ከአምስት ወራት በኋላ የሕክምና መገልገያዎች ዛሬ ትግራይ መድረሳቸውን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ

የቀይ መስቀል መኪና

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጦርነት ክፉኛ ለተጎዳችው ትግራይ ከአምስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ጥር 18/2014 ዓ.ም ህይወት አድን የህክምና መገልገያዎችን ማድረሱን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ገለጸ።

ከ15 ወራት በላይ በዘለቀው ጦርነት መድኃኒትና ምግብን ጨምሮ በመሰረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት እየተሰቃየችው ላለችውም ትግራይ ይህ ዜና የተስፋ ጭላንጭል ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የጤና አስተባባሪ አፖሎ ባራሳ "የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ወደ ትግራይ ሆስፒታሎች መድረሱ ትልቅ እፎይታ ነው። ድጋፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ማስቀጠል የሚያስችል ነው" ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ጥር 18/2014 ዓ.ም አስፈላጊ መድኃኒቶችን የያዘ አውሮፕላን ወደ ትግራይ መዲና መቀለ እንደደረሱም ተገልጿል።

በመጪዎቹ ቀናትም ተጨማሪ በረራዎች እንዲሁም እርዳታ የጫኑ መኪኖችንም እንደሚልክ ድርጅቱ አስታውቋል።

ይህም ተፈጻሚ የሆነው መንግሥት በህወሓት ቁጥጥር ስር ለምትገኘው የትግራይ ክልል አስፈላጊ የሆኑ የምግብ እና የሕክምና አቅርቦቶችን በአየር ለማጓጓዝ ለማመቻቸት የገባውን ቃል ተከትሎ ነው።

ሆኖም በትግራይ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እርዳታውን በጭነት መኪኖች ለማድረስ የበለጠ ሊያወሳስበው እንደሚችልም እየተገለጸ ነው።

ድርጅቱ ቀደም ሲል በትግራይ ያለው የመድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች እጥረት የህክምና ባለሙያዎች ጓንቶችን እንደገና አጥበው እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋልም ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በትግራይ ክልል ካለፈው ዓመት ሐምሌ አጋማሽ የሕክምና ቁሳቁሶች ለማቅረብ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሊፈቀድለት እንዳልቻለ ገልጾ ነበር።

ሆኖም በጦርነቱ ለተጎዱት አማራና አፋር ክልሎች የሕክምና ቁሳቁሶች ማድረስ መቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በቅርቡ በትግራይ አንዳንድ የጤና አገልግሎቶች በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ አቁመዋል ብሏል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንት እየሞቱ መሆናቸውን ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ እንዲሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ መድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች ወደ ሆስፒታሎች ባለመድረሳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ መንግሥት ምንም አይነት እገዳ በትግራይ ላይ እንዳልጣለና በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ችግር ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።

በክልሉ መዲና መቀለ በሚገኘው ትልቁ የጤና ተቋም የሚገኙ ዶክተሮች እንደተናገሩት በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያስፈልጉ በደም ስር የሚሰጡ እና የሰመመን መስጫ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ቀዶ ህክምና ማድረግ አለመቻላቸውን ነው።

የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች ባወጡት መግለጫ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና ያልተሟላ የኦክስጂን አቅርቦት ለታካሚዎች ሞት ምክንያት ነው ብለዋል።

ጓንቶች፣ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች፣ የህመም ማስታገሻዎች፣ በምጥ ላይ ላሉ ሴቶች ወሳኝ መድኃኒቶች እንዲሁም ለተለያዩ የአዕምሮ ህመም የሚውሉ መድኃኒቶችና መሰረታዊ የላብራቶሪ ምርመራዎች በሌሉበት ሁኔታ በሆስፒታሉ ውስጥ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ጠቅሰዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ የመገልገያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንደሚጠቀሙና ያለውም ብቸኛ አማራጭ እሱ በመሆኑ አሁንም አስቸኳይ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማንም በቻሉት መጠን እየተንከባከቡ እንደሆነ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን በማደናቀፍ እርስ በእርሳቸው ሲወቃቀሱ ይሰማል።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቧል።