80 በመቶ የዓለማችን ወጣቶች የአካል እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕድሜያቸው ከ11 ጀምሮ 17 የሚመዘዝ የዓለማችን ታዳጊዎች በቂ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ እያደረጉ አይለም ይላል አንድ አዲስ የወጣ ጥናት።
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው የሕፃናት አካላዊና ልቡናዊ ጠና በዚህ ምክንያት እየተቃወሰ ነው። አልፎም ማሕበራዊ አኗኗራቸው ቅጥ ያጣ እየሆነ ነው።
ድርጅቱ ይህ ችግር የደላቸው የዓለም ሃገራት ብቻ ሳይሆን 'ድሃ' በሚባሉ የዓለም ሃገራትም በሰፊው የሚንፀባረው ነው።
ጥናቱ በተካሄደባቸው 146 የዓለም ሃገራት ታዳጊ ወንዶች ከሴቶች በተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ተደርሶበታል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዴት ያለው ነው?
የልብ ምት ከተለመደው ፈጠን እንዲል የሚያደርግ እንቅስቃሴ በጠቅላላው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደርጎ ይቆጠራል።
- ሩጫ
- ብስክሌት መጋለብ
- ዋና
- ገመድ ዝላይ
- ዱብ ዱብ [ሰኞ ማክሰኞ ጨዋታ ከዚህ የሚመደብ ነው]
- ጂምናስቲክ
እኒህን እንቅስቃሴዎች በቀን ለ60 ደቂቃ ያክል ማከናወን ከቻሉ ይመኑን ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሁለት ይከፈላል። መጠነኛና ከበድ ያለ። ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትንፋሽ ሊያሳጣዎት ሁላ ይችላል።

ጉዳዩ የሚያስጨንቅ ነውን?
ዋናው ጤና ነው እንዲል የሃገሬ ሰው። ዋናው ጤና። አሁን ባለንበትና በመፃዒው ሕይወታችን።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ሰዎች ጤናማ ልብ እና ሳንባ፤ ጠንካራ አጥንት እና ጡንቻ፤ የተሻለ የአእምሮ ጤና እና መጠነኛ የሰውነት ክብደት ይኖራቸዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የልብ ሕመም እና ስትሮክ ተጋላጭነት ይቀንሳል። ከሁለም በላይ ለጤናማ አስተሳሰብ የራሱን አአስተዋፅኦ ያደርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
ታዳጊዎች ምነው ሰነፉ?
«ታዳጊዎች ሰንፈው አይደለም» ይላሉ ዶክተር ቡል። «ጥናቱ የሚነግረን ሌላ ነገር አለ፤ ይህም እና ታዳጊዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አለመገፋፋታችን ነው። ደግሞ ችግሩ ዓለም አቀፍ መሆኑ አስጊ ያደርገዋል።»
ታዳጊዎች ለምን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አያደርጉም የሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ያለው አይመስልም። ነገር ግን በርካታ መላ ምቶች ይሰጣሉ።
አንደኛው መላ ምት ታዳጊዎች ከአካላዊ ጤናቸው ይልቅ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ መገፋፋታቸው ነው የሚል ነው።
ከጥናቱ አጥኚዎች አንዱ የሆኑት ሊያን ራይሊ፤ «ታዳጊዎች መማሪያ ክፍሎችም ውስጥ ቤታቸው ለበርካታ ሰዓታት ተቀምጠው እንዲያጠኑ ይደረጋሉ። ይህ ደግሞ ንቁ አካል እንዳይኖራቸው ያግዳል» ይላሉ።
ሌላኛው እንቅፋት ምቹ፤ የተሟላ እና ክፍያው ዝቅ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ሥፍራ ማጣት ነው።
ሌላው ቀርቶ በማደግ ላይ ባሉ የዓለማችን ከተሞች ተማሪዎች ከቤት-ት/ቤት በብስክሌት ለመሄድ አሊያም ለመራመድ ይቸግራቸዋል። የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ መንገዶቹ አደጋ የሚበዛባቸው መሆናቸው ነው።
ሶስተኛው መላ ምት ከሥልጣኔ ጋር የተያያዘ ነው። 'ዲጂታል' ዓለም ታዳጊዎችን እያቀበጠ ነው። ስልክ፣ ታብሌት፣ ኮምፒውተር እያሉ ማን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋል።
«ዘንድሮ ታዳጊዎች ዘና የሚሉባቸው በርካታ አማራጮች አሉ፤ እኒህ አማራጮች ጊዜን ይሻማሉ» ይላሉ ዶ/ር ራይሊ።
የትኞቹ ሃገራት ይሻላሉ?
የዓለም የጤና ድርጅት ከአፍጋኒስታን እስከ ዚምባብዌ የአካል ብቃት ያለማድረግ ችግር ሁሉም ሃገራት ላይ የሚስተዋል ነው ይላል።
ሌላው ቀርቶ ከሌሎች ሃገራት በላቀ ታዳጊዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጉባታል የምትባለው ባንግላዴሽ 66 በመቶ ታዳጊዎች ንቁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም።

ፊሊፒንስ 93 በመቶ ወንድ ታዳጊዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉባት ሃገር፤ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ 97 በመቶ ሴቶች የማይንቀሳቀሱባት ሃገር ተብለው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
እንግሊዝ ውስጥ 75 በመቶ ወንዶች፤ 85 በመቶ ሴቶች ንቁ የስፖርት ሰዎች አይደሉም ሲሉ ጥናቱ ያስቀምጣል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በአራት የዓለማችን ሃገራት ብቻ ሴቶች ከወንዶች በላቀ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። እኒህ ሃገራት ቶንጋ፣ ሳማዎ፣ አፍንጋኒስታን እና ዚምባብዌ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታየ 78 በመቶ ወንዶች፤ 85 በመቶ ሴት ታዳጊዎች ንቁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ አይደሉም።
አሜሪካ እና አየርላንድ ደግሞ የወንድ ታዳጊዎች ቁትር ከሴቶቹ እጅግ የላቀ ሆኖ የተመዘገበባቸው ናቸው።
ባሕልና አስተሳሰብ ሴቶች ከወንዶች ባነሰ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርገዋል ተብሏል።
በጠቅላላው የባለሙያዎቹ ወቀሳ ቴክኖሎጂ ላይ ያነጣጠረ ነው።
ብዙ መቀመጥ፤ ትንሽ መተኛት፤ አለመራመድ. . . የዘመናዊ ሕይወት መገለጫ ሆነዋል። የእኛስ ይሁን ልጆቻችንን ግን እንቀይራቸው የጥናቱ መልዕክት ነው።













