ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሕፃናትና አዋቂዎች ሕክምና ምርቶች አምራች ኩባንያ ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመድሃኒትና ተያያዥ ዕቃዎች አምራቹ 'ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን' የተሰኘው አሜሪካዊ ኩባንያ ለፈፀመው ጥፋት 572 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ተወሰነበት።
ኩባንያው ኦክላሆማ የተሰኘችው ግዛት ውስጥ 'የኦፕዮይድ ቀውስ' እንዲመጣ አድርጓል በሚል አሜሪካዊው ዳኛ ኩባንያ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ዶላር እንዲቀጣ የወሰኑት።
'ኦፕዮይድ' የተሰኘው ሱስ አስያዥ መድሃኒትን በኦክላሆማ ግዛት አሰራጭዋል የተባሉ ሌሎች ኩባንያዎችም ክሳቸውን እየተከታተሉ ነው።
ድርጅቱ ከፍርዱ በኋላ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ጥር ሁለት ኩባንያ እንዲሁ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው አንደኛው 270 ሚሊዮን ዶላር ሌላኛው ደግሞ 85 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጡ መሆናቸው አይዘነጋም።
'ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን' የተሰኘው ኩባንያ ዋነኛ ጥፋት የተባለው ሱስ አስያዥ መሆኑ የታወቀ ማስታገሻ [ፔይንኪለር] መድሃኒትን ማስተዋወቅ እና መሸጡ ነው።
ከኩባንያዎቹ ቅጣት የሚገኘው ረብጣ ዶላር 'ኦፕዮይድ' በተሰኘው መድሃኒት ሱስ ለናወዙ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች መልሶ ማገገሚያ አገልግሎት ይውላል ተብሏል።
መድኃኒቱን አብዝተው በመውሰዳቸው በ18 ዓመታት [99-2017] ውስጥ 400 ሺህ አሜሪካዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ድርጅቱ የመድኃኒቱን ጉዳት አሳንሶ በማስተዋወቁ ምክንያት ሰዎች ባለማወቅ በርከት አድርገው ወስደዋልና ይህ ትልቅ ጥፋት ነው ሲሉ የግዛቲቱ ጠበቃ ሞግተዋል።
ጄኤንድጄ በተሰኘ ቅጥል ስም የሚታወቀው ድርጅት 'አኔ ከደሙ ነፃ ነኝ፤ መድኃኒታችን ውስጥ ያለው የኦፕዮይድ መጠን እጅግ አናሳ መሆኑን ሁሉም ያውቃል' ሲል ፍርዱን አምርሮ ተቃውሟል።
'ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን' የተለያዩ መድሃኒቶችን እና ቅባቶችን በማምረት ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ለሕፃናት የሚሆኑ ቅባቶች፣ ዘይቶች እና 'ፖውደር' አምርቶ በመላው ዓለም በማከፋፈል ይታወቃል።













