በዲሞክራቲክ ኮንጎ በጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት 400 የሚደርሱ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የሚገኙ ሁለት መንደሮች በጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት ከተመቱ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስከሬን በፍለጋ ተገኘ።
ከአደጋው በኋላ ነዋሪዎች ባደረጉት ፍለጋ ከፍርስራሾች ውስጥ እና ከተደረመሰ አፈር ውስጥ 400 የሚደርሱ ሰዎችን አስከሬን ለማውጣት ችለዋል።
ባለፈው ሐሙስ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል 200 ሰዎች ሞተዋል በማለት ገልጸው ነበር።
በኪቩ ሐይቅ ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኙ በርካታ መንደሮች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች የተቀበሩ ሰዎችን ፍለጋ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ በእጃቸው ሳይቀር ጭቃ እየማሱ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
የሟቾቹ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ የኮንጎ ቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች አስከሬኖች የሚሰበሰቡበት በቂ መያዣዎች ማቅረብ አልቻሉም።
በዚህም የተነሳ የሟቾቹ አስከሬን በደቡብ ኪቩ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ቡሹሹ እና ኒያሙኩቢ በተባሉ መንደሮች በብርድ ልብሶች ተጠቅልለው እንዲቀመጡ ተደርጓል።
ጎርፉ እና የመሬት መንሸራተቱ ከተከሰተ አራተኛ ቀኑ ቢሆንም በአደጋው የሞቱ ሰዎች አሃዝ ግን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። በአሁኑ ወቅትም ቁጥሩ 394 የደረሰ ሲሆን ፍለጋው በመቀጠሉ ቁጥሩ ይጨምራል ተብሎ ተሰግቷል።
አንዲት ከአደጋው ተርፋ በካበድ ሐዘን ውስጥ የምትገኝ የኒያሙኩቢ መንደር ነዋሪ የሆነች እናት ባሏ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል የገባ ሲሆን ልጆቿ ግን መሞታቸውን ገልጻለች።
“የምጽአት ቀን ነው የሚመስለው” በማለት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል - ኤኤፍፒ የተናገረችው የ27 ዓመቷ ጄንትሌ በአደጋው ወላጆቿን እና ሁለት እህቶቿን አጥታለች።
በእንጨት እና በቆርቆሮ የተሰሩ በአካባቢው የነበሩ ቤቶች በጎርፉ ምክንያት ተጠርገው ተወስደዋል።
በቡሹሹ መንደር ውስጥ ከአደጋው የተረፉ የተወሰኑ ቤቶች ደግሞ ግማሽ ክፍላቸው ድረስ በጭቃ ተቀብረዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ከደረሰው ከዚህ የጎርፍ አደጋ ቀደም ብሎ በስተ ምሥራቅ በምትጎራበታት እና ከኪቩ ሐይቅ በሌላኛው ወገን በምትገኘው ሩዋንዳ ውስጥም ከባድ ጉዳት ደርሷል።
በሩዋንዳ ከቀናት በፊት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ130 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
ባለፈው ሳምንት ለጉብኝት ወደ ኬንያ መጥተው የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እየተከሰቱ ያሉት የጎርፍ አደጋዎች የአየር ፀባይ ለውጥ ሌላኛው ግጽታ ነው ብለዋል።












