"በምሥራቅ አፍሪካ ሐሰተኛ 'አንቲባዮቲክ' መድኃኒቶች ተሠራጭተዋል"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ጤና ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኬንያ የመድኃኒት ገበያ ሀሰተኛ አንቲባዮቲክስ መሠራጨቱን ደርሼበታለሁ ሲል አስጠነቀቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው በተለይ 'አውጉመንቲን' የተሰኘውን በባክቴሪያ የሚመጡ ሕመሞችን የሚያስታግስ ጸረ ባክቴሪያ መድኃኒት ሀሰተኛ ቅጂው በስፋት ተሠራጭቷል ብሏል።
'አውጉመንቲን' በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰቱ በርካታ ኢንፌክሽኖችን ለማዳን የሚሰጥ ወሳኝ የሚባል መድኃኒት ነው፤ በኬንያ ይህንን መድኃኒት ለመግዛት የሐኪም ትዕዛዝ ሲጠየቅ አይስተዋልም። ወደ ማንኛውም መድኃኒት ቤት ጎራ ብሎ ልክ እንደ ሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች መግዛት ተለመደ ሆኗል።
ሐሰተኛው የመድኃኒት ምርት 'ግላክሶስሚዝ ክሊነ' [GlaxoSmithKline (GSK)] ከተሰኘው ትክክለኛው ምርት ጋር ተመሳስሎ እንደተሠራ ተደርሶበታል። ይኸው ኩባንያ በበኩሉ ሐሰተኛ ምርቶቹ የኔ አይደሉም ብሏል።
786627 የሚል የምርት ቁጥር የተፃፈበት ሐሰተኛው መድኃኒት የተገኘው በድንገተኛ ፍተሻ ወቅት በተደረገ አሰሳ ነው።
በመሆኑም መድኃኒቱን የታዘዘለት ማንኛውም ሰው ከተረጋገጡና ሕጋዊ ከሆኑ መድኃኒት ቤቶች ብቻ ባለሞያ እያማከሩ ትክክለኛውን ገዝተው እንዲጠቀሙ አስጠንቅቋል።
የኬንያ መንግሥት በበኩሉ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ማሳሰቢያ ሕዝቡ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ የ'አውግመንቲን' መድኃኒትን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሲያወጣ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያው ባሳለፍነው ሚያዚያ ነበር የተላለፈው።
የሐሰተኛ ጸረ ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) መድኃኒቶች ሥርጭት ከኬንያ በተጨማሪ በኡጋንዳም መታየቱን ድርጅቱ ጠቅሷል። ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ ያለው ነገር የለም።














