የቀድሞ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ገላሳ ዲልቦ አረፉ

አቶ ገላሳ ዲሊቦ

በኢህአዴግ የሽግግር ወቅት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀ መንበር የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት የፓርላማ አባሉ አቶ ገላሳ ዲልቦ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸውን አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እኚሁ የቤተሰብ አባል "ሌሊት ላይ በድንገተኛ ህመም መሞታቸውን" ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሞታቸው ከተሰማ በኋላም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሃዘናቸውን በክልሉ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ማኅበራዊ ትስስር ገፅ አስፍረዋል።

"ኦሮሚያ አንድ ዋርካ አጥታለች። በኦሮሞ የነፃነት ትግል ውሰጥ ትልቅ ስም የነበራቸው፤ በአስቸጋሪ ወቅቶች እድሜያቸውን ለአሮሞ ህዝብ እየታገሉ ያሳለፉት ገላሳ ዲልቦ ከዚህ ዓለም በመለያታቸው የተሰማኝን ሃዘን እየገለፅኩ ለኦሮሞ ሕዝብ መፅናናትን እመኛለሁ" ብለዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አንዱ መስራች የሆኑት አቶ ገላሳ ዲልቦ ባለፈው ዓመት በነበረው ምርጫ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጎላኦዳ ቁምቢ መልካ በሎ ወረዳዎችን በመወከል በግል ተወዳድረው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።

አቶ ገላሳ ዲልቦ ለረጅም ዓመታት በስደት ኑሯቸውን በለንደን አድርገው የነበሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በውጭ አገራት የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ አንጋፋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነበሩ።

አቶ ገላሳ ከቢቢሲ በነበራቸው ቆይታ ከ27 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ ኢህአዴግ ሥልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ በነበረው የሽግግር መንግሥቱ ጉባኤ ላይ መሳተፋቸውንና ከሁለት ቀናት በኋላ በህመም ምክንያት ወደ አውሮፓ ሄዱ።

ህክምና አግኝተው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቢመለሱም የወቅቱ ሁኔታ እንደጠበቁት አላገኙትም "ሁኔታዎች ስለተበላሹ ተመልሰን ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት ተገደድን። በሽግግሩ ወቅት የኦነግ ሊቀ መንበር የነበርኩት እኔ ነበርኩኝ" ብለዋል።

በአሁኑ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው የኦነግ ፓርቲ የወጡት በአውሮፓውያኑ 1998 የኦነግ መከፋፈልን ተከትሎ ሲሆን፣ "አባኦ ቃማ ጨኡምሳ" የሚባል ሌላኛውን የኦነግ ፓርቲን መስርተው በሊቀ መንበርነት ለረጅም ዓመታት ሲያገለልግሉ ነበር።

አቶ ገላሳ ዲልቦ የተወለዱት ምሥራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ሲሆን አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ነበር የተከታሉት።

በአውሮፓውያኑ 1974 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የገቡ ቢሆንም የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ደርግ ሥልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ለትግል ወደ ሶማሊያ መሄዳቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር።

ሆኖም የሶማሊያ መንግሥት ወደ አገር ቤት ስለመለሳቸው በአገር ቤት የነበረውን የትጥቅ ትግል መቀላቀላቸውንና የትግል ሕይወታቸውም በዚያው እንደተጠነሰሰም በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።