ከስድስት ወራት በኋላ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ወደ ትግራይ መግባታቸውን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, ICRC
አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያዎችና የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ከስድስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ቅዳሜ መጋቢት 24፣ 2014 ወደ ትግራይ መግባታቸውን አስታውቋል።
መኪኖቹ በአፋር በኩል የገቡ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጾ ወደ ትግራይ የገቡት እነዚህ መኪኖች መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁሶች፣ የውሃ ፓምፖች፣ የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎችና በሶላር (በጸሓይ ኃይል) የሚሰሩ ፋኖሶች መያዛቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
ከሰሞኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 13 የእርዳታ ጭነት መኪኖች መቀለ የደረሱ ሲሆን በተጨማሪም 47 ሺህ ሊትር ነዳጅም ወደ መቀለ ከስምንት ወራት በኋላ መድረሱን አስታውቋል።
ሆኖም በጦርነቱ በተጎዳችው የትግራይ ክልል ያለውን መጠነ ሰፊ ፍላጎት ለማሟላት በየሳምንቱ 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልግልም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠቁሟል።
"በትግራይ ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ነዋሪዎች የጤና እንክብካቤ፣ በቂ የምግብ አቅርቦት እና መሰረታዊ ቁሶችንና አገልግሎት በማያገኙበት ሁኔታ እጅግ በጣም ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ነው" በማለት በኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ ተናግረዋል።
አክለውም "በተጨማሪም የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት በክልሉ የጤና አጠባበቅ ስርዓት እና በህክምና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ የጤና ማዕከላት በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ ማቆማቸውን ያስታወቀ ሲሆን በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንት እየሞቱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
"አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በአሁኑ ወቅት በተደረሰው የተኩስ ስምምነት እና የጦርነቱ ተሳታፊዎች አስፈላጊውን ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ባሳዩት ፈቃደኝነት ደስተኛ ነን" ብለዋል ኒኮላስ
አክለውም "እርዳታው በየጊዜው ወደ ክልሉ መድረሱ በጣም ወሳኝ ነው" ማለታቸውንም ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ከዚህ ቀደም ተቋሙ ከጥር ወር ጀምሮ 40 በረራዎችን በማድረግ ህይወት አድን የሆኑ እንደ ኢንሱሊን፣ ሄሞዳያሊስስ፣ ኦክሲቶሲን፣ ቴታነስ ቶክሳይድ የመሳሰሉ መድኃኒቶች እንዲሁም ጓንት እና የቀዶ ህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ ክልል ማድረስ ችሏል።
ከትግራይ በተጨማሪ በአፋር ክልል የሚገኙ 9 ሺህ ተፈናቃዮች የምግብ እህል፣ የስንዴ ዱቄት፣ አተር፣ ጨውና ዘይት የመሳሳሉ እርዳታዎችን ከተቋሙ ማግኘታቸውም ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ወደ ትግራይ የሚደርሰው እርዳታ ይጨምራል የሚል ተስፋን ሰንጥቋል።
ለአስራ ሰባት ወራት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ስድስት ሚሊዮን የሚገመት የክልሉን ነዋሪ እርዳታ ፈላጊ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትንም ለረሃብ ዳርጓል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አስራ ሰባት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።












