የኢትዮጵያ መንግሥት 'ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም' መወሰኑን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲደርስ ለማስቻል የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት ለማቆም መወሰኑን አታወቀ።
በመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በኩል በወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እና እንግልትን ለመቀነስ "ከተለመደው የተለየ እርምጃን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ" እዚህ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
በዚህም መሠረት ይህ ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ከሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ. ም. ከከሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ያሳለፈው በሰሜን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሲካሄድ በቆየው ግጭት ሳቢያ የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ "በእጅጉ ሊያሻሽል እንደሚችል ብሎም በቀጣይ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል" ተስፋ በማድረግ መሆኑን ገልጿል።
ጨምሮም ይህ ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ መንግሥት "በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ" ጠይቋል።
በመንግሥት በኩልም አስቸኳይ የሰብአዊ አቅርቦቶች ወደ ትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ መድረስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ተባብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጽ፤ ዓለም አቀፍ ለጋሾች እያቀረቡ ያለውን እርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርቧል።
የመንግሥት መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር፣ ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የነዳጅና የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ማመቻቸቱን እንዲሁም በአፋር ክልል በኩል አስፈላጊው እርዳታ እንዲቀርብ አስፈላጊውን ማድረጉን ገልጿል።
ነገር ግን ይህ አቅርቦት በትግራይ ክልል ያለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ባለማስቻሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ሰብአዊ እርዳታ ፍለጋ ወደአጎራባች ክልሎች እየገቡ መሆናቸውን አመልክቷል።
እየተባባሰ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑንና ይህም አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ በነጻነት ተጓጉዞ ለተረጂዎች እንዲደርስ ለማድረግ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ያወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
አክሎም ይህ መንግሥት የወሰደው እርምጃ እና ቁርጠኝነት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ በማሻሻል የሚኖረው ስኬታማነት የሚወሰነው "ሌላኛው ወገን በተመሳሳይ ለዚህ አላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት" መሆኑን በማመልከት ህወሓትም የበኩሉን ማድረግ እንዳለበት ገልጿል።
በዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ባሳለፈው ውሳኔ ዙሪያ ከህወሓት በኩል ያለው ምላሽ እስካሁን አልታወቀም።
ይህ የመንግሥት ውሳኔ ይፋ የሆነው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርገው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዋነኛ ትኩረት በጦርነት ብዙ ምስቅልቅል ባጋጠመው ትግራይ ክልል እና በሌሎችም አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ይህንን በተመለከተም ሳተርፊልድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተቋረጠ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ቁርጠኛ ቢሆንም፣ በህወሓት ታጣቂዎች ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ እክል እየገጠመው መሆኑን ለልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ካለፈው ታኅሣሥ ወር ወዲህ ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ አቅርቦት በየብስ አለመድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ ምግብ ለማግኘት ከፌደራል መንግሥቱና ከክልል ባለሥልጣንት ፈቃድ ማግኘቱን ከቀናት በፊት አስታውቋል።
በ2013 ዓ. ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
ጦርነቱ እስካሁን መቋጫ ስላላገኘ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስና እርዳታ ለማቅረብ አስቻጋሪ በመሆኑ በአስቸኳይ እርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የእርዳታ ድርጅቶች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እገዳ ጥሏል በማለት ሲከስ መንግሥት ደግሞ በእርዳታ አቅርቦት መስመሮች ላይ ጥቃት በመክፈት የእርዳታ አቅርቦትን ያስተጓጎለው አማጺው ኃይል ነው ሲል ይወቅሳል።














