ሶሪያ ወደ አረብ ሊግ አባልነቷ እንድትመለስ ተፈቀደላት

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሶሪያ ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪው የአረብ አጋር የጋራ ማኅበር ወደ ሆነው አረብ ሊግ መልሳ እንድትቀላቀል ተፈቀደ።
ተቃዋሚዎች ላይ በደረሰው ጭቆና ምክንያት ከአሥር ዓመት በፊት ነበር ከሊጉ የተባረረችው።
ከተቃውሞው በኋላ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብታ ቆየረታለች።
ወደ ሊጉ መመለሷ ሶሪያ ከአረብ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ መሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል።
ሊጉ በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ጉባዔ የሚያካሂድ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድ በጉባዔው ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሶሪያ ወደ አረብ ሊግ መመለሷን ተችተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ሶሪያ ወደ ሊጉ ለመመለስ ብቁ ባትሆንም፣ አረብ ሊግ የሶሪያን ቀውስ ለመፍታት የሚያደርገውን የረዥም ጊዜ ጥረት አሜሪካ ትደግፋለች።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ አሕማድ በበኩላቸው “ዩኬ ከአሳድ አገዛዝ ጋር የሚደረግ ግንኙነትን በመቃወም ትቀጥላለች። አሳድ አሁንም ንጹህ ሶሪያውያንን እየገደለ፣ እያገተ እና እያሰቃየ ነው” ብለዋል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ የሊጉን ውሳኔ “ትልቅ ትኩረት” ሰጥቶ እንደሚመለከት ገልጾ “የአረብ አገራት ትብብርና ትስስር ያስፈልጋቸዋል” ብሏል።
ከአረብ ሊግ 22 አባል አገራት የ13ቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በካይሮ ባደረጉት ውይይት ተገኝተው ነው ውሳኔው የተላለፈው።
የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት መቆም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። የሶሪያ የስደተኞች ቀውስ እና ስውር ዝውውር እንዲገታም አሳስበዋል።
በሶሪያ የተባባሰው ድህነት እና ሥራ አጥነት ብዙዎች ወደ አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እንዲገቡ አድርጓል።
ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ እና ኢራቅ የሚገኙበት ኮሚቴ ሶሪያን ለማገዝ እንደሚቋቋም ተገልጿል።
የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አሕመድ አቡል ጊት ሶሪያን ወደ ሊጉ መልሶ የማስገባት ውሳኔ በሶሪያ ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።
ውሳኔው የሶሪያ እና አረብ አገራትን ግንኙነት በጥቅሉ የሚያስቀጥል እንዳልሆነና እያንዳንዱ አገር የራሱን እርምጃ መውሰድ እንደሚችል አክለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በሶሪያ ጦርነት ከ300,000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ100,000 በላይ ደግሞ ታግተዋል ወይም ያሉበት አይታወቅም።
ከ21 ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎች ግማሹ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በአማጽያን በተያዘችው ኢድሊብ ውስጥ የተፈናቀሉ ሶሪያውያን በሊጉ ውሳኔ መደናገጣቸውን ገልጸዋል።
አንድ ነዋሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል “የአረብ አገራት መሪዎች እኛን ከመርዳት እና እየተሰቃየን ካለንባቸው ካምፖች ከማስወጣት ይልቅ የወንጀለኞችን እጅ መጨበጥ መርጠዋል” ብለዋል።
አንድ ሌላ ነዋሪ ሊጉ “ትልቁን ዋጋ ይከፍላል” ብለዋል።
አሳድ በሩሲያ እርዳታ እአአ በ2015 አገሪቱን መልሰው መቆጣጠር ጀምረዋል።
የአረብ አገራት ከወራት በፊት ቱርክ እና ሶሪያን ክፉኛ ከጎዳው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ግንኙነታቸውን እያደሱ ነው።
ባለፈው ሳምንት መባቻ የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ራኢሲ አሳድን ጎብኝተዋል።
ራኢሲ ሶሪያ ወደ ሊጉ እንድትመለስ ጫና አሳድረዋል ተብሎም ይታመናል።
የግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ጉብኝት አድርገዋል። ከቱኒዚያ ጋርም በድጋሚ ግንኙነታቸው ታድሷል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ ብዙ የአረብ አገራትን ጎብኝተዋል።
አሜሪካ እና ዩኬ ከአሳድ አገዛዝ ጋር ግንኙነታቸውን እንደማያድሱ ከገለጹ ምዕራባውያን አገራት መካከል ናቸው።












