የኤርትራ መንግሥት፡ 'የካቶሊክ ጤና ተቋማትን መውሰዴ ትክክል ነው' አለ

የኤርትራ መንግሥት፡ 'የካቶሊክ ጤና ጣቢያዎችን መውሰዴ ትክክል ነው'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኤርትራ መንግሥት በቅርቡ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ንብረት የሆኑ የጤና አገልግሎት መስጫ ጣብያዎችን መውረሱን ተከትሎ ለመጡ ትችቶች ምላሽ ሰጥቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ልዩ መልዕክተኛ ዳንዔላ ካርቬትዝ፤ «ጉዳዩ የኤርትራ መንግሥት ምን ያህል ሰብዓዊ መብትን እየጨቆነ እንደሆነና ሁኔታዎች እንዳልተቀየሩ የሚያሳይ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

የኤርትራ መንግሥት «መልዕክተኛዋ ድምዳሜ ላይ የደረሱት የተሳሳተ መረጃ ይዘው ነው» ሲል ወርፏቸዋል።

በኤርትራ መንግሥት መረጃ ሚኒስቴር በኩል የወጣው ምላሽ «እንደ ዓለማዊ [ሴኩላር] ሃገር ማንኛውም ዓይነት የኃይማኖት ተቋም የሪፈራል ሕክምና ሊሰጥ አይገባም» ሲል ያትታል።

«በመሆኑም ተቋማት በመረጡት መስክ ተሰማርተው ሕብረተሰባዊ አገልግሎት መስጠት አይችሉም፤ ይህ የእነርሱ ተከታይ ያልሆነ ላይ አድልዎ እንደማድረስ የሚቆጠር ነው» ሲል መግለጫው ያክላል።

የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ መግለጫ 'ሁሉም ኃይማኖታዊ ተቋማት ጤና ተቋሞቻቸውን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማስረከብ ግዴታ እንዳለባቸው' ያስታውቃል።

በሌላ ቋንቋ መንግሥት ሕጉን ተከተለ እንጂ ስህተት አልሠራም ነው የኤርትራ መንግሥት አመክንዮ።

ባለፈው ወር መገባደጃ ገደማ ነበር የኤርትራ መንግሥት የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ንብረት የሆኑ የጤና ተቋማትን የወረሰው።

22 ያክል የጤና አገልግሎት ሰጭ ጣቢያዎቿ የተዘረፉባት የኤርትራ ሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የመንግሥት ድርጊት ተቃውማለች።

የጤና ጣብያዎቹ በመንግሥት እጅ መውደቅ በገጠር አካባቢ ላሉ እናቶች እና ሕፃናት እክል ይሆናል ቢባልም የኤርትራ መንግሥት በጤና አሰጣጥ በኩል አልታማም ብሏል።