ደራርቱ ቱሉ በአትሌቶች የሽልማነት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰላም እንዲወርድ ተማጸነች

የፎቶው ባለመብት, "የአልቤርቶ ሳላዛር መታገድ በዮሚፍ ቀጀልቻ ላይ ምንም አያስከትልም" ሻለቃ ደራ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ትናንት ረቡዕ መጋቢት 14/2014 ዓ.ም ቤልግሬድ ውስጥ በተካሄደው የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ለተሳተፉ አትሌቶች በተከናወነ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ሰላም እንዲያወርዱ ጠየቀች።
ደራርቱ ቱሉ በ18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፈው ኢትዮጵያ የውድድሩ የበላይ ሆና እንድታሸነፍ በማድረግ ድል ተጎናጽፈው ለተመለሱት የአትሌቲክስ ቡድኑ አባላት በተደገረው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ጦርነቱ እንዲቆም ተማጽናለች።
"ትግራይ ትናንም ኢትዮጵያ ናት። ዛሬም ኢትዮጵያ ናት። ነገም ኢትዮጵያ ናት። እባካችሁ መሪዎቻችን፤ እባካችሁ፤ ተጠቅማችሁ ሳይሆን ተጎድታችሁ ኢትዮጵያን አንድ አድርጓት። ይህን ከፈጣሪ ጋር ትችላለሁ" ስትል ደራርቱ ጥሪ አቅርባለች።
ኮማንደር ደራርቱ ስሜታዊ ሆና እያነባች ባደረገችው በዚህ ንግግር "የትግራይ እናቶች እና አባቶች፤ እናቶቻችን እና አባቶቻችን ናቸው። በእርግጠኝነት ደግሞ ነገ ሌላ ቀን ነው። ኢትዮጵያ ታርቃ አንድ ሆና ትቆማለች" ብላለች።
በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፈው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን በመጥቀስም፤ ለአትሌቶቹን "አይዟችሁ አይክፋችሁ። ነገም ሌላ ቀን ነው። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋችሁ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ስላደረጋችሁ በጣም እናመሰግናለን" በማለት ኮማንደር ደራርቱ ምስጋናዋን አቅርባለች።
ከመጋቢት 9 እስከ 11/2014 ዓ.ም. በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ በተካሄደው 18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።
በቤት ውስጥ የዓለም ሻምፒዮናው በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብር እና በሁለት ነሐስ በድምሩ በዘጠኝ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ በአንደኛነት አጠናቃለች።
ከትግራይ የተገኙ ሴት አትሌቶች አሰልጣኝ የሆኑት ህሉፍ ይህደጎም በመድረኩ ላይ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ በዚህ ውድድር በ3,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው ለምለም ኃይሉ፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወርቅ ያስገኘችው ጉዳፍ ጸጋዬ እና በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው ፍሬወይኒ ኃይሉ አሰልጣኝ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, ALEX PANTLING
አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ የሚያሰለጥኗቸው ሦስቱ አትሌቶች በ18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ወደ ቤልግሬድ ከመጓዛቸው በፊት ለምምድ የሚያደርጉበት ቦታ አጥተው ተቸግረው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ካለው ሁኔታ አንጻር ብዙ ትራክ ስላላገኘን ከትራክ ውጪ አፈር ላይ ነው ልምምድ ያደረግነው" ያሉ ሲሆን በመሰል ተጽእኖዎች እና በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ያሉ የቤተሰሰብ አባላቶቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው "የልጆቹን ሥነ ልቦናም ማገዝ ነበርብን" ሲሉ አሰልጣኝ ህሉፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በትናንትናው መድረክ ላይ "ስፖርት ወንድማማችነት ነው፣ ፍቅር፣ ሰላም ነው። እነዚህ ልጆች [አትሌቶች] ምንም ሳይበግራቸው ለሰላም ቆመው ለውጤት በቅተዋል" በማለት ፖለቲከኞችም ለልዩነቶቻቸው መፍትሄ ሰጥተው አገር ሰላም እንድታገኝ ተማጽናለች።
"ብሔር ሳንለይ፣ ጾታ ሳንለይ ባንዲራ ያነሳነው ስለተባበርን ነው፤ . . . የትግራይ መሪዎችም ሆናችሁ የኢትዮጵያ መሪዎች እባካችሁ፣ እባካችሁ ስለ ኢትዮጵያ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ አንድነት፤ እና ሰላም ስትሉ አንድ ሁኑ" በማለት ደራርቱ ጠይቃለች።
በኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት የሆነችው ደራርቱ ቱሉ በውድድር ዘመኗ በታላላቅ መድረኮች ላይ በአሸናፊነት የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውለበለበች ታላቅ አትሌት ስትሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት እያመራች ትገኛለች።
ደራርቱ ከስፖርቱ ባሻገር ለአገሯና ለሕዝቡ ይጠቅማል የምትለውን ጥያቄና ሐሳቦችን በተለያዩ መድረኮች በማንጻባረቅም ትታወቃላች።












