ግጭት ማቆም፣ ተኩስ ማቆም. . . ምን ማለት ነው? የትስ ሊያደርስ ይችላል?

ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ በሚል ከሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ላለፉት 16 ወራት ሲዋጋ የቆየው የፌደራሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ፣ በጦርነቱ ምክንያት አስፈላጊው ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ለማድረስ ባለመቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አጉራባች አካባቢዎች እየተሰደዱ መሆናቸውን አስታውቋል።

በዚህም ሳቢያ የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይፈጠር በሚል በተናጠል ግጭትን ለማቆም መወሰኑን ገልጿል። የፌደራሉ መንግሥት በዚህ ጦርነት እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በሰኔ 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት አብዛኛውን የትግራይ ክፍል ለቅቆ ሲወጣ፤ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እና የትግራይ አርሶ አደሮች በክረምቱ የእርሻ ሥራ እንዲያከናውኑ ለማስቻል በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ እንደነበረ ይታወሳል።

ነገር ግን በወቅቱ መንግሥት አውጆት የነበረው የተናጠል ተኩስ አቁም በህወሓት በኩል ተቀባይነትን አላገኘም ነበር። በዚህም ሳቢያ አማጺያኑ በአፋርና በአማራ ክልሎች በኩል ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ጥቃት በርካታ ከተሞችን በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ለመቃረብ ችለው ነበር።

ኋላ ላይ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱንና የክልል ኃይሎችን አስተባብሮ በጠቅላይ ሚኒስተሩ መሪነት በወሰደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መልሶ በመቆጣጠር ግጭቱ በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ተወስኖ ቆይቷል።

ከዚህ በፊት በመንግሥት በኩል ከታወጀው በተለየ ሁኔታ አሁን የፌደራሉ መንግሥት ወደ ትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ግጭት ለማቆም መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ ህወሓት አውንታዊ ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ በአስቸኳይ የሚደርስ ከሆነ ግጭት ለማቆም እንደሚስማማ ገልጿል።

ይህ መንግሥት ያሳለፈው ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ፣ ከተኩስ አቁም ስምምነት ወይም ግጭትን ለማቆም ከሚደረስ የተኩስ ማቆም ስምምነት የተለየ ነው።

በመንግሥት መግለጫ ይህ ውሳኔ "በቀጣይ ያለ ተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል" ተስፋ እንደሚያደርግ የገለጸውም ለዚህ ነው።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ በኋላም የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግጭት የማቆም ውሳኔን ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በድርድር ላይ ወደተመሠረተ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲያደርሱት መክሯል።

ለሰብዓዊነት ግጭት ማቆም(Humanitarian Truce)

የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ማቆም (Humanitarian Truce) ሆነ የተኩስ አቁም ስምምንት (Cease Fire) በአንድ አካባቢ የሚካሄድን ግጭት ለማብረድ ቁልፍ ሚና ቢኖራቸውም፣ ተፈጻሚነታቸውም ሆነ ከዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚታለፉ ዝርዝር ሁኔታዎች የተለያዩ ናቸው።

በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሁለት ጎራ ሆነው ሲፋለሙ የነበሩት አሜሪካ እና ሩሲያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለግጭት አለመፈላለግ (cessation of hostilities) የሚል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

በወቅቱ በኪንግስ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን በጦርነት ጉዳዮች ጥናት መምህር እና ፀሐፊ የሆኑት ሳሚር ፑሪ፤ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭትን መግታት/ማቆም (Humanitarian Truce)፣ ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities)፣ የተኩስ አቁም ስምምነት (Cease Fire) እና ግጭትን ማብቃት (Armistice) ልዩነቶች ላይ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

ወታደር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ግጭት መግታት(Truce)

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ከሆነ ግጭት ለመግታት ስምምነት ተደረሰ ማለት፤ በተዋጊዎች መካከል በጊዜያዊነት ተኩስ ለማቆም 'ብዙ ያልተመከረበት ስምምነት' መኖሩን ያመላክታል ይላሉ።

ተዋጊዎች ግጭት ለመግታት ከስምምነት ለመድረስ (Truce) ይፋዊ እና ሥርዓትን የተከተለ ስምምነት ላይ መድረስ አይጠበቅባቸውም።

በዚህ ውሳኔ ተፋላሚ ኃይሎች ረዥም ጊዜ የዘለቀ ጦርነት ጋብ እንዲል እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲገታ ሊስማሙ ይችላሉ።

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ከሆነ ተዋጊ ኃይሎች በሁሉም ግንባሮች ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ግንባር ብቻ ግጭት ለመግታት ሊወስኑ ይችላሉ። ለሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ተዋጊዎች ግጭትን ለመግታት ውሳኔ ሊያሳልፉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።

ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities)

ዶ/ር ሳሚር እንደሚሉት ለግጭት አለመፈላለግ (Cessation of hostilities) እንደ የተኩስ አቁም ስምምነት (Cease Fire) ይፋዊ እና ዝርዝር ነገር ባይኖረውም ግጭትን ለመግታት (Truce) ከሚደረስ ስምምነት የተሻለ ይፋዊ የሆነ ሥርዓት አለው።

ተዋጊ ኃይሎች ለግጭት ላለመፈላለግ (Cessation of hostilities) ስምምነት ደረሱ ማለት፤ ላለመዋጋት እና ሠራዊታቸው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ ተስማምተዋል ማለት ነው በማለት ያብራራሉ።

ይኹን እንጂ ይላሉ ዶ/ር ሳሚር፤ "ይሁን እንጂ፤ በግጭት ላለመፈላለግ መስማማት (Cessation of hostilities) ተኩስ ማቆም ማለት አይደለም።" ነገር ግን ይህ ለግጭት ላለመፈላለግ የሚደረስ ስምምነት ዘላቂ ለሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።

እንደ ዶ/ር ሳሚር ገለጻ ለግጭት ላለመፈላለግ የተስማሙ ተዋጊዎች በአንድ አካል ትንሽ ጠብ አጫሪነት ስምምነታቸው በቀላሉ ፈርሶ ወደለየለት ጦርነት ተመልሰው ሊገቡ ይችላሉ።

ተኩስ አቁም (Ceasefire)

በተዋጊዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት (Ceasefire) ተደረሰ ማለት፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ወገኖች በሚገዛ ስምምነት ተዋጊ ኃይሎች ግጭት ለማቆም ቁርጠኝነት አሳዩ ማለት ነው ይላሉ ዶ/ር ሳሚር።

የተኩስ አቁም ስምምነት ትጥቅ መፍታት፣ ወታደሮች ይዘዋቸው ከሚገኙ ቦታዎች መልቀቅ፣ ቀጠናዎችን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግን ሊያካትት ይችላል።

ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ግጭትን ማብቃት (Armistice)

እንደ ዶ/ር ሳሚር ገለጻ ግጭትን የማብቃት ስምምነት (Armistice) በመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚመጣ ነው።

ተዋጊ ኃይሎች ከተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ዘላቂ ሰላም ስለሚመጣበት ሁኔታ ከስምምነት ሲደርሱ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ግጭትን ለማብቃት ተስማሙ ማለት ይቻላል ይላሉ።

ግጭትን ለማብቃት የሚደረጉ ስምምነቶች ሕጋዊ ኃላፊነቶችን ይዘው ይመጣሉ።

እንደ ምሳሌም ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በይፋ እንደቆሙ ያረጋገጡት ከስምምነት የተደረሱ ግጭትን የማብቃት (Armistice) ስምምነቶች መሆናቸውን ዶ/ር ሳሚር ያብራራሉ።

ወዴት ሊያደርስ ይችላል?

በትግራይ ውስጥ ተጀምሮ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ያዳረሰው ጦርነት ከመባባሱ በፊት የተለያዩ ወገኖች መንግሥትና አማጺያኑ ንግግር አድርገው መፍትሔ እንዲፈልጉ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ጦርነቱ ተባብሶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞቱ፣ ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል እና ለተያዩ ችግሮች ከተዳረጉ በኋላ አሁንም ግጭቱና ፍጥጫው እንደቀጠለ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሠረት በሰሜን ኢትዮጵያ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በተከሰተ ሰብአዊ ቀውስ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከተጠቀሰው አሃዝ ውስጥ አብዛኞቹ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በድርጅቱ ግምት መሠረት በትግራይ ካለው ሕዝብ 90 በመቶ የሚሆነው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

ይህ በኢትዮጵያ መንግሥት የታወጀው ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም እርምጃና ህወሓትም የተቀበለው ውሳኔ ወደ ትግራይ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የእርዳታ አቅርቦት ለማድረስ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በርካቶች በዚህ እርምጃ ሌላ የሰላም ንግግር በር ሊከፈትና ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ንግግር ሊያመራ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ።