በማሪዩፖል ያሉ የዩክሬን ተዋጊዎች የሩሲያን የ'እጅ ስጡ' ጥያቄ ውድቅ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሞስኮ ከባድ ጥቃት ስር የምትገኘው የማሪዩፖል ከተማ አስተዳዳሪዎች የሩሲያን እጅ የስጡ ጥያቄ ውድቅ አደረጉ።
ሞስኮ በከተማዋ ያሉ ተዋጊዎች እጅ ከሰጡ፤ በማሪዩፖል ያሉ ነዋሪዎች በሰላም ከከተማው መውጣት ይችላሉ ብላለች።
ይሁን እንጂ ዩክሬን ቁልፍ የሆነችውን የወደብ ከተማ አሳልፌ አልሰጥም ብላለች።
በማሪዮፖል ከ300ሺህ ያላነሱ ሰዎች እንደሚገኙ ይገመታል። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለው መሠረታዊ አቅርቦት እያለቀ ሲሆን ሰብዓዊ እርዳታም ወደ ከተማዋ ማስገባት አልተቻለም።
የከተማዋ ነዋሪዎች ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለሳምንታት በሩሲያ ጦር ጥቃት ስር ቆይተዋል።
የሩሲያ ጦር ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ጄነራል ሚካሂል ሚዚንስቴቭ ዩክሬን ይህችን ከተማ አሳልፍ እንድትሰጠ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እስከ ሰኞ (ዛሬ መጋቢት 12) ረፋድ 5 ሰዓት ድረስ ጊዜ ተሰጥቷል ብለዋል።
ዩክሬን ጥያቄውን የምትቀበል ከሆነ፤ የዩክሬን ወታደሮች እና "የሌላ አገር ቀጥረኛ ወታደሮች" ትጥቃቸውን ፈትተው ከከተማዋ ከወጡ በኋላ፤ መንገዶች ከፈንጅ እና አደጋዎች ከጸዱ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ከተማ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋ የሩሲያው ጄነራል።
ጄነራል ሚካሂል ሚዚንስቴቭ ሲቪል ሰዎችም በምዕራብ ወይም ምሥራቅ አቅጣጫ ከከተማዋ መውጣት ይችላሉ ብለዋል።
ይሁን እንጂ እሁድ ረፋድ ላይ የማሪዩፖል ከተማ ከንቲባ አማካሪ፤ "አንድ ወታደር እስኪቀረን ድረስ እንዋጋለን" ብለዋል።
አማካሪው ፒዮትራ አንደራዩሼንኮ ሞስኮ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ከተማዋ አስገባለሁ ማለቷ የሚታመን አለመሆኑን እና ሞስኮ የከተማዋን ነዋሪዎች እያስገደደች ወደ ሩሲያ እየወሰደች ስለመሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመሳሳይ የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው የሞስኮን ጥያቄ እንደማትቀበለው አስታውቀዋል። ማሪዮፖልን መከላከላችንን አናቆምም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "እጅ መስጠጥን፣ ትጥቅ መፍታት በመለከተ ጥያቄ የለም" ስለማለታቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ማሪዩፖል ለሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ቁልፍ ስፍራ ስትሆን፤ ሩሲያ ከተማዋን ለመያዝ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለች ነው።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
ሞስኮ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የከበበች ሲሆን፤ የከተማዋን የውሃ፣ ጋዝ እና የአሌኬክትሪክ አገልግሎትን አቋርጣለች።
ከፍተኛ ጦርነት ባስተናገደችው ማሪዮፖል ከተማ ከሚገኙ ሕንጻዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት መውደማቸውን ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው አንድ ጥናት አመልክቷል። ባለፉት 3 ሳምንታት ሲካሄድ በቆየው ጦርነት ቢያንስ 2ሺህ 500 ሰዎች ሳይገደሉ እንደማይቀሩ የዩክሬን ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።
ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በግል ተሸከርካሪዎቻቸው ከተማዋን ለቅቀው የወጡ ሲሆን፤ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘውን ነዋሪ ለማስወጣት የተደረው ጥረት ግን ሩሲያ ተኩስ በመክፈቷ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።
የዩክሬን መንግሥት ዛሬ መጋቢት 12 ነዋሪዎችን ከከተማዋ ለማስወጣት 50 አውቶብሶችን ወደ ከተማዋ እንደሚልክ አስታውቋል።
ፕሬዝደንት ቮሎድሚየር ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦር ንጹሃን ዜጎች ከከተማዋ እንዳይወጡ ሆነ ብሎ ተኩስ እየከፈተ መሆኑን በመጥቀስ፤ "ይህ የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል።
"ይህ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ነው። እነሱ (የሩሲያ ጦር) በተቻላቸው መጠን በዩክሬን ከተሞች ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር የተቻላቸውን እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተቀብለዋል" ብለዋል።












