ኦፌኮ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ሁሉን ያሳተፈ ብሔራዊ ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, ofc/fb
ለሁለት ቀናት ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አጠቃላይ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
ኦፌኮ አዲስ አበባ ውስጥ ባካሄደው ጉባኤው በአገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች፣ በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ጉዞ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ በተካሄደው ለውጥ ዙሪያ በመወያየት የአቋም መግለጫውን እንዳወጣ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት ኦፌኮ በአገሪቱ መጥቶ የነበረው የለውጥ ሂደት እና ወደ ዲሞክራሲ ሥርዓት የመሸጋገር ዕድል ተቀልብሷል ካለ በኋላ፣ ይህም ወደ ተስፋ መቁረጥ፣ ወደ የእርስበርስ ጦርነት እና "በአገሪቱ ላይ የመፈረስ አደጋን ደቅኗል" ብሏል።
ፓርቲው በአገሪቱ ውስጥ ለተከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት "ወደ ዲሞክራሲያዊ ሕብረ ብሔራዊ ሥርዓት ግንባታ መስመር መመለስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ ነው" በማለት አቋሙን ገልጿል።
የኦፌኮ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በዚህ መግለጫ በአጠቃላይ በአገሪቱ፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ስላለው የሰላም ሁኔታና በብሔራዊ ምክክር ዙሪያ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
የኦፌኮ ጉባኤተኞች በዚህ መግለጫ በአገሪቱ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው የእርስ በርስ ጦርነት ሐዘናቸውን ገልፀዋል።
ኦፌኮ በመግለጫው መንግሥት በቅርቡ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ ያደረገውን አካሄድ በበጎ እንደሚመለከተው ጠቅሷል።
ሁለቱም ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማቆም የደረሱበት ውሳኔ በቶሎ ወደ ተግባር እንዲለወጥና ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ እንዲሁም ግጭት መልሶ እንዳይቀሰቀስ በአፋጣኝ ከስምምነት ላይ እንዲደርስ ጥሪ አቅርቧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በኦሮሚያ ያለው ጦርነት ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱን የገለጸው መግለጫው፣ መንግሥት በሌላው የአገሪቱ ክፍል ያለውን ጦርነት ለማብቃት የጀመረውን የሰላም እርምጃ ኦሮሚያ ውስጥም ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በዚህም ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ጋር ያለው አለመግባበት በአስቸኳይ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ በመጠየቅ "ሰላማዊ ኦሮሚያ ሳትኖር አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ያላት ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም" በማለት ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ አሁን የተጀመረው ሂደት ላይ ያለውን ስጋት አንጸባርቆ፣ ምክክሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ፣ ገለልተኛና ተአማኒነት ባላቸው አካላት የሚመራ አካል የአገሪቱን ችግር ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም መሠረት የተሳካ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት በማቆም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል።
ጨምሮም በግጭቱ ውስጥ ካሉ ኃይሎች ጋር ድርድር ለማድረግ ያሉ የሕግ ማነቆዎች ሙሉ በሙሉ በማንሳት ብሄራዊ ምክክር ላይ እንዲሳተፉ እንዲደረግና የብሔራዊ ምክክሩ አዋጅ በጋራ ስምምነት እንዲዘጋጅ እንዲሁም ኮሚሽነሮቹም ምክክሩ ላይ በሚሳተፉ አካላት ሊመረጡ ይገባል ብሏል።
ቅዳሜና እሁድ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሊቀመንበርነት እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር እንዲቀጥሉ ሲወስን አቶ ጃዋር መሐመድ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።
ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰፊ ተጽእኖ አላቸው ከሚባሉ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ላይ በርካታ አመራሮቹና አባላቱ በመታሰራቸው እንዲሁም ከ200 በላይ ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋታቸውን በመጥቀስ በምርጫው ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።
ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ገርባንና ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በርካታ አባላቱ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ቆይተው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር የተፈቱት።












