የቀድሞ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ተጫዎች ፓሪስ ውስጥ ተገደለ

ፌዴሪኮ አራምቡሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፌዴሪኮ አራምቡሩ

የቀድሞ የአርጀንቲና ራግቢ ብሔራዊ ቡድን ተጫዎች ፌዴሪኮ ማርቲን አራምቡሩ ባለፈው ቅዳሜ ፓሪስ ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉ ተሰምቷል።

ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን 22 ጊዜ የተጫወተው አራምቡሩ፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 በፈረንሳይ በተካሄደው የራግቢ የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በአስተናጋጇ ሀገር ላይ ባሳየው ብቃት አርጀንቲና በውድድሩ ሶስተኛ ሆና እንድታጠናቅቅ ወሳኙን ሚና ተጫውቷል።

የ42 ዓመቱ የቀድሞ ተጨዋች በምሽት መዝነኛ ክበብ ውስጥ ከሰዎች ጋር ሲጨቃጨቅ እንደነበረ እና ከተጫዋቹ ጋር ቃላት ሲለዋወጡ የነበሩ ሰዎች ጥቂት ቆይተው በመኪና ተመልሰው በጥይት ተኩሰው እንደገደሉት የፈረንሣይ ጋዜጣች ዘግበዋል።

የፓሪስ አቃቤ ህግ ቢሮ የግድያ ምርመራ መዝገብ የከፈተ ሲሆን ፖሊስ ሶስት ተጠርጣሪዎችን እየፈለገ እንደሚገኝ ተዘግቧል።

በ'ስታድ ዴ ፍራንስ' በሚደረገው እና ፈረንሳይ ከእንግሊዝ ጋር በምታደርገው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ አራምቡሩ የተዘከረ ሲሆን ምስሉ በስታዲየሙ ስክሪኖች ላይ ታይተዋል።

የተጨዋቹ የቀድሞ የቡድን አጋር ዲሚትሪ ያችቪሊ ለራግቢ ከፍተኛ ፍቅር ያለውን ሰው አጥተናል ብሏል።

አራምቡሩ "ሁልጊዜ መልካም፣ ንቁ እና አቅም ያለው ነው" ያለው ተጫዎቹ "ታላቅ የቡድን አጋር ከመሆኑ በላይ ራግቢን የሚወድ ሰው ነበር" ሲልም አክሏል።

አራምቡሩ በ2010 ግላስጎው ዋሪርስን ከመቀላቀሉ በፊት በፈረንሳዩ ክለቦች ፐርፒግናን፣ ቢያርትዝ እና ዳክስ ብዙ ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ሕይወቱ እስኪያልፍ ይጫወትበት የነበረው ክለቡ በተጨዋቹ "ድንገተኛ እና አሳዛኝ ሞት" መደናገጡን እና ማዘኑን አስታውቋል።

የእውነተኛ ተፋላሚ እና በሁሉም ዘንድ ተወዳጅነት ከነበረው ተጨዎች ቤተሰቦች ጋር በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ሃዘኑን እንጋራለን ሲልም ጨምሯል።