ወላጆች የጨቅላ ልጆቻቸውን ቋንቋ እንዴት መልመድ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጨቅላዎች ገና እንደተወለዱ በሚያሰሙት የመጀመሪያቸው በሆነው የልቅሶ ድምጽ ለወላጆቹ የምሥራችን ያበስራሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ሲሳይም “ልጆች ከእናታቸው ማሕፀን እንደወጡ የሚያሰሙት የልቅሶ ድምጽ ጠንካራ እና ጤናማ እንደሆኑ የምናውቅበት ነው” ይላሉ።
ሕጻናት ከተወለዱበት ከእናታቸው ማሕፀን ከወጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሦስት ወር ድረስ የተለያዩ ድምጾችን ያሰማሉ። ነገር ግን ከሚያሰሙት ከእያንዳንዱ ድምጽ ቀጥሎ ለቅሷቸው ነው ይመጣል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕጻናት ሕክምና እና ጤና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ ጨመዳ “ልጆች ያለምክንያት አያለቅሱም። ሲያለቅሱ የሆነ ሊነግሩን የፈለጉት ነገር አለ ማለት ነው” ይላሉ።
ሕጻናት የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ቋንቋ መልመድ ከመጀመራቸው በፊት፣ የትም ይወለዱ፤ ቤተሰቦቻቸው የትኛውንም ቋንቋ ይናገሩ ራሳቸውን የሚገልፁበት መንገድ አላቸው።
እርሱም ለቅሶ፣ ፈገግታ እና የአካል እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል።
የአንድ ሕጻን ለቅሶ የእጅ የእግር እና የጭንቅላት እንቅስቃሴ የሚፈልጉት ነገር መጠቆሚያ ሊሆን ይችላል ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ።
ዶ/ር ሲሳይ አክለውም ሕጻናት አንድን የፈለጉትን ነገር የሚገልፁበት መንገድ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ነው።
ባለሙያው እንደሚሉት ልጆች ከተወለዱ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ውስጥ ለምን እንደሚያለቅሱ መረዳት ለቤተሰብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ሕጻናትን ሊያስለቅሱ የሚችሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ረሃብ፣ ድካም፣ የሆድ ሕመም፣ ምቾት ማጣት፣ እንቅልፋቸው ሲመጣ እና ትኩረት በሚፈልጉበት ጊዜ ሊሆን ይችላል።
መደበኛ ቋንቋን ያልጀመሩ ሕጻናት ሲርባቸው፣ ምቱን በጠበቀ መልኩ ነው የሚያለቅሱት ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ።
ሲያማቸው ደግሞ ያለማቋረጥ፣ በተጨማሪም ከፊታቸው ላይ የጭንቀት ምልክት እያሳዩ ሊሆን ይችላል የሚያለቅሱት።
ቀስ ብለው የሚያለቅሱ እና ፊታቸውን የሚያሻሹ ከሆነ ደግሞ መተኛት ፈልገው ወይም ደግሞ ደክሟቸው ሊሆን ይችላል።
የአውስትራሊያ ዜግነት ያላት ፐርስላ ደንስተን የኦፔራ ስልት ሙዚቃ አቀንቃኝ ብቻ ሳትሆን፣ ልጆች ከማልቀሳቸው በፊት የሚያወጡትን ድምጽ ላይ ተመራማሪም ነች።
ደንስተን በሙዚቃ ላይ ያላትን የድምጸት ችሎታ በመጠቀም፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሕጻናትን ድምጽ በተለይም መደበኛ ቋንቋ መናገር ያልቻሉ ሕጻናትን ድምጽ ለስምንት ዓመታት ያህል አጥንታለች።
ደንስተን እንደምትለው ሕጻናት ልቅሶ ከመጀመራቸው በፊት የሚያሰሙትን ድምጽ ቤተሰብ ቢያውቀው፣ ልጃቸው ምን ሊነግራቸው እንደፈለገ ለመለየት ይረዳል።
ደንስተን “የሕጻናት ቋንቋ ሙሉ በሙሉ እንደ ቋንቋ ባይቆጠርም መደበኛ ቋንቋን ያልለመዱ ሕጻናትን ለመረዳት የሚረዳ መፍትሔ በመሆን ሊያገለገለ ይገኛል” ትላለች።
ደንስተን በስሟ የሰየመችው የምርመር ሥራ ‘ደንስተን የሕጻናት ቋንቋ’ ይሰኛል።
እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ ከሆነ ልጆች ከማልቀሳቸው በፊት የሚያሰሙት አምስት ዓይነት ድምጽ አለ።
እነዚህን ድምጾች ልጆች ማልቀስ ከመጀመራቸው በፊት በትኩረት መስማት ምን እንደፈለጉ ለማወቅ ይረዳል።
በደንስተን የሕጻናት ቋንቋ የተለዩ አምስቱ ድምጾች
ኔህ = እርቦኛል
ኤህ = አስገሱኝ
ምርር (እሪ) ሲያለቅሱ = መጸዳዳት ፈልገው
ህእ (እህ) = አካላዊ ምቾት ማጣት (ሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ ርጥበት)
ኦህ= እንቅልፍ
የሚያመለክቱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደንስተን የተባለው ይህ የሕጻናት ቋንቋ የሕጻናቱን የአካል አንቅስቃሴ በመጠቀም ልጆች ምን እንደሚፈልጉ ለማወቅም ይሞክራል።
ወላጆች ልጆቻቸው ስንት ጊዜ እንዳለቀሱ እና እንዴት እንዳለቀሱ መከታተል አለባቸው የሚሉት ዶ/ር ሲሳይ፣ ይህንን ሀሳብ ይደግፋሉ።
በአጠቃላይ መደበኛ ቋንቋን መናገር ያልጀመሩ ጨቅላ ሕጻናት የሚፈልጉትን ነገር የሚገልፁበት መንገድ ከሕጻን ሕጻን እምብዛም የማይለያይ እና ተመሳሳይ ነው ይላሉ።
ደንስተን የሕጻናት ቋንቋ ወላጆች እንዲለዩት ካስቀመጠው የአካል እንቅስቃሴ መካከል፣
አንድ ሕጻን ሳያለቅስ ጭንቅላቱን የሚያንቀሳቅስ ከሆነ ለመተኛት ፈልጓል ማለት ነው። ነገር ግን ጭንቅላቷን እያንቀሳቀሰች የምታለቅስ ከሆነ ምቾት ማጣት እና ሕመም እየተሰማት መሆኑን ነው።
የእጅ መዳፍን መጨበጥ የረሃብ ምልክት፣ እጅን ማወናጨፍ ደግሞ የፍርሃት እና የድንጋጤ ምልክት ናቸው።
ጭብጥ ማለት (ጎብጦ መተኛት ) የሚያሳየው ሕጻኑ ወይንም ሕጻኗ ከሚገባው በላይ ጠግበው ማግሳት መፈለጋቸውን ነው።
ይህ ምልክት ግን ሁለት ወር ለሞላቸው ሕጻናት ይለያል። ይህም ማለት ድካም አንደተሰማቸው አልያም ምቾት ማጣታቸውን ያመለክታል።
እግራቸውን ከፍ አድርገው ሲያነሱ ደግሞ አየር ማስወጣት አልያም ደስተኛ ሆነው ለመጫወት ከመፈለግ እንደሆነ ደንስተን በጥናቷ መለየት ችላለች።
ይህ የደንስተን የሕጻናት ቋንቋ ይሰራል፣ አይሰራም የሚለውን ለማረጋገጥ የሩሜኒያ ተመራማሪዎች ከተለያዩ አገራት 65 የጨቅላ ድምጾችን ሰብስበው በደንስተን አምስቱ የሕጻናት ቋንቋ መሰረት ለመለየት ሞክረዋል።
በዚህም 89 ከመቶ እነዚህ አምስቱ የሕጻናት ድምጾች ትክክል ሆነው ተገኝተዋል።
ደንስተን ባደረገችው ጥናት ሕጻናት ከተወለዱበት ቀን አንስቶ እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ እነዚህ አምስቱ ድምጸቶች የበለጠ ውጤታማ ናቸው።
ልጆች እያደጉ በሄዱ ቁጥር የራሳቸውን የተለየ ድምጸት እያመጡ ይሄዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወላጆች የልጆቹን አለቃቀስ ማወቅ እና መለየት ወሳኝ መሆኑን እና የልጅን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚረዳ ዶ/ር ሲሳይ ይናገራሉ።
በዚህም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የደንስተን የሕጻናት ቋንቋን ተምረው የተጠቀሙ እና ይህንን አምስቱን የሕጻናቱን የመግባቢያ ቋንቋን እና የአካል እንቅስቃሴን ከማይጠቀሙ ወላጆች በተሻለ ሁኔታ ከጨቅላ ልጆቻቸው ጋር እንደሚግባቡ ያሳያሉ።
ከዚህ ውጪ ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ ጨቅላ ሕጻናት ወይንም ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሚፈልጉት ነገር ከተሟላላቸው ከ16 ሰዓት በላይ ጊዜያቸውን በመተኛት ነው የሚያሳልፉት።
ልጆች ካልተራቡ፣ ካላመማቸው፣ የሚተኙበት ቦታ ከተመቻቸው “ሌላ የሚፈልጉት ነገር የወላጆቻቸውን ትኩረት ነው። እንዲያጫውቷቸው ይፈልጋሉ። የሰውነታቸው ሙቀት መካከለኛ ወይንም ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል።”
ጨቅላ ሕጻናት የተረጋጉ እንዲሆኑ ወይንም እንዳይረበሹ ለማድረግ ደግሞ ለስለስ ያለ ሙዚቃ መክፈት ይመከራል።
ይህንን እናቶች የሰባት ወር ነፍሰጡር ሆነው ጀምሮ ልጆቻቸውን መስማት ቢያለማምዱ የተረጋጉ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ይላሉ ሐኪሙ።
በተጨማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ራሳቸው ሰውነታቸው ሙቀት ማስጠጋት፣ ለብ ባለ ውሃ በየጊዜው ማጠብ፣ ዳይፐራቸውን እየተከታተሉ መቀየር እንዳያለቅሱ እና የተረጋጉ እንዲሁም ንቁ አንዲሆኑ ይረዳቸዋል ይላሉ።
ዶ/ር ሲሳይ ልጆች የሚፈልጉት ነገር ሳይኖር እንደዚሁ እንደማያለቅሱ በአጽንኦት በመናገር ወላጆች የጨቅላ ልጆቻቸውን ቋንቋ እንዲከታtሉ እና እንዲረዱ ያበረታታሉ።












