ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ምን ያህል እርዳታ ትግራይ ደረሰ?

የፎቶው ባለመብት, ICRC Ethiopia
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት አካላት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ከተስማሙ በኋላ በዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አማካይነት ቢያንስ አራት ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ ደርሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መጋቢት 15/2014 ዓ. ም. ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑ ይታወሳል። የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ተከትሎ ህወሓትም በተመሳሳይ ሰብአዊ እርዳታ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲደርስ ግጭት የማቆም ውሳኔ ላይ መድረሱ አይዘነጋም።
ምንም እንኳን ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ለሰብአዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርጉም በትግራይ ክልል በቂ የሰብአዊ እርዳታ እየደረሰ እንዳልሆነ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ከተሰማ በኋላ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ሰብአዊ እርዳታ ወደ ክልሉ ልከዋል።
ትላንት ሚያዚያ 6/2014 ዓ.ም. የዓለም ምግብ ፕሮግራም 47 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ መላኩን ገልጿል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትላንት በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ ምግብ ከጫኑ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ 3 ነዳጅ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ገልጿል።
ወደ ትግራይ ለ109 ቀናት ያህል እርዳታ ሳይገባ ቆይቶ ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ስምምነት ከተደረገ በኋላ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ 21 እርዳታ ጫኝ መኪኖችን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ልኮ ነበር።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ድጋፍ
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ምግብና የሕክምና ቁሳቁስን ጨምሮ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ የትግራይ መዲና መቀለ መድረሳቸውን አስታውቋል።
ቀይ መስቀል ከስድስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 24/2014 ዓ.ም. መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ወደ ትግራይ መግባታቸውን ገልጾ ነበር።
ትላንት ሚያዝያ 6/2014 ዓ.ም. በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ በሁለተኛ ዙር ምግብ፣ የውሃ አቅርቦት፣ መድኃኒት፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች እንዲሁም ሌሎችም የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪኖች መቀለ መግባታቸውን ገልጿል።
በሁለቱ ወገኖች ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበርን ጨምሮ እርዳታ ጫኝ መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።
ሆኖም ግን በትግራይ ክልል ካለው ፍላጎት አንጻር እርዳታው በቂ እንዳልሆነ ቢቢሲ ከአንድ ሳምንት በፊት ያነጋገራቸው የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር አትንኩት መዝገበ ተናግረዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም በቀን 100 እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት አለባቸው ብሎ የነበረ ቢሆንም በወራት ሂደት እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በክልሉ ያለውን የእርዳታ ፍላጎት ለሟሟላት በየቀኑ 300 መኪኖች እንዲገቡ መስማማቻተውን አቶ አትንኩት ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ለቢቢሲ በላከው ኢሜል፣ ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት እንዲቆም ውሳኔ ከተላለፈ ወዲህ እርዳታ መግባቱ በጎ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ አስምሮበታል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም በህወሓት በኩል ለሰብአዊነት በሚል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ለሰብአዊ እርዳታ የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ እንዳለቸው ገልጸዋል።












