ኢትዮጵያን የሚመለከተው ኤስ3199 ረቂቅ ሕግ ወደ አሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ያረቀቀውን ኤስ3199 ረቂቅ ሕግ አጸደቀ።
ኮሚቴው በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት ወይም 'The Ethiopia Peace and Democracy Promotion Act' በሚል ያረቀቀውንና ኤስ3199 የተሰኘውን ይህን ህግ በትናንትናው እለት መጋቢት 20፣ 2014 ዓ.ም ካጸደቀም በኋላ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት መርቶታል።
ማከሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም በከፍተኛ ድምፅ ያለፈው ይህ ረቂቅ ሕግ ለኢትዮጵያ መንግሥት በፀጥታ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ ከማገድ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ፣ ከጦርነቱ የሚያተርፉ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲባባስ በገንዘብ እንዲሁም በቀጥታ የተሳተፉ አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ነው።
ረቂቅ ሕጉ ከቀረበበት ከወራት በፊት የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መልክ መቀየሩን የተናገሩት የምክር ቤቱ አባል ጂም ሪሽ፣ ሆኖም በዋነኝነት መሠረታዊ ጉዳዮቹ ተመሳሳይ መሆናቸውን መናገራቸውን የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ረቂቅ ሕጉ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ለፈጸሟቸው መጠነ ሰፊ ጥሰቶችና አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቸችም አስምረዋል።
በተጨማሪም በዚህ ጦርነት ከፍተኛ ስፍራ ያላቸውን የውጭ አገራት ሚናም እትኩሮት እንደሚሰጥ አውስተዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥት የታወጀውን የአንድ ወገን ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ጥሩ እመርታ ነው ያሉት የምክር ቤቱ አባል ነገር ግን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ አሁንም ቅንጣት እርምጃ አልተሄደም ብለዋል።
በተጨማሪም ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ አልደረሱም እንዲሁም ወደ ድርድር ለመምጣት አለመስመማታቸውን ጠቅሰው "ለብሔራዊ እርቁም መንገዱ ረጅም ነው" ብለዋል።
"ይህ ረቂቅ ሕግ ኮንግረሱ መጠየቅ ያለባቸውን አካላትን በተመለከተና ግጭቱን በመፍታት ረገድ ጠንካራ አቋም እንዳለው ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋል" ማለታቸውም መግለጫው አትቷል።
የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሮበርት ሜንዴዝ በበኩላቸው ረቂቅ ሕጉ በከፍተኛ ድምፅ በማለፉ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
"በዛሬው ዕለት ከፍርድ ውጭ የተደረጉ ግድያዎች፣ የጅምላ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የግዳጅ መፈናቀል እና የሰብዓዊ እርዳታ እገዳዎችን እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ የምንናገርበት ብቻ ሳይሆን እነዚህን አሰቃቂ ድርጊቶች ለማስቆም እርምጃ የምንወስድበት ነው" ብለዋል።
ሴናተር ሜንዴዝ እንዳሉት "ድርጊቶቹ የጦር ወንጀሎች፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት ጋር ሆነው እንዲቆጠሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ወክለው ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የምክር ቤቱ አባል ክሪስ ኩን በበኩላቸው፤ ከዚህ ጉብኝት በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ግጭት የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብዓዊ ምላሽ የሚያጠናክረውን ይህንን ረቂቅ ሕግ ማስተዋወቃቀቸውን ገልጸዋል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ የተደረገው የተኩስ ማቆም እና የተሻሻለ ሰብዓዊ አገልግሎት አቅርቦትን በተመለከተ የተደረጉ አዎንታዊ ሁኔታዎች እንደ በጎ ማየታቸውን ቢጠቅሱም "የግጭቱ ተሳታፊዎች ከቃላት ይልቅ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል። ዘ ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ስታብላይዜሽን አክት ለዚህ ጥረት ጠቃሚ መሳሪያ ነው" ማለታቸው ሰፍሯል።
በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የቀረበው ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለመደገፍ የአሜሪካ አስተዳደር ዲፕሎማሲያዊ፣ ልማታዊ እና ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅና ይህንንም ሂደት እያደናቀፉ ያሉ አካላት ላይ አስተዳደሩ ማዕቀብ የሚጥልበትን ማዕቀፍ ለመፍጠር ማለሙንም አሜሪካ አስታውቃለች።
ይህን ረቂቅ ሕግ ለሴኔቱ ያስተዋወቁት የኒው ጀርሲው ሴናተር ሮበርት ሜንዴዝ ናቸው። ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም. ለሴኔቱ ቀርቦ ለሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተመርቶ ነው ውይይት ተደርጎበት ወደ ቀጣዩ ሂደት እንዲያልፍ የተደረገው።
ረቂቅ ሕጉ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርቦ ሌላ ዙር ውይይት የሚደረግበት ሲሆን ሴኔቱ የሚያጸድቀው ከሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ይቀርባል፣ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎት ካለፈ በቀጣይነት ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ ፊርማቸውን ካኖሩበት ሕግ ሆኖ ተግባራዊ ይሆናል።
በተመሳሳይ ሌላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የተመለከተ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት መተዋወቁ ይታወሳል።
ይህ ረቂቅ ሕግ ኤችአር 6600 የሚባል ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ የተቃወማቸው እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በፕሬዝዳንት ባይደን የሚጸድቁ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ትጥላለች።
ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 01/2014 ዓ.ም. ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ ረቂቅ ሕጉ ለምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች፣ ፍትሕ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለጦር ኃይል አገልግሎቶች ተመርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Hermela Aregawi
ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ ይዘት ምንድነው?
በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታ እና የሰብዓዊ መብት መከበርን እንደምትደግፍ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለተከሰተ ግጭት መፍትሄ እና እርቅ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፏን እንደምታደርግ ረቂቅ ሕጉ ያትታል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሚደረጉ የሰላም፣ የመረጋጋት እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥረቶችን በሚያደናቅፉ ግለሰቦች ላይ የንብረት እና የጉዞ እግድ ይተላለፍባቸዋል ይላል።
ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ከወጣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር መሳሪያ አትልክም። በአሜሪካው "Better Utilization of Investments Leading to Development Act of 2018" መሠረት ዋሽንግተን በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ድጋፍ አታደርግም።
እንደ ኤችአር 6600 ሁሉ ኤስ3199 ረቂቅ ሕግ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ትጠቀማለች ይላል ረቂቅ ሕጉ።
እነዚህ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ እና ጦርነቱን ለማብቃት የሚደረጉትን የሰላም ጥረቶች የሚያደናቅፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራዎች ናቸው በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ ተቃውሟቸዋል።
እንዲሁም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕጎቹ እንዳይጸድቁ ጥረትና የተቃውሞ ሰልፎች እያደረጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሕጎቹን መጽደቅ የሚደግፉ ኢትዮጵያውያንም ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።












