በዋስ እንዲለቀቁ በተፈቀደላቸው ጋዜጠኞች ላይ ፖሊስ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Social media
ሁለት የአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ጋዜጠኞች በዋስ እንዲለቀቁ ከተወሰነ በኋላ ፖሊስ ያቀረበውን ይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።
ማክሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለወራት በእስር የቆዩት የኤፒ ዜና ወኪል ጋዜጠኛው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ በዋስ ከእስር እንዲወጡ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኞችን ይዞ ለመመርመር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመጥቀስ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቦ ነበር።
የጋዜጠኞቹ ጠበቃ መላኩ ኦጎ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ለተጨማሪ ቀናት ይዞ ለመመርመር የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበ በመጥቀስ አቤቱታውን ውድቅ እንዳደረገ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠበቃው መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ይዞ ለማቆየት ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን ዳግም ሊያቀርብ ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል።
የኤፒ ዜና ወኪል ጋዜጠኛው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አድርገዋል በሚል ነበር ተይዘው ለአራት በእስር ላይ የሚገኙት።
ከቀናት በፊት ሁለቱ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ሲወስን፣ እያንዳንዳቸው የ60ሺህ ብር ዋስትና እንዲያሲዙና ጉዳያቸው ውሳኔ አስኪያገኝ ድረስም ከአገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 20 የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተከትሎ የአሚር አማን ታናሽ ወንድም የሆነው ናድር አማን፤ አሚርን ለማስፈታት የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ለመክፈል ቤተሰቡ ጥረት እያደረገ እንደነበረ ተናግሯል።
ሁለቱን ጋዜጠኞች ከሌላ አንድ ግለሰብ ጋር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ኅዳር ወር አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ላይ ሲሆን መያዛቸው ይፋ የሆነው ከበርካታ ቀናት በኋላ ነበር።
በጋዜጠኞቹ ላይ በመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በቀረበው ዘገባ "ሽብርተኛ ቡድንን ለማስተዋወቅ ሲሰሩ ነበር" ሲል ፖሊስ ገልጾ ነበር።
የጋዜጠኞቹ አሰሪ የሆነው አሶሺየትድ ፕሬስ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በመንግሥት የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረገው ሲሆን፣ "አሚር ኢላማ የሆነው የጋዜጠኝነት ሥራውን በማከናወኑ መሆኑ ግልጽ ነው" ብሏል።
"አሚር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭት ውስጥ ሁሉንም የሚመለከት ጠቃሚ ሥራዎችን ያከናወነ ነጻ ጋዜጠኛ ነው" ብሏል በመግለጫው ላይ።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ በነበረበት ወቅት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ አሚር እና ቶማስን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሆነው ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ቆይተው ነበር።
ጋዜጠኞቹ ለተለያዩ ጊዜያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ታስረው ከቆዩ በኋላ ብዙዎቹ በነጻ መለቀቃቸው ይታወሳል።
አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለሦስት ወራት ያህል በእስር ላይ ቆይተው ጉዳያቸው በተከታታይ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ነው ዛሬ በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነው።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ በመቀጠል ሁለተኛ ናት ማለቱ ይታወሳል።












