠዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ንግግር ቢያደርጉ ኖሮ “ከጂሀድና ሽብርተኛነት” ጋር ለሚደረገው “ትግል” ትብብር እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች “የእስራኤል መከላከያ ኃይልን፣ ወታደሮችን እና የእስራኤል ዜጎችን የሚጎዳ እንቅስቃሴን መደገፍ የለባቸውም” ለማለት አቅደው ነበር።

ብዙ የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች በመሰናዶው አንገኝም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእስራኤል የአውሮፓ ኅብረት አገራት አምባሳደሮች ስብሰባ ካካሄዱ በኋላ መሰናዶውን ለመሰረዝ ተወስኗል።

ውሳኔውን የተቃወሙት ወግ አጥባቂዎቹ የእስራኤል ደጋፊዎች ሀንጋሪ እና ፖላንድ እንደሆኑ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ለአውሮፓ ቀን መታሰቢያ ያዘጋጀው የቴል አቪቭ የአደባባይ ባህላዊ ሕዝብ መሰናዶ እንደታቀደው እንደሚካሄድ አስታውቋል።

“ጠንካራና ገንቢ ወዳጅነታችንን በማስመልከት በእስራኤል ከአጋሮቻችን ጋር ቀኑን እናከብራለን” ብሏል።

ቀኝ ዘመሙ ሚኒሰትር የአውሮፓ ኅብረት መሰናዶውን መሰረዙን ተችተዋል።

“አሳፋሪ ነው። ዴሞክራሲና የባህል ልዩነትን አከብራለሁ የሚል አካል ዲፕሎማሲያዊ ያልሆነ አፈና ሲያካሂድ ያሳፍራል” ብለዋል።

“የእስራኤልን መንግሥት፣ ጀግኖች ወታደሮችን እና ሕዝቡን በማንኛውም ጉባዔ መወከል ኩራቴ ነው” ሲሉም አክለዋል።

እስራኤል ቀኝ ዘመም የመንግሥት ኃላፊዎችን ከሾመች በኋላ የእስራኤል ወዳጅ የሆኑ አውሮፓ አገራት ተወካዮች ቀኝ ዘመሙ ኢታማር ቤንጊር እንዲሁም ቀኝ ዘመሙ የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሊል ስሞትሪች ጋር ለመገናኘት አልፈቀዱም።

እስራኤል ባለፈው ሳምንት በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ለፍልስጤማውያን የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤተልሔም አቅራቢያ የተሠራ ትምህርት ቤትን ማፍረሷ ቁጣ ቀስቅሷል።

እስራኤል ትምህርት ቤቱ ሕገ ወጥ ነው በሚል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈርስ አድርጋለች።

በፍልስጤም የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች በትዊተር ገጻቸው ድርሪቱ “አሳፋሪ” ነው ብሏል። ትምህርት ቤቱን ማፍረስ 60 ልጆችን ከመጉዳቱም በላይ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር ገልጿል።

እስራኤል በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ሕገ ወጥ ብላ የምታፈርሳቸው ሕንጻዎች፣ ፍልስጤማውያን ይፋዊ የግንባታ ፍቃድ ማግኘት ባይችሉም የሚገነቧቸው ናቸው።