ሕጻናት ለምን በተደጋጋሚ ለቶንሲል ህመም ይዳረጋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቶንሲል በርካታ ወላጆችን የሚያሳስብ ህመም ነው። ቶንሲል በሕጻናት ላይ በስፋት የሚከሰት ሲሆን በተደጋጋሚም ሊያጋጥም ይችላል።
በእርግጥ በሽታው ዕድሜ አይለይም። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ያጠቃል።
በተለይ በሁለቱ የዕድሜ ጫፎች በሚገኙ ሰዎች ላይ ህመሙ ይበረታል-በሕጻናት እና በአረጋውያን ላይ።
ይህ ህመም ብዙውን ጊዜ ችላ የሚባል ግን ደግሞ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል ነው።
ለመሆኑ የቶንሲል ህመም ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል? ለምን በተደጋጋሚ ይከሰታል? መፍትሔውስ?
ስለእነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዶ/ር ትንሳኤ አለማየሁን ጠይቀናቸዋል።
ዶ/ር ትንሳኤ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የሕጻናት ተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ናቸው። በአዲስ አበባ በሚገኘው በአሜሪካ ሜዲካል ሴንተር ይሰራሉ። በቅዱስ ጳውሎስ የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥም ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።

የቶንሲል ህመም በአብዛኛው ሕጻናትን የሚያጠቃ በትንፋሽ የሚተላለፍ የጉሮሮ ህመም ነው ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ ስለምንነቱ ማብራራት ሲጀምሩ።
ይህ በሽታ በባክቴሪያ አሊያም በቫይረስ ሳቢያ ሊከሰት ይችላል።
አብዛኛውን የቶንሲል ህመም የሚያስከትሉት ግን ቫይረሶች ናቸው።
ኮቪድን ጨምሮ የተለመዱት በትንፋሽ የሚተላለፉ የጉንፋን ቫይረሶች የቶንሲል ህመምን ያስከትላሉ።
በባክቴሪያዎች ሳቢያ የሚመጣው ግን በቫይረስ ከሚከሰቱት ይለያል።
የሚያስከትለው ህመም የበረታ ሲሆን በጊዜ ካልታከመ የከፋ ጉዳትን ያስከትላል። በዚህም ምክንያት በቫይረስ ከሚከሰተው በበለጠ ልዩ ትኩረትን ይሻሉ።
በህክምናም እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ስለሚያስከትል ነው።
ምንም እንኳን በዚህ ሳቢያ በሚከሰት የቶንሲል ህመም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የሚያስከትለው መዘዝ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።
ታዲያ ያጋጠመን የቶንሲል ህመም የትኛው እንደሆነ እንዴት መለየት ይቻላል?
ዶ/ር ትንሳኤ ሲመልሱ “ያጋጠመን የቶንሲል ህመም በምን ምክንያት እንደመጣ ያለ ምርመራ መለየት አዳጋች ነው” ይላሉ።
የህክምና እውቀት የሌለው ሰውም ይህንን መወሰን አይችልም። እርሳቸው እንደሚሉት የህክምና እውቀት ያለውም ቢሆን በጥንቃቄ ካልተመለከተ ለመለየት አስቸጋሪ ነው።
ማንኛውንም የተከሰተ የቶንሲል ህመም በምን ምክንያት እንደመጣ ሳያረጋግጡ እንደ ቀላል መቁጠር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ዶ/ር ትንሳኤ ያስጠነቅቃሉ።
የቶንሲል ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ትኩሳት፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር እንዲሁም በተለምዶ ንፍፊት በሚባለው የአንገት ክፍል ላይ የሚከሰት እብጠት የሚታዩ ምልክቶች ናቸው።
በምርመራ ወቅትም ቶንሲሎቹ አብጠው አሊያም መግል ይዘው ይታያሉ።
ይህ አጠራጣሪ ከሆነም ከጉሮሮ ላይ ናሙና ተወስዶ በሚደረግ ምርመራ አንድ ሰው የቶንሲል ህመም እንዳለበትና እንደሌለበት ማረጋገጥ ይቻላል።
ለቶንሲል ህመም እምብዛም በማይጠቁት ጨቅላ ሕጻናትም ላይ ትኩሳት፣ ጡጦ አሊያም ጡት መጥባት ማቆም፣ የምግብ አወሳሰድ መቀነስ ሊታይ ይችላል።
በዚህ ወቅት ለቶንሲል ህመም ተዳርገው ሊሆን ስለሚችል ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ትንሳኤ ይመክራሉ።
የቶንሲል ህመም በአብዛኛው ከሦስት ዓመት ጀምሮ ያሉትን ሕጻናት ነው የሚያጠቃው። በተለይ ዕድሜያቸው ከሦስት ዓመት እስከ 18 ዓመት ያሉ ሕጻናትና ወጣቶች ከሁሉም በላይ ተጋላጭ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ትንሳኤ እንደሚሉት አብዛኞቹ ተላላፊ በሽታ ሕጻናት ላይ ጠንከር ይላሉ።
ሕጻናት እና በጣም ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች ላይ በሽታ የመከላከል አቅም ዝቅ ስለሚል አብዛኞቹ ተላላፊ በሽታዎች በእነዚህ የዕድሜ ክልሎች ላይ በስፋት ይከሰታሉ።
በተለይም በማደግ ላይ ባሉ የአፍሪካ እና የእስያ አገራት ባለው የተጨናነቀ እና የተፋፈገ የአኗኗር ዘይቤ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ያለ ሰው ቶሎ ቶሎ በቶንሲል ህመም የመያዝ እድሉ ከፍተኛ ነው።
በበሽታው በቀላሉ በበሽታው ከተያዘ ሰው ወደ ሌሎች የሚተላለፍ በመሆኑም በሽታ የመከላከል አቅም ዝቅተኛ በሆነበት የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ሰዎች ተጨማሪ አደጋን ይፈጥርባቸዋል። በተደጋጋሚም ይከሰታል።
ዶ/ር ትንሳኤ “ተደጋጋሚ የሆነ ቶንሲልን ጨምሮ በትንፋሽ የሚተላለፍ ህመም አንድ ሰው የሚኖርበት ማኅበረሰብ ነጸብራቅ ነው” ይላሉ።
የውሃ አቅርቦት አናሳ በሆነበት፣ ሰዎች ተፋፍገው በሚኖሩበት፣ ልጆች ተፋፍገው በሚማሩበት ቦታዎች፣ አንድ ሕጻን ታሞ ሕክምናው ተሰጥቶት ተመልሶ ከገባ በኋላም በዓመት ውስጥ ሦስት ወይም አራት ጊዜ ተደጋግሞ ቢመጣ የሚደንቅ እንዳልሆነም ያስረዳሉ።
ተደጋግሞ በሚከሰትበት ጊዜም የአየር ቧንቧ ጥበት ፣ የመተንፈስ ችግር፣ በእንቅልፍ ሰዓት የአየር ማስተላለፍ ችግሮች፣ ማንኮራፋት የመሳሰሉ እክሎች እየጨመሩ ይመጣሉ። ይህም በልጆች የቀን ተቀን እንቅስቃሴ እና የትምህርት አቀባበል ጭምር ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ሁኔታው ከከፋ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ሊያስፈልግም ይችላል።
የቶንሲል ህመም የሚያስከትለው የከፋ የጤና ችግር ምንድን ነው?
የቶንሲል ህመምን እንደ ቀላል የማየት ልማድ አለ።
ህመሙ ችላ ስለሚባልም በቤት ውስጥ በሚደረጉ ሕክምናዎች ብቻ ለማለፍ ሲሞከረም ይስተዋላል፤ ነገር ግን የተከሰተው የቶንሲል ህመም በምን ምክንያት እንደመጣ ሳያረጋግጡ እንደ ቀላል መቁጠር ሕይወትን አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ።
እርሳቸው እንደሚሉት በተለይ በባክቴሪያ የሚመጣው የቶንሲል ህመም ሁለት ዓይነት ውስብስብ የጤና ችግሮችን ያመጣል።
የመጀመሪያው ከቶንሲሉ ዳርና ዳር ያለው የጉሮሮ ክፍል ላይ በቶንሲሉ ምክንያት የመጣው የመግል መቋጠር ሲሰፋ የሚከሰት ነው።
አንገታችን ጠባብ ነው። በዚህ ጠባብ የሰውነታችን ክፍል የሚተላለፉ ወሳኝ የሆኑ የአየር እና የምግብ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች አሉ።
በመሆኑም ቶንሲሉ እያበጠ ሲመጣ የእነዚህ ወሳኝ የአካል ክፍሎችን ሥራ ያስተጓጉላል። መተንፈስና ምግብ ማስተላለፍን እስከመከልከል ሊደርስ ይችላል።
ሁለተኛው ደግሞ በጊዜው ካልታከመ ለተወሰኑ ሳምንታት ይቆይና ከጉሮሮ አልፎ የልብ ቫልቮች ላይ ጉዳት ያስከትላል።
የልብ ቫልቮች አንደኛውን የልብ ክፍል ከሌላኛው የልብ ክፍል የሚያገናኙና እንደ በር እየተከፈቱና እየተዘጉ ደም የሚያስተላልፉ ቦታዎች ናቸው።በቶንሲል ህመም ሳቢያ በእነዚህ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በእንግሊዝኛው አጠራሩ Rheumatic fever ይባላል።
በተለይ የቶንሲል ህመም በተሰራጨባቸው አገራት ውስጥ ከቶንሲል ጋር በተያያዘ የልብ ህመም የሚጠቁ ሕጻናት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው።
ሪውማቲክ የልብ ህመም
- ይህ የልብ በሽታ በአግባቡ ካልታከመ በባክቴሪያ በሚመጣ የቶንሲል ህመም ሳቢያ የልብ ቫልቮች ላይ ከሚደርስ ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው።
- እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ይህ የልብ በሽታ በአብዛኛው የሚያጠቃው ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ያሉ ሰዎችን ነው።
- በአብዛኛውም በልጅነት ዕድሜ የሚከሰት ሲሆን ለሞት አሊያም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ የሚዘልቅ ጉዳትን ያስከትላል።
- በዚህ የልብ ህመም ሳቢያ በየዓመቱ ከ288 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ይዳርጋሉ።ከእዚህ መካከል አብዛኛው የሚከሰተው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ነው።
- ይህንን ህመም ኢንፌክሽኖች እንዳይከሰቱ በመከላከል፣ ከተከቱም ሳይረፍድ ተገቢውን ሕክምና በማድረግ መከላከል ይቻላል።
ይህ ብቻም አይደለም። ያልታከመ የቶንሲል ህመም የኩላሊትን የማጣራት አቅም የሚያደክም ውስብስብ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ዶ/ር ትንሳኤ ይናገራሉ።
በዚህ ህመም የተጠቁ ልጆች ፊታቸው ያብጣል፣ የደም ግፊታቸው ይጨምራል፣ የኩላሊታቸው የማጣራት ችሎታም ይቀንሳል።
“ካልታከመ የከፋ ጉዳት ስለሚያስከትል አክብረንና ትኩረት ሰጥተን ነው የምናክመው” ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ።
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ሕጻናት በዚህ የልብ ህመም ምክንያት ለልብ ቀዶ ሕክምና ይዳረጋሉ።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በኢትዮያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል፣ የጽኑ ህሙማን ከፍተኛ የልብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሔለን በፍቃዱ “ቶንሲል እንዴት መታከም እንዳለበት በስፋት ግንዛቤ መስጠት ብቻውን የዛሬ 15 ዓመት ሊመጡ የሚችሉ የልብ ቀዶ ህክምናን የሚሹ ሕጻናትን ቁጥር በብዙ እጥፍ ይቀንሳል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቤት ውስጥ ሊደረግ የሚችል ሕክምና አለ?
የቶንሲል ህመም በሚያጋጥምበት ጊዜ በተለምዶ በቤት ውስጥ የምናደርጋቸው ሕክምናዎች አሉ። ጨው ባለው ውሃ መጉመጥመጥ፣ የሎሚ ጭማቂ መጠጣት እና የመሳሰሉት።
ይሁን እንጂ ዶ/ር ትንሳኤ የቶንሲል ህመሙ ምንነት በምርመራ ሳይረጋገጥ ይህንን ማድረግ አይመከርም ይላሉ።
በእርግጥ አብዛኛው የቶንሲል ህመም የሚከሰተው በቫይረስ ነው።ይህም ማስታገሻዎች ብቻ ነው የሚፈልገው። ለምሳሌ ትኩሳት ካለ የትኩሳት መድሃኒት፣ ህመም ካለ የህመም ማስታገሻ እና በቂ ፈሳሽ በመውሰድ ያለ ዘመናዊ ሕክምና ይጠፋል።
“ለዚህ ዓይነቱ ህመም ቤት ውስጥ የሚደረጉ ነገሮች ጨው ባለው ውሃ መጉመጥመጥ እና ፈሳሽ በመውሰድ የመሳሰሉት በመጠኑ ሊረዱ ይችላሉ” ይላሉ።
“ይህ ባይደረግ እንኳን ቫይረሱ የራሱ የሆነ ሒደትና የሚበስልበት ጊዜ ስላለው ጊዜውን ሲጨርስ ራሱ ይጠፋል” ሲሉም ያክላሉ።
በባክቴሪያ የሚመጣው ቶንሲል ግን በዘመናዊ ሕክምና ፀረ ባክቴሪያ [አንቲባዮቲክ] ካልተወሰደ ውስብስብ እና አደገኛ የጤና ችግሮችን ያስከትላል።
ዶ/ር ትንሳኤ እንደሚሉት ምልክቶቹ ተቀራራቢ በመሆናቸውም ለመለየት አዳጋች ናቸው።
በቫይረስ የሚመጣ የቶንሲል ህመም የንፍጥ መዝረክረክ፣ የአፍንጫ መደፈን ሊታይ ይችላል።
በባክቴሪያ የሚመጣ ደግሞ መግል የመቋጠርና ህመሙ ጠንከር የማለት ነገር አለ። ይሁን እንጂ ይህ ባክቴሪያ ነው ቫይረስ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።
በትክክል የሚታወቀው ከጉሮሮ ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ ነው።
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የመመርመሪያ አቅም ስለሌላቸው ለምሳሌ የንጽህና ጉድለት ያለበት እና የተፋፈገ የመኖሪያ አካባቢዎች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ውስጥ በባክቴሪያ የተከሰተ የቶንሲል ህመም የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
በመሆኑም “ባክቴሪያ አሊያም ቫይረስ ይሆናል የሚል ግምት ሰጥተን ሳይሆን ባላክመው ምን ሊከተል ይችላል? በሚል አንቲባዮቲክ ነው የምንሰጠው” ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ።
"ባደጉ አገራት ግን በቂ የመመርመሪያ ዕቃዎች ስላላቸው እና በሽታው ቶሎ ቶሎ አይከሰትም" የሚሉት ዶ/ር ትንሳኤ፣በባክቴሪያ የሚከሰተው ህመም በጣም አነስተኛ በመሆኑ ሁሉም ታማሚ አንቲባዮቲክ ወይም ሌላ መድሃኒት አይወስድም።
“መድሃኒት የሚሰጠው በምን ምክንያት የመጣ ነው የሚለው ከተለየ በኋላ ነው” ሲሉም ያስረግጣሉ።
በመሆኑም ለተከሰተው ማንኛውም የቶንሲል ህመም በቤት ውስጥ ሕክምና ብቻ ማድረግ፣ በተለይ ልጆች በቶንሲል ቶሎ ቶሎ በሚያዙበት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት አይመከር ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
እንዴት መከላከል ይቻላል?
በትንፋሽ የሚተላለፍን በሽታ መከላከል አደጋች ነው። ይህም የኮቪድ ወረርሽኝ ሥርጭት ጣሪያ በነካበት ወቅት የታየ ሐቅ ነው።
በተለይ ደግሞ በተጨናነቁ እና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች በበሽታው የተያዘ ሰው ምልክቶቹ ባይታዩበትም በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።
ቢሆንም ግን የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ ፣ ከሰዎች ጋር ከተቀላቀልን በኋላ እጃችንን በማጽዳት፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን በሳሙና እና በውሃ በደንብ በመታጠብ አሊያም ሳኒታይዘር በመጠቀም መከላከል ይቻላል።
“ወላጆችም ይህንን ተግባራዊ እያደረጉ ለልጆች ማስተማር ተገቢ ነው” ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ።
የህመም ምልክት ከታየ ግን ሕክምና ቦታ ሄዶ ምርመራ ማድረግ ነው የሚመከረው።ተገቢው ሕክምና በጊዜው ከተደረ ለውስብስ የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል።
በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገራት ያሉ ሰዎች ለዚህ ህመም ከተዳረጉ ሕክምና ቦታ እንዲሄዱ ይመክራል።
ሕክምናው ምንድን ነው?
ዶ/ር ትንሳኤ ሕክምናው እንደ ህመሙ ዓይነትና ክብደት ይለያያል ይላሉ።
ቀላል ሕክምና ፀረ ባክቴሪያ [አንቲባዮቲክስ] መድሃኒቶች በሽሮፕ አሊያም በክኒን መልክ ይሰጣል።
በጣም ከተደጋገመ እና አንገት ላይ መግል ከተቋጠረ በመርፌ እንዲፈስ በማድረግም ሕክምናው ሊሰጥ ይችላል።
በተደጋጋሚ በመከሰቱ ሳቢያ የቶንሲሉ ስጋ እየወፈረ ከሄደም ቶንሲሎቹን በቀዶ ሕክምና ማስወገድ ድረስ ሕክምናው ይሰጣል።
በጊዜው ሕክምና ካልተደረገ እና ልብ እና ኩላሊት ላይ የጤና እክል ካጋጠመ ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል።
በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉ የቶንሲል ህመሞች ባለመታከማቸው በርካታ ሕጻናት በልብ ህመም እንደሚሰቃዩ በልብ ሕክምና ማዕከል ወረፋ የሚጠባበቁ ሕጻናትን ማየት በቂ ነው ይላሉ ዶ/ር ትንሳኤ። ይህን ሕክምና ማግኘት የሚችሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
“በተለይ እንደ እኛ አገር ውስን የሕክምና መሠረተ ልማትና አቅርቦት ላለው፣ ቴክኒካል የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች አነስተኛ በሆኑበት ትኩረት ማድረግ ያለብን መከላከል ላይ ነው” ሲሉም ይመክራሉ።
ከ30 ዓመታት በላይ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ የልብ ሕክምናዎችን እየሰጠ በሚገኘው የኢትዮጵያ የልብ ማዕከል በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ሕክምናውን ለማግኘት ወረፋ ይጠባበቃሉ። አንዳንዶቹም ወረፋ ሳይደርሳቸው ሕይወታቸው ያልፋል።












