"ኢትዮጵያ ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መሻገር አለባት"- ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ያቀረበው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና "ኢትዮጵያ ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መሸጋገር እንዳለባት" ሲሉ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

አገሪቷ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ቀውስ ውስጥ እንደገባች የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ ከእንደዚህ አይነት ፈተና መውጣት የሚቻለውም "በሃቀኛ ድርድር" መሆኑን አስምረዋል።

"ኢትዮጵያ መቀጠል አለባት የሚሉና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ኃይሎች፣ ቁጭ ብለው አገሪቷንና ሕዝቦቿን ለመታደግ የሚፈልጉ ኃይሎች ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ አገሪቷ እንድትሻገር ቁጭ ብለን መነጋገር፣ መደራደር ያስፈልጋል" ብለዋል።

አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ከገባችበት ጦርነት፣ እልቂት፣ ረሃብና በሚሊዮኖች መፈናቀል መውጣት የምትችለውም ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።

"ኢትዮጵያ በቃት፤ በታሪኳ ያላየችው እልቂት ውስጥ ገብታለች። ከዚህ በኋላ ከመገዳደል ፖለቲካ መውጣት አለባት። የሰለጠነው ዓለም ከዚያ የወጣው የተሳካ ብሔራዊ መግባባት፣ የተሳካ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሁም የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በማድረግ ነው።"

ኦፌኮ አዲስ አበባ ውስጥ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ጉባኤው በአገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች፣ በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ጉዞ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በተካሄደው ለውጥ ዙሪያ በመወያየት የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በዚህም መግለጫው በአገሪቱ ብሔራዊ ምክክር ላይ እንደማይሳተፍ አስታውቋል።

ለኦፌኮ በብሔራዊ ምክክሩ የማይሳተፍበት ዋነኛ ምክንያቶች በመሠረታዊነት ኮሚሽኑ ማሟላት የነበረበት ነፃና ገለልኛነት እንዲሁም አካታች ባለመሆኑ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።

ነፃና ገለልተኛ ያልሆኑ ተቋማት ዳኝነት መስጠት እና ማግባባት እንደማይችሉ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ በተመሳሳይ መልኩ ሁሉንም አካላት ማካተት ካልቻለ ትርጉም የለሽ መሆኑን ያሰረዳሉ። ለዚህም የሚያነሱት በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች በዚህ ምክክር አለመሳተፋቸውን ነው።

አሁን የተቋቋመው ኮሚሽን "ጫካ ያሉትን የኦሮሞ ታጣቂዎች ይጨምራል ወይ? ሄደው ማነጋገር ይችላሉ ወይ? ማግባባት ይችላሉ ወይ?" በማለት የሚጠይቁት ፕሮፌሰር መራረ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቀናቃኝ ኃይሎችን ወደ አንድ መድረክ ማምጣት እንደማይችሉም ያስረዳሉ።

በትግራይ ያሉትን በሁለት መቶ ሺዎች የሚሆኑ ሠራዊት በመጥቀስ እንዲሁም የኦሮሞ ታጣቂዎችን፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች፣ የጋምቤላ ታጣቂዎችን በማንሳት "እነሱን ምን አድርጎ ጠመንጃ እንዲያስቀምጡ ያደርጋል? ምን አድርጎ ነው ጠመንጃ አስቀምጡ ሊል የሚችለው። እና እነሱስ ይሰሙታል ወይ?" በማለት ይጠይቃሉ።

አክለውም "በተለይም ሁለቱን መሠረታዊ ጉዳዮች ያላሟላና የገዥው ፓርቲ በራሱ 98 በመቶ በተቆጣጠረው ፓርላማ ራሱ መልምሎ ራሱ አሰማርቶ ብሔራዊ መግባባት አምጡ ቢል ብሔራዊ መግባባት ይወልዳሉ? ምንድን ነው የሚያደርጉት? ተቀናቃኝ ወገኖች አልተስማሙበትም" ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

መንግሥት እነዚህ ኮሚሽነሮች በሕዝብ ነው የተመረጡት በሚልም ቢቢሲ ፕሮፌሰር መረራን የጠየቃቸው ሲሆን እሳቸውም ታሪክን ዋቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ምርጫ "የይስሙላ" ሲሉ ተናግረዋል።

አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ መጨረሻ ዘመናቸው የተመረጠ ፓርላማ ይሉ እንደነበር ደርግም ሪፐብሊክ በማለት ሕዝብ እንደመረጠው እንደሚናገር ባለፉት 27 ዓመታትም ኢህአዴግ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ይል እንደነበር ጠቅሰዋል።

"እውነታው ግን እንዳልመረጣቸው አይተናል። ይሄ ሁኔታ ኢትዮጵያን እዚህ አድርሷታል" ብለዋል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ምርጫ በተመለከተም፣ ምርጫው መፍታት የነበረበትን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አልፈታም ይላሉ። እነዚህም ሰላምና መረጋጋት፣ ዲሞክራሲያዊ ስሥዓት እንዲሁም ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያው ልማትና ብልጽግና ማምጣት አልተቻለም ይላሉ።

"በኢትዮጵያ ታሪክ ያልታየ ረሃብ ተፈጥሯል። ለሺዎች ዓመታት አንድ ላይ የኖሩት አማራና ቅማንት እልቂት ውስጥ ገብተዋል። ለሺዎች ዓመታት አንድ ላይ የኖሩት አገው፣ አማራና ትግራይ የተፈጠረውን እልቂት መጥቀስ ይቻላል። እኛ እያልን ያለነው ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ እንሸጋገር ነው" በማለት ያስረዳሉ።

ብሔራዊ ምክክር ያስፈልጋል ሲል የነበረው ኦፌኮ እንደመሆኑ መጠን በሕዝብ አለመመረጣቸውንና ነፃ አለመሆኑን በተመለከተ ምን ማስረጃ አለዎት? የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ ቀርቦላቸው ነበር።

ኮሚሽነሮቹን በግለሰብ ደረጃ ከሆነ ስድስቱን በቅርበት እንደሚያውቋቸው፣ ነገር ግን ጥያቄው ኮሚሽነሮቹን የማወቅና ያለማወቅ ሳይሆን ሂደቱን የተመለከተ ነው።

"ሂደቱ የተበላሸ ወይም ሳይወለድ የሞተ ኮሚሸን ነው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ እንደ ምክንያት ብለው የሚያነሱትም በውይይቱ ላይ ዋነኛ ተቃናቃኞች አለመኖራቸውን በመጥቀስ ነው።

"ገዢው ፓርቲውና ደጋፊዎቹ በፈለጉበት ወቅት ፓርላማ ሊወያዩ ይችላሉ። ተቀናቃኝ ኃይሎች ይህ ኮሚሽን ሊያግባባን ይችላል ወይ ብሎ የማመንና ያለማመን ጉዳይ ነው። ይሄ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማግባባት ወይም ማሻገር ይችላል ብዬ አላምንም። ሂደቱ መንገድ የሳተ ስለሆነ ነው" ይላሉ።

በተለይም የተለያ አካላትን ለማወያየት እንዲህ አካሄድ እንዳለው ጠቅሰው በኢትዮጵያ ሽምግልና በሚለው አሰራር እያንዳንዱ ወገን የራሱን ሽማግሌ የሚቆጥርበት፣ በሌላው ዓለም ደግሞ ሦስተኛ ወገን የሚባል እንደሚሳተፍበት ጠቅሰው በኢትዮጵያ ያለው አካሄድ ይሄንን የተከተለ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮም ድርድር እንደሚያስፈልግ ሲናገሩ መቆየታቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መረራ፣ ከዚህም ባለፈ መንግሥት በኮሮና ወረርሽን ምክንያት ምርጫ ማራዘምን እንዲሁም ከህወሓት ጋር ጦርነት መግባትን እንደማያስፈልግ መምከራቸውንም ያስታውሳሉ።

ኦፌኮ በተደጋጋሚ ድርድር ሊደረግ ይገባል በሚል ከመጠየቁም አንጻር ጥያቄያቸው በምርጫ ሳይሳተፉ ሥልጣን የመያዝ ጥያቄ ይሆን? በሚል ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

እሳቸውም ሲመልሱ "ሥልጣን የሕዝብ ነው። ከምርጫ ተገፍተን ወጥተናል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በምርጫ አልተሳተፈም። ምርጫው ነፃ ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው አይደለም" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የነበረውንም የኢትዮጵያ ምርጫ ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በበርካታ ስፍራዎች ምርጫ አልነበረም ይላሉ።

"ትልቁ የኢትዮጵያ አካባቢ ኦሮሚያ ነው፤ በዚህ አካባቢ ምርጫ አልነበረም። ምርጫ አለ ማለት ተወዳዳሪ አለ ማለት ነው። ገዢው ፓርቲ ከራሱ ጋር ብቻ ነው የተወዳደረው። ከራስ ጋር ለመወዳደር የሕዝብ ሀብት ለምን ይፈሳል?" ሲሉ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልልም እንዲሁ የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ተገፍቶ መውጣቱን በመጥቀስ "ከሞላ ጎደል ምርጫ የሚመስል የነበረው አማራ ክልልና አዲስ አበባ ብቻ ነው" ይላሉ።

በሌሎቹ አካበቢዎች በቤንሻንጉል ጉመዝ ክልል በአብዛኛው እንዲሁም በትግራይ ምርጫ አለመካሄዱን ዋቢ በማድረግ በርካቶችን ያላሳተፈና የምርጫ ደረጃን የሚመጥን እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

"ሥልጣን የሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ነው የሚሰጠው ይፍረድ። ይህ አገር መሻገር የሚችለው በብሔራዊ መግባባት የታጀበ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ፣ በገለልተኛ አካል የሚመራ ምርጫ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ነው ተቀባይነት ያለው ምርጫ የሚሆነው" ብለዋል።