በኢትዮጵያ የበላይነት የተጠናቀቀው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ከግራ ወደ ቀኝ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ አክሱማይት እምባዬ፣ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ጉዳፍ ጸጋዬ እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሒሩት መሸሻ።

የፎቶው ባለመብት, Alex Pantling

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ አክሱማይት እምባዬ፣ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ጉዳፍ ፀጋዬ እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ሒሩት መሸሻ

ከመጋቢት 9 እስከ 11/2014 ዓ.ም. በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ በተካሄደው 18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

በቤት ውስጥ የዓለም ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ የበላይነትን ይዛ ያጠናቀቀችው በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብር እና በሁለት ነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ነው።

በውድድሩ ከ2008 እስከ 2018 በነበሩት ተከታታይ ውድድሮች ሰንጠረዥ በአንደኝነት ስትመራው የነበረችው አሜሪካ ስትሆን፣ ዘንድሮ ይህንን የበላይነት በኢትዮጵያ ተነጥቃለች።

በውድድሩ ታሪክም በሰንጠረዡ አናት በመቀመጥ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ነች።

በዘንድሮ የቤት ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ሲዊትዘርላንድ እና ስዊዲን ኢትዮጵያን ተከትለው በውድድሩ ሰንጠረዥ ከሁለት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ የዘወትር ተፎካካሪ የሆነችው ኬንያ 1 ብር እና 1 ነሐስ በማግኘት በረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ መካተት ከቻሉት 29 አገራት በ22ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሌላኛው አፍሪካዊት አገር ኡጋንዳ ደግሞ አንድ ነሐስ ማግኘት ችላለች።

680 አትሌቶች [308ቱ ሴቶች] የተወደደሩበት የዘንድሮ 18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 136 አገራት ተሳትፈውበታል።

ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ስድተኞችን የያዘው ቡድንም የውድድሩ ተሳታፊ ነበር።

ኢትዮጵያ ለውድድሩ ከ800 እስከ 3 ሺህ ሜትር ሩጫ ላይ የሚሳተፉ 5 ወንድ እና 9 ሴት አትሌቶችን የላከች ሲሆን በወንዶች 2 ወርቅ እና 1 ብር ስታገኝ የተቀረው 6 ሜዳሊያ በሴቶች የተመዘገበ ነው።

ጉዳፍ ጸጋዬ እና ሳሙኤል ተፈራ በ1 ሺህ 500 ሜትር ለሀገራቸው ወርቅ ያመጡ ሲሆን፤ ሰለሞን ባረጋ እና ለምለም ሃይሉ ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቀዋል። ሳሙኤል ተፈራ በርቀቱ የውድድሩን ክበረወሰን አሻሽሏል።

ሰለሞን ባረጋ 1ኛ በወጣበት 3ሺህ ሜትር ለሜቻ ግርማ 2ኛ መሆን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። የተቀረውን የብር ሜዳሊያ ደግሞ ፍሬወይኒ ሃይሉ በ800 ሜትር እና አክሱማይት እምባዬ በ1 ሺህ 500 ሜትር ያስመዘገቡበት ነው።

ሒሩት መሸሻ በ1 ሺህ አምስት መቶ ሜትር እና እጅግአየሁ ታዬ 3 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በሶስት ሺህ ሜትር የሴቶች አትሌቲክስ ውድድር ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለው ደረጃ ኢትዮጵያውያኑ የተቆጠጠሩት ሲሆን አንደኛ የወጣችው ለምለም ሃይሉ በርቀቱ የውድድሩን ሪከርድ ሰብራለች።

ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር ርቀት የውድድሩን ክበረወሰን አሻሽሏል።

የፎቶው ባለመብት, Michael Steele

የምስሉ መግለጫ, ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር ርቀት የውድድሩን ክበረወሰን አሻሽሏል።

ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም ቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

የተሳታፊዎች ብዛት: 14 [5 ወንድ እና 9 ሴት]

የተወዳደሩባቸው ርቀቶች: 800፣ 1 ሺህ 500 እና 3 ሺህ ሜትር

የሜዳሊያ ብዛት: 9 [4 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሃስ]

የሜዳሊያ ብዛት በጾታ: 6 በሴቶች [2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ] 3 በወንዶች [2 ወርቅ፣ 1 ብር]

የሜዳሊያ ብዛት በርቀት: 2 ወርቅ በ3 ሺህ ሜትር፣ 2 ወርቅ በ1 ሺህ 500 ሜትር፣ 1 ብር በ800 ሜትር፣ 1 ብር በ1 ሺህ 500 እና 1 ብር በ3000 ሜትር እንዲሁም 1 ነሃስ፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር እና 1 ነሃስ በ3000 ሜትር

ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች

ወርቅ

  • ሰለሞን ባረጋ: በ3,000 ሜትር
  • ለምለም ሃይሉ: በ3,000 ሜትር
  • ጉዳፍ ጸጋዬ: በ1 ሺህ 500 ሜትር
  • ሳሙኤል ተፈራ: በ1 ሺህ 500 ሜትር

ብር

  • ለሜቻ ግርማ: በ3,000 ሜትር
  • ፍሬወይኒ ሃይሉ: 800 ሜትር
  • አክሱማይት እምባዬ: በ1 ሺህ 500 ሜትር

ነሐስ

  • ሂሩት መሸሻ: በ1 ሺህ 500 ሜትር
  • እጅግአየሁ ታዬ: በ3,000 ሜትር

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደ አውሮፓውያኑ በ1985 የቤት ውስጥ ጨዋታዎች በሚል በፈረንሳይ ፓሪስ የተጀመረ ሲሆን በ1987 የመጀመሪያው ስያሜ ተቀይሮ አሁን ያለውን መጠሪያ ይዟል።

ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ ይካሄዳል።