ወንድሙ በአደንዛዥ ዕጽ የሞተበት ግለሰብ በይፋ ዕጽ ሲሸጥ በፖሊስ ተያዘ

ጄሪ ማርቲን አደንዛዥ ዕጽ መሸጫ ተንቀሳቃሽ ሱቀን የከፈተው ዕጽ ተጠቃሚዎች በሚያዘወትሩት ጎዳና ላይ ነበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄሪ ማርቲን አደንዛዥ ዕጽ መሸጫ ተንቀሳቃሽ ሱቀን የከፈተው ዕጽ ተጠቃሚዎች በሚያዘወትሩት ጎዳና ላይ ነበረ

ካናዳ ውስጥ ወንድሙ ከመጠን በላይ አደንዛዥ ዕጽ ወስዶ የሞተብት ግለሰብ ተንቀሳቃሽ የአደንዛዥ ዕጽ መሸጫ ሱቅ በመክፈት ዕጽ ሲሸጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።

የ51 ዓመቱ ጄሪ ማርቲን በተንቀሳቃሽ ሱቁ ኮኬይን፣ ሄሮይን እና ሌሎች አደንዛዥ ዕጾችን ለተጠቃሚዎች ለመሸጥ አቅዶ ነበር። ነገር ግን ፖሊስ ሕገወጥ ነው ሲል ከልክሎታል።

ግለሰቡ አደንዛዥ ዕጾቹን በይፋ ለመሸጥ የተነሳው ከሌሎች አደገኛ ንጥረ ነገሮች ጋር ተቀላቅለው በድብቅ የሚሸጡ ዕጾች የሚያስከትሉትን ሞት እና ከባድ ጉዳትን ለመከላከል ነው ብሏል።

ይህንን መከራከሪያውን ለፍርድ ቤት በማቅረብም ፖሊስ የወሰደበት እርምጃ እንዲቀለበስ አደርጋለሁ ብሏል።

የቫክኩቨር ፖሊስ ጄሪ ማርቲንን በቁጥጥር ስር ያዋለው “ሕገወጥ የዕጽ መሸጫን በመጠቀም አደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር” መሆኑን ቢገልጽም መደበኛ ክስ ግን አልመሰረተበትም።

ግለሰቡ በፖሊስ የተያዘው ተንቀሳቃሽ የዕጽ መሸጫ ሱቁን ከፍተኛ ዕጽ ተጠቃሚዎች ባለበት የቫንኩቨር አካባቢ ከከፈተ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የሱቁ ባለቤት ማርቲን ወንድሙ ከልክ በላይ አደንዛዥ ዕጽ ወስዶ ለህልፈት ተዳርጎበታል። ይህንንም ንግድ የጀመረው የካናዳ የጤና ባለሥልጣን ትንሽ መጠን ያለው ጠንካራ ዕጽ ይዞ መገኘትን ከፈቀደ ከወራት በኋላ ነው።

ይህ ውሳኔ የተሰጠው በምዕራባዊ የካናዳ ግዛት ውስጥ በድብቅ የሚዘዋወረው አደገኛ የሆነው ፌታኒል በተባለውን ዕጽ ከልክ በላይ በመጠቀም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ነው።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከ2,720 በላይ ሰዎች በካናዳዋ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ውስጥ ከልክ በላይ ዕጽ በመጠቀም ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፣ ይህም በአማካይ በየቀኑ ሰባት ሰዎች ይሞታሉ ማለት ነው።

የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት አደንዛዥ ዕጽን ከመጠን በላይ በመጠቀም በርካታ ሰዎች ከሚሞቱባቸው የካናዳ ግዛቶች መካከል ሁለተኛዋ ናት።

ጄሪ ማርቲንም በከፈተው ተንቀሳቃሽ ሱቅ አማካይነት ከልክ በላይ ዕጽ በመጠቀም የሚከሰተውን ሞት ለማስቀረት እስከ 2.5 ግራም የሚደርሱ የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾችን ለመሸጥ አቅዶ ነበር። በተጨማሪም የሚሸጣቸው ዕጾች አደገኛ ንጥረ ነገር ያልተጨመረባቸው ናቸው።

ምንም እንኳን መንግሥት የተወሰነ መጠን ያለው ዕጽ ዜጎች እንዲይዙ ቢፈቅድም፣ ለሕዝብ ጤናና ደኅንነት ሲባል ፖሊስ የዕጽ ዝውውርን የመቆጣጠር ሥራውን ይቀጥላል በማለት ገልጿል።

አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት በርካታ ሰዎች ዕጽ ለመግዛት በተንቀሳቃሽ የአደንዛዥ ዕጽ መሸጫው ሱቅ አካባቢ ተሰልፈው ነበር።

የሱቁ ባለቤት በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ፍርድ ቤት እስኪቀርብ ድረስ መለቀቁን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፣ ሱቁን ከፍቶ ከነበረበት አካባቢም ድርሽ እንዳይል ተነግሮታል።

በካናዳ ውስጥ ፌንታኒል የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ ከልክ በላይ በመጠቀም የሚደርሰው የሰዎች ሞት ከ2016 (እአአ) ጀምሮ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ150 በመቶ አሻቅቧል።