ሕጻናት በቤት ሠራተኞች ማደጋቸው ችግሩ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቤት እመቤትነት ዘመን እያበቃ ይመስላል። እናት እና ልጅ የሚተያዩት ጠዋት እና ማታ ሆኗል።
“ማማዬ! እንዳትኚ እሺ! እየመጣሁ ነው” የሚሉ ድምጾች ታክሲ ሰልፍ ላይ ሳይቀር ይሰማሉ።
ምን ይደረግ? የሕይወት ዘይቤ ተለወጠ። የልጆች ፍላጎትም ተለጠጠ። ኑሮው ቀን በቀን ይፋጃል።
እንኳን ለብቻ በጋራ ታግሎ መጣል ከብዷል።
አሁን የልጆች ዕድገት ባለሙያዎችን እያስጨነቀ ያለው ይህን ተከትሎ እየመጣ ያለው አደጋ ነው።
በእርግጥ ልጆችንን ማን ነው የሚያሳድጋቸው?
ኮስተር ብለን ከጠየቅን ልጆች በወላጆቻቸው ስም ይጠራሉ እንጂ ወላጆቻቸው አይደሉም የሚያሳድጓቸው።
አሁን አሁን የወላጆች ድርሻ በድርጀት ውስጥ የቦርድ የበላይ ጠባቂነት ሚናን እየመሰለ ነው፤ ውሳኔዎችን ማጽደቅ፤ በፊርማ ለሚመለከተው አካል ‘ይፈጸም’ እያሉ መምራት።
አቶ ሰኢድ ኢብሬ በልጆች አስተዳደግ የሥነ ልቦና ዘርፍ ተመራማሪ እና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው።
በተለይ በከተሞች አካባቢ ልጆች ከእናቶቻቸው ጋር ሳይተዋወቁ እያደጉ ነው ይላሉ።
አሁን አሁን ልጆች እያደጉ ያሉት “በቤት ሠራተኛ እና በቴሌቪዥን የጋራ ትብብር ይመስለኛል።”
የቴሌቪዥኑን ነገር እናቆየውና ልጆች በሠራተኛ ማደጋቸው ምንድነው ችግሩ?
የጭንቅ እና የናፍቆት ውሎ
እናቶች በተለይ የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ በአጭር ወራት ውስጥ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ይገደዳሉ።
ልጆቻቸው ሳይጠግቧቸው፤ እነርሱም እንደባቡ፣ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ዳግም ላይተያዩ ይለያያሉ።
ቅዳሜ እና እሑድ ለሠራተኛ እናቶች ብርቅ የሚሆኑት ለዚሁ ይሆን?
የባሕል እና የልምድ ጉዳይ ሆነና በልጆች ዕድገት ውስጥ የአባቶች ተሳትፎ የሳሳ ነው።
አባቶች ይህን የቀኑን ክፍለ ጊዜ ለመሸፈን የሚችሉበት ዕድል እና ፍላጎት ዝቅተኛ ነው።
በዚህ መካከል ልጆች ትምህርት ቤት እስኪረከባቸው ድረስ በቤት ሠራተኞች ለማደግ ይገደዳሉ።
“ይህ በራሱ ችግር ላይሆን ይችላል” ይላሉ አቶ ሰኢድ።
ነገር ግን ምን ያህሉ ሠራተኞች የልጆቹ አስተዳደግ ያሳስባቸዋል? ብለው ይጠይቃሉ።
“እንደምናስተውለው ከሆነ ሠራተኞች ልጆች ዝም፣ ጭጭ እንዲሉላቸው ነው የሚፈልጉት።”
ሶፋ ላይ፣ ወይ መኝታ ቤት አስቀምጠዋቸው ሥራቸውን መጨረስ ላይ ነው ትኩረታቸው።
በዚህ ጊዜ ልጆቹ አማራጭ አይኖራቸውም፤ “ቀኑን ሙሉ ከዱዳ ስልክ እና ብቻውን ከሚለፍፍ ቲቪ ጋር ተፋጠው ይውላሉ።”
ይህ ደግሞ በልጆቹ ዘንድ የሥነ ልቦና መቀንጨርን ያስከትልባቸዋል። ይህ እንዴት ሊከሰት እንደሚችል አቶ ሰኢድ እና ሌላኛዋ የልጆች ዕድገት ባለሙያ ጆርጎ ድሪባ ቆየት ብለው ያብራሩታል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚነሳው ሌላው ተጓዳኝ ጉዳይ ግን የእናቶች ጭንቅ ነው።
በሥራ ገበታ የሚገኙት እናቶች ልጄ ምን ሆና ይሆን? የሚለው ጭንቅ በሥራቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆናል።
ቀኑን ሙሉ እየበረገጉ ውለው ነው ቤት ተንሰፍስፈው የሚደርሱት።
ይህን በአሐዝ ማስደገፍ ባይቻልም በደምሳሳው ግን ምርታማነታቸውን እንደሚቀንስ መገመት ይቻላል።
ቀኑን ሙሉ እየበረገጉ ከዋሉ ደግሞ የአእምሮ ጤናቸውን አይጎዳውም አይባልም።
ይህ ማለት በየቤቱ፣ በየዕለቱ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ጤና እየተቃወሰ ነው ማለት ነው፤ የልጅ እና የእናት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቤት ሠራተኞች የማደግ የጎንዮሽ ጉዳቶች
የልጆች አስተዳደግ ተመራማሪው አቶ ሰኢድ ኢብሬ በልጆች አስተዳደግ በእኛ አገር ብዙ ሰው ትኩረት የሚሰጠው ለ“ሃርድዌር ዕድገታቸውን” ነው ይላሉ።
ይህ ደግሞ አካላዊ ዕድገትን ብቻ የሚመለከት ነው።
“ልጆች ከበሉ፤ ከወፈሩ፣ ድንቡሽቡሽ ካሉ ዕድገታቸው የተሟላ ይመስለናል፤ ነገር ግን ተሳስተናል” ይላሉ። ይህ የሕጻናት ዕድገት ባለሙያዋ ጆርጎ ድሪባም የሚስማሙበት ነው።
“እንደ ኢትዮጵያዊ ለስሜት ብዙም ቦታ አንሰጥም፤ ልጅ ከበላ ከጠጣ ሌላውን ትርፍ አድርገን ነው የምናየው። ነገር ግን አዋቂ የሚያልፍባቸውን ስሜቶች ሁሉ ልጆችም ያልፉባቸዋል። ልጆች ይፈራሉ፤ ይጨነቃሉ፤ ግራ ይገባቸዋል ወዘተ።”
መዘንጋት የሌለብን ይላሉ አቶ ሰኢድ፣ “የማንዳስሰው የልጆች ሥነልቦናዊ ጤና የዕድገታቸው ወሳኝ ክፍል መሆኑን ነው።”
ስለ ልጆች አካላዊ ዕድገት (ሃርድዌር) የሚጨነቅ ወላጅ በልጆች ላይ ስለሚጫኑ ‘ሶፍትዌሮች’ (ሥነ ልቦናዊ ዕድገት) አስተውሎት አይኖረውም።
ሶፍትዌሩ የሚጫነው በማን ነው? ከእናት ይጀምሩና አባት፣ ቤተሰብ ትምህርት ቤት፣ እኩዮቻቸው፣ ብሎም የሚመለከቷቸው ፊልሞችን ያካትታል።
ከሠራተኛ ጋር እንደ ሳሎን ውሻ ሶፋ ላይ ተጎልተው የሚውሉ ልጆች ታዲያ በዚህ ረገድ ብዙ ይጎድልባቸዋል።
አቶ ሰኢድ ይህን ሲያስረዱ ሦስት መሠረታዊ የልጆች አስተዳደግን በመዘርዘር ነው። አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ማኅበረ-ስሜታዊ ብለው ይከፍሏቸዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት አንዱ ከሌላው አይበልጥም አያንስም። የአንዱ ዕድገት መጓደል ግን የሌላውንም ዕድገት ያሰናክላል።
“አፍህን ዘግተህ ቁጭ በል!”
ለአቶ ሰኢድ ኢብሬ በልጆች ዕድገት እጅግ ወሳኙ ዘመን ከ1 እስከ 5 ዓመት ያለው ነው። ሳይንሱም ያንን ነው የሚለው።
ይህ የልጆች ዕድሜ አእምሮ በከፍተኛ ሁኔታ መረጃን የሚቀበልበት፣ ጠያቂ የሚሆኑበት፣ ከፍተኛ የአእምሮ አቅም የሚያገኙበት ነው።
ለዚህም ነው ይላሉ አቶ ሰኢድ፣ “አንዲትን ሕጻን ለሦስት ቋንቋዎች ብናጋልጣት ያለምንም ድካም ‘ትራይሊንጓል’ የምትሆነው። እደግመዋለሁ ያለምንም ጥረት።”
ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ምክንያቱ አንድ ነው። በዚህ ዕድሜ የልጆች አእምሮ መረጃን የሚቀበልበት ፍጥነት ስፖንጅ ውሃን የሚመጥበት ዓይነት ነው።
ይህ ዕድሜ ያለማቋረጥ ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን የሚጠይቁበት ጊዜ ነው ደግሞ።
“እግዚአብሔር የት ነው የሚኖረው? ለምን እኛ ቤት አይመጣም? ብቻውን ነው የሚኖረው?” እያሉ ሺህ ጥያቄን ይጠይቃሉ።
በዚህ ጊዜ የሚመጥናቸውን ምላሽ የሚሰጣቸው ወላጅ ይሻሉ።
የቤት ሠራተኞች ለእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ አይገመትም።
በዋናነት በሌላ ሥራ ስለሚጠመዱ፤ አንድም ግድ ስለማይሰጣቸው፤ ወይም መልስ ስለሌላቸው።
በአመዛኙ ካየን እነርሱ ልጆች ዝም እንዲሉላቸው ነው የሚመርጡት።
“በቃ አትጨቅጭቂኝ” ሊሆን ይችላል ምላሻቸው። “አፍህን ዘግተህ ተቀመጥ” ሊሆን ይችላል መልሳቸው።
ልጆች በዚህ ወሳኝ ዕድሜ እንዲህ ዓይነት ምላሽ ከተሰጣቸው ካደጉ በኋላ ለመጠየቅ ፈሪ፣ ኃላፊነትን የሚሸሹ፣ ጮክ ብለው መናገር የሚያፍሩ፣ ማንሾኳሾክ የሚመርጡ ይሆናሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሠራተኛ የሚያድጉ ልጆች ሁሉ ፈሪ ይሆናሉ?
ወላጅ እናት 4 ወር ላይ ልጇን ጥላ ሥራ ትገባለች። አባትም ሥራ ይውላል። ልጅ በሠራተኛ ያድጋል። ታዲያ ምን ችግር አለው?
የልጆች ዕድገት ባለሙያዋ ጆርጎ ድሪባ “ችግርማ አለው” ይላሉ።
ለምሳሌ ምን ዓይነት ችግር?
ለምሳሌ ልጆች ከእናታቸው ድምጽ ጋር ቁርኝት የሚጀምሩት ገና በማህጸን ሳሉ ነው። አንድ ዓመታቸው ሲሆን አካባቢያቸውን ይቃኛሉ። የእናታቸው ጠረን የደኀንነታቸው ዋስትና ሆኖ ይሰማቸዋል።
በልጆች ዕድገት የመጀመሪያው ዓመት የ“Trust-mistrust” [መቀራረብ እና መተማመን የሚገነቡበት] ዓመት ነው ይላሉ ጆርጎ።
“ለዚያም ነው እያለቀሱ እንኳ ቢሆን የእናታቸውን ድምጽ ከሩቅ ሲሰሙ ዝም የሚሉት፤ ዋስትና ስለሚሰማቸው።”
ስለዚህ ገና ሳይጠኑ ከእናታቸው ሙቀት ሲለዩ፤ ብሎም እንደነገሩ በሠራተኛ ሲያድጉ ምን ይፈጠራል የሚለውን መገመት ነው።
“ልጆቹ ድንጉጥ ይሆናሉ፤ ፈሪዎች ይሆናሉ፤ ስጋታም ይሆናሉ፤ ተጠራጣሪ ይሆናሉ።”
ጆርጎ ነገሩን ሲያጠቃልሉት፤ እናታቸው ስትርቃቸው ሽብር ውስጥ ይገባሉ፤ “የጭንቅ ሆርሞን ነው በሰውነታቸው የሚረጨው” ይላሉ።
ምግብ የማይበሉት ለዚያ ይሆን?
ልጆች የምግብ ፍላጎታቸው ከፍ የሚለው ደኅንነት ሲሰማቸው ነው።
በፍርሃት እና በስጋት ውስጥ ከሆኑ ምግብ አይበሉም።
ልጆች የአእምሮ ሴሎቻቸው የሚያድጉት ከጭንቀት ነጻ ሲሆኑ ነው። ደኅንነት ሲሰማቸው ነው።
ሠራተኛ ያን ደኅንነት ካልሰጠቻቸው የአእምሮ ዕድገታቸው ተጓደለ ማለት ነው።
“የሚስቅ፣ የሚቦርቅ፣ የሚፈነድቅ ልጅ ነው ጥሩ ዕድገት ያለው ልጅ ማለት” ይላሉ ባለሙያዋ ጆርጎ።
አንዳንድ ጥናቶች እንዳሳዩት ደግሞ ልጆች የሕጻናት መዋያ ሲወሰዱ እና ወላጆች እዚያ አስቀምጠዋቸው ሲሄዱ የሚሰማቸው ስሜት መልካም እንዳልሆነ ነው።
“የተተዉ፣ የማይፈለጉ ሆነው ይሰማቸዋል፤ ብቻ ፈርጀ ብዙ ነው ችግሩ” ይላሉ ባለሙያዋ።
ምግብ ለመብላት ያላቸው ፍላጎት ዝቅ ማለት አንዱ ምክንያት የደኅንነት ማጣት ነው ሊባል ይችላል።
ደኅንነት ማጣቱ ደግሞ የሚመጣው ወላጆች ለሠራተኛ ጥለዋቸው ሲሄዱና ከዚያ ወዲያ ባለው ጊዜ የሚሰማቸው ስሜት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
የሠራተኞች መቀያየር የሚያመጣው ጣጣ
ሌላው ችግር ልጆች በሠራተኛ ጥሩ የሚባል እንክብካቤ እያገኙ ደኅንነት ተሰምቷቸው መሳቅ መቦረቅ ሲጀምሩ ሌላ ሠራተኛ ይተካባቸዋል።
ይህ ሁኔታ እንደ አዲስ ልጆቹ ግራ መጋባት ውስጥ ይከታቸዋል። እንደ አዲስ ዋስትና እንዲሰማቸው የማድረግ ጥረቱም ቀላል አይሆንም።
በዚህ ሁኔታ የሚያድጉ ልጆች የስሜት ዝብርቅርቆሽ ይፈጥርባቸዋል።
ልጆች ከሠራተኛ ጋር ቤት ሲውሉ ምን ስሜት ይሰማቸዋል?
ይህ ከልጅ ልጅ ቢለያይም ይላሉ ባለሙያዋ፣ በአእምሯቸው የሚመላለሰው ግን ያለመፈለግ እና ያለመወደድ ስሜት ነው። ለእነርሱ ግድ ያለው ሰው እንደሌለ ያስባሉ።
ልጆች ስለሆኑ ይህን አያስቡም ብሎ ማለት ግን የዋህነት ነው።
ወላጆች ለምን ሥራ እንደሚውሉ ማታ ሲገቡ ለልጆቻቸው ማስረዳት አለባቸው፤ ይላሉ ጆርጎ። ወደ ሥራ ሲሄዱም እንዲሁ።
“እኔ ሥራ የምሄደው ይህን ላደርግ ነው፤ ግን ስመለስ ደግሞ ካንተ ጋር ወይም ካንቺ ጋር አንዲህ እናደርጋለን” ብለው በፍቅር ነው መሰናበት ያለባቸው።
አለበለዚያ ልጆቹ የመተው - ያለመፈለግ ስሜት ያድርባቸዋል።
“አንዳንዴ ከተቻለ ልጆችን ሥራ ቦታ ይዞ መሄድ እና ማሳየትም ጥሩ ነው፤ ብዙ ነገር ይረዳሉ።”
መፍትሄው ምንድነው?
ወላጆች ሥራ አቁመው ልጅ ያሳድጉ አይባል ነገር።
ባለው ሁኔታ ግን ነገሮች ማሻሻል እንደሚቻል ሁለቱ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
አንዱ ወላጆች ማታ ቤት ሲመለሱ ከልጅ ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ [ዕድሜው ከፈቀደ]፣ ብሎም የልጃቸውን ውሎ ጥንቅቅ አድርጎ መረዳት ያስፈልጋል።
ልጆቹ ለመናገር የሚፈሩት ነገር ካለ አደጋ እንዳለ ተረድቶ ያን መፈተሽም ይመከራል።
ጆርጎ ድሪባ እናቶች ሞግዚቶችን በልጅ ፊት ማመናጨቃቸው ያለውን አደጋ ያስረዳሉ።
አንደኛ በሠራተኛዋ ላይ መጥፎ ስሜት ይፈጥራል። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ የሠራተኛዋ በጎ ያልሆነ ስሜት ወደ ልጅ መጋባቱ የማይቀር ነው።
ሁለተኛ ልጅ ከዚህ የማመናጨቁ ክስተት በጎ ያልሆነ ነገር ይቀስማል። መመናጨቅ ያለባቸው ሰዎች አሉ ብለው ልጆች እንዲያስቡ ያደርጋል።
ስለዚህ ወላጆች ጤናማ ተግባቦት ከሠራተኛ ጋር መመሥረትን ቅድሚያ ይስጡ ይላሉ ሁለቱም ባለሙያዎች።
“እኛ ላይ ሊደረግብን የማንፈልገውን ነገር ሌላው ላይ ባናደርግ።”












