የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘጋቢው አሚርና የካሜራ ባለሙያው ከእስር ተፈቱ

የፎቶው ባለመብት, Social media
ለአራት ወራት ያህል በእስር ላይ የነበሩት የአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዜና ወኪል ዘጋቢው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ በዛሬው ዕለት መጋቢት 23፣ 2014 ዓ.ም በዋስ ከእስር ተፈቱ።
ጋዜጠኞቹ አሚር አማንና ቶማስ እንግዳ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠውን ውሳኔ ፖሊስ እንዲሻርለት ረቡዕ መጋቢት 21፣ 2014 ዓ.ም ይግባኝ ቢያቀርብም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ በዋስ በዛሬው ዕለት ተለቀዋል።
ማክሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጋዜጠኞቹ እያንዳንዳቸው የ60ሺህ ብር ዋስትና እንዲያሲዙና ጉዳያቸው ውሳኔ አስኪያገኝ ድረስም ከአገር እንዳይወጡ እገዳ በመጣል በዋስ ከእስር እንዲወጡ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
የኤፒ ዜና ወኪል ጋዜጠኛው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጅው ድርጅት ጋር ግንኙነት አድርገዋል በሚል ነበር ተይዘው ለወራት በአስር የቆዩት
አቃቤ ህግ በአማን ላይ ያለው ምርመራ እንደቀጠለ መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ በዛሬው ዕለት ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።
"ጋዜጠኛ አሚር አማን ኪያሮ በዋስ ተፈትቶ ከቤተሰቡ ጋር በመገናኘቱ እፎይታ ሰጥቶናል" ሲሉ የኤፒ ስራ አስፈፃሚ ጁሊ ፔስ መናገራቸውን ኤፒ በዘገባው አስፍሯል።
"ሆኖም በአሁኑ ወቅት ምርመራ መቀጠሉ ስጋት ላይ ጥሎናል።የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጋዜጠኝነት ስራው ምክንያት ኢላማ በሆነው አሚር ላይ የሚያደርጉትን መሠረተ ቢስ ምርመራ እንዲያቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን።" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሁለቱን ጋዜጠኞች ከሌላ አንድ ግለሰብ ጋር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ኅዳር ወር አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ላይ ሲሆን መያዛቸው ይፋ የሆነው ከበርካታ ቀናት በኋላ ነበር።
በጋዜጠኞቹ ላይ በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በቀረበው ዘገባ "ሽብርተኛ ቡድንን ለማስተዋወቅ ሲሰሩ ነበር" ሲል ፖሊስ ገልጾ ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ በነበረበት ወቅት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ አሚር እና ቶማስን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሆነው ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ቆይተው ነበር።
ጋዜጠኞቹ ለተለያዩ ጊዜያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ታስረው ከቆዩ በኋላ ብዙዎቹ በነጻ መለቀቃቸው ይታወሳል።
አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለሦስት ወራት ያህል በእስር ላይ ቆይተው ጉዳያቸው በተከታታይ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ነው ዛሬ በዋስ የወጡት።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ በመቀጠል ሁለተኛ ናት ማለቱ ይታወሳል።












